ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ የዩኤስይድ ተፅዕኖ በነፍስ አድን እና በጤና ዘርፎች ላይ እንደሚበረታ የሲቪል ማኅበረሰብ ምክር ቤት አስታወቀ
ለሦስት ወራት እንቅስቃሴው የተገደበው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ኤጄንሲ (ዩኤስኤይድ) በኢትዮጵያ "ትልቅ ድጋፍ" እንደሚያደርግ ተነግሯል።
በዋናነት በጤና፣ በትምህርት፣ በሰላም እና ዲሞክራሲ ግንባታ ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አስታውቋል።
አምስት ሺህ 300 የሚሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በአባልነት ያቀፈው ምክር ቤቱ ድጋፉ መቋረጡ በቀጥታ ማኅበረሰቡ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ "ከፍተኛ ጉዳት" እንደሚያደርስ ለቢቢሲ ገልጿል።
ድንገተኛ የሆነው እገዳው በተለይም ፋታ በማይሰጡት በነፍስ አድን እና በጤና ዘርፎች ላይ ተፅዕኖው እንደሚበረታ የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ሁሴን ተናግረዋል።
"አንዳንዶች [መርሃ ግብሮች] ፋታ የሚሰጡ ሊሆኑ ይችላሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ፋታ የሚሰጡ አይደሉም። ስለዚህ ከዚህ አንፃር ትልቅ ተፅዕኖ የሚያደርስ ነው" ብለዋል።
"በአብዛኛውን የጤና ዘርፍ የሚደግፈው ዩኤስኤይድ ነው" የሚሉት ፕሬዝዳንቱ፤ እንደ የዓለም የጤና ድርጅት እና የበሽታ መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከል (ሲዲሲ) ያሉ ተቋማትም ከፍተኛ ድጋፎችን እንደሚያገኙ ገልፀዋል።
ኤችአይቪ/ኤድስ እና ቲቢ ለመሰሉ በሽታዎች እንዲሁም ለተመጣነ ምግብ ሰፊ ድጋፍ ያደርጋል የተባለው ኤጄንሲው፤ ሚሊዮኖች ላይ ተፅዕኖውን እንደሚያሳርፍ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በተለይም ህፃናት እና እናቶች ላይ ዳፋው እንደሚያመዝን እሙን ነው።
"ያለምንም ቅድመ ዝግጅት፤ ማንም ምንም ሳይዘጋጅ በዚህ መልኩ [ውሳኔው] መምጣቱ አሳሳቢ ነው" የሚሉት በጤና ሚኒስቴር የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ያደታ፤ እርምጃው የጤና አገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነትን ሊቀንስ እንደሚችል ጠቁመዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት በኢትዮጵያ የዩኤስኤይድ ድጋፍ መታገድ ተፅዕኖ እንደሚኖረው በገለፀበት ሪፖርቱ በተለይም ብሔራዊ የኤችአይቪ/ኤድስ ምላሽ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳለው አስታውቋል።
ዓለም አቀፍ የኤችአይቪ/ኤድስ ግቦችን ለመሳካት እየተጠጋች ላለችው ኢትዮጵያ፤ በአንድ ሺህ 400 ጤና ጣቢያዎች ከግማሽ ሚሊዮን ለሚልቁ ሰዎች የሚሰጠው የየኤችአይቪ መድኃኒት እና ሕክምና ስጋት ላይ መውደቁን ዩንኤድስ ገልጿል።
በተጨማሪም 235 ሺህ በላይ ሰዎችም በኤችአይቪ/ኤድስን እና በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል ይቀርብ የነበረውን ኮንዶም እንዳያገኙ ያደርጋል ብሏል።
የድጋፉ መታገድ ምን ያህል የኅብረተሰብ ክፍሎች ይጎዳል የሚለውን "በጥንቃቄ" ለመለየት ም/ቤቱ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እየተከታተሉ መሆኑን አቶ አህመድ ገልፀዋል።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ በዩኤስኤይድ በቀጥታ የተቀጠሩ እና ኤጄንሲው በሚያቀርበው የገንዘብ ድጋፍ የተቀጠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ሠራተኞችም ከሥራቸው እየተሰናበቱ ነው።
"በየመሥሪያ ቤቱ ለድጋፍ (Secondment)፣ መንግሥትን የሚያማክሩ በርካታ ተቀጣሪዎች አሉ። ማኅበረሰቡን ለመደገፍ በተቋቋሙ ሲቪል ማኅበራት ተቀጥረው ቤሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩ፤ ኑሯቸውን የሚመሩ በርካታ ዜጎች አሉ" በማለትም ከሥራቸው የሚሰናበሩ ሰዎች ቁጥር "በጣም ብዙ ነው" ብለዋል።
ጤና ሚኒስቴር ባለፈው ሳምት ለሁሉም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች በፃፈው ደብዳቤ በዩኤስኤይድ እና በሲዲሲ የተቀጠሩ ከአምስት ሺህ በላይ ድግፍ ሰጪ ሠራተኞች ውል እንዲቋረጥ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
"በደሞዝ የሚተዳደር ማንኛውም የማኅበረሰብ ክፍል ሁለት ወር ሦስት ወር [ያለ ደሞዝ] ለመኖር ሊቸገር ይችላል። አሁን በምናየው ተጨባጭ ሁኔታ፤ በግጭት፤ በፀብ ውስጥ ባለ አገር ተጨማሪ ጫና ነው የሚሆነው" በማለት ሠራተኞች ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ገልፀዋል።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ዩኤስኤይድ በመላው ዓለም ካሉት 10 ሺህ ገደማ ሠራተኞች ከ300 የሚያንሱትን ብቻ ለማቆየት መወጠኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤትም በዩኤስኤይድ የሚደገፍ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ አቶ አህመድ ሁሴን "ሌሎቹ እንደሚደርስባቸው ዓይነት ጫና አይደለም" በማለት ተፅዕኖው ቀለል ያለ ነው ብለዋል።
ጫናው መንግሥት ላይም እንደሚያርፍ የሚያነሱት አቶ አህመድ፤ "በዚህ ድርጅት አማካኝነት ድጋፍ የሚያገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ካሉ ዕቅዱን ወደ ሌላ ያደርጋል። ስለዚህ ወደ ሌላ የቀለበሰውን ዕቅድ ተመልሶ እንዲያይ፤ መልሶ እንዲያቅድ ይገደዳል" በማለት እርምጃው የሁሉንም ቤት ያንኳኳል ብለዋል።
ለማሳያነት የጤናውን ዘርፍ የሚያነሱ ሲሆን፤ መንግሥት ክፍተቱን ለመሙላት አቅም ከሌለው ሊፈጠር የሚችለው ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
"በድህነት ውስጥ ያለ አገር ነው፤ በድህነት ውስጥ ያለ ሕዝብ ነው። በአንድ ጊዜ ሁሉንም መድረስ ስለማይቻል ዲፕሎማሲያችንን ተጠቅመን ሙከራ ማድረግ አንድ የሚጠበቅ ተግባር ነው" ብለዋል።
እግዱ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ "መደናገጥ" መፍጠሩን የገለፁት አቶ አህመድ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣንም ከፍቃዱ እና ከመደበኛ ሥራዎች ውጪ ሀብት እና ገንዘብ ለሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፍ ከልክሏል።
ባለሥልጣኑን እዚህ ውሳኔ ላይ ያደረሰው አምስት የሚሆኑ ድርጅቶች ለገጠማቸው ችግር ንብረቶቻቸውን ለማስተላለፍ ጥያቄ በማቅረባቸው መሆኑን አቶ አህመድ ተናግረዋል።
"ሲቪል ማኅበረሰቡ ፈጥኖ ወደ ሌላ እርምጃ መግባት ሳይሆን፤ ምንድን ነው ማድረግ ያለብን የሚለው ነው መቅደም ያለበት። ስለዚህ ወደ ንብረት መሸጥ፣ መለወጥ፣ ማስተላለፍ [ውሳኔ] ውስጥ በፍፁም መገባት የለበትም ከሚል እሳቤ ያደረጉት እንደሆነ ጠቅሰዋል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጫናውን ለመቀነስ አማራጭ ድጋፎችን ከሌሎች ተቋማት እንደሚያማትር ገልጿል።