ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ምን ያህል እርዳታ ስታገኝ ነበር? ትራምፕ ዩኤስኤይድን መዝጋት ይችላሉ?
የአሜሪካ መንግሥት ዋነኛው ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋም የሆነው ዩኤስኤይድ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በአሁኑ ጊዜ አጠራጣሪ ሁኔታ ላይ ያለ ሲሆን፣ በአሜሪካ እና በዓለም ዙሪያ ያሉ ሠራተኞቹ ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ ታዘዋል።
ወደ ሥልጣን በተመለሱ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በመላው ዓለም ነውጥ የቀሰቀሱት ትራምፕ የእርዳታ ድርጅቱ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድረጅት (ዩኤስኤይድ) በጀቱ እና የሰው ኃይሉ ተገድቦ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሥር እንዲሆን ማቀዳቸው ተነግሯል።
ፕሬዝዳንቱ እና ዋነኛው አማካሪያቸው ቢሊየነሩ ኢላን መስክ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ዩኤስኤይድን ሲተቹ የቆዩ ሲሆን፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ አማካይነት ድርጅቱን መልሶ የማዋቀሩን ሥራ እያካሄዱ ነው። በቀጣይ ሦስት ወራትም የዩኤስኤይድ እንቅስቃሴዎች እንዲቋረጡ ተደርገዋል።
በዚህ ጊዜም የድርጅቱ ሥራዎች ተገምግመው ቀጣይ እርምጃዎች ይፋ ይሆናሉ።እስካሁንም ዩኤስኤይድ በቀጥታ እና በሌሎች ተቋማት በኩል የሚያከናውናቸው ሥራዎች ከመቆማቸው በተጨማሪ ሠራተኞች የግዳጅ እረፍት እንዲወስዱ እንዲሁም እንዲሰናበቱ እየተደረጉ ነው።
ይህ በመላው ዓለም በምግብ፣ በጤና፣ በግብርና እና በሌሎችም ዘርፎች ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ድጋፍ የሚያደርገው የእርዳታ ተቋም መዘጋት በዓለም ዙሪያ በሚካሄዱ የሰብአዊ እርዳታ ፕሮግራሞች ላይ ጥልቅ ተጽእኖ እንደሚኖረው እየተነገረ ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከአሜሪካ ምን አገኘች?
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ መንግሥት የተለያዩ ዓይነት እርዳታ እና ድጋፎችን ከሚቀበሉ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ስትሆን፣ በዚህም የሰብአዊ፣ የጤና፣ የልማት፣ ወታደራዊ እና ሌሎችንም ድጋፎችን ስታገኝ ቆይታለች።
አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ በዓለም ዙሪያ ለእርዳታ እና ለድጋፍ የምታወጣውን ወጪ ለመገደብ እና የበለጠ ፍላጎቱን ለማሟላት በሚያስችለው ሁኔታ ለመጠቀም እየወሰደው ባለው እርምጃ የምታጣው ቀላል እንደማይሆን ይታመናል።ለመሆኑ ኢትዮጵያ በየትኞቹ ዘርፎች ከአሜሪካ ምን ያህል ድጋፍ ታገኛለች?
የአሜሪካ መንግሥት በዩኤስኤይድ እና በሌሎችም ተቋማቱ አማካኝነት ለአገራት የሚሰጠውን የእርዳታ እና የድጋፍ መጠንን በተመለከተ ባወጣው መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ከግብፅ በመቀጠል በአፍሪካ ከፍተኛውን ድጋፍ የምታገኝ አገር ናት።
የአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ የሆነችው እና በአረቡ ዓለም ተጽእኖ ያላት ግብፅ በ2023 ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ከአሜሪካ ስታገኝ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ድጋፍ ተበርክቶላታል። በሦስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ናይጄሪያ ደግሞ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ደርሷታል።
የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት የሚሰጡት ድጋፍ በልማት፣ በሰብአዊ እርዳታ፣ በሰላም እና ደኅንነት፣ በጤና፣ በዴሞክራሲ፣ በሰብአዊ መብት፣ በመልካም አስተዳር እና በሌሎችም መስኮች የሚደረጉ ድጋፎችን የሚሸፍኑ ናቸው።
የተጠናቀቀው 2024ን በተመለከተ የወጣው አሃዝ የተሟላ ሪፖርት ያካተተ ባይሆንም ኢትዮጵያ ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን የአሜሪካ መንግሥት እርዳታ እና ድጋፍን እንዳገኘች ያመለክታል።
ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ከፍተኛውን የውጭ እርዳታ በ2023 በማግኘት ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ስትሆን፣ እንደ ዋሽንግተን ፖስት ዘገባ በዓመቱ 420 ሚሊዮን ዶላር ለምግብ እርዳታ፣ ለጤና መርሃ ግብሮች 213 ሚሊዮን ዶላር ለልማት ድጋፍ ደግሞ 105 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች።
በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ናይጄሪያ ደግሞ 537 ሚሊዮን ዶላር ለጤና ፕሮግራሞች እና 56 ሚሊዮን ዶላር ለልማት የሚውል ድጋፍ ከአሜሪካ በኩል ተበርክቶላታል።
እነዚህ በተለያዩ ዘርፎች በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሌሎችም አገራት ከአሜሪካ መንግሥት ሲሰጡ የቆዩት ድጋፎች በትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ መሠረት እንቅፋት ገጥሟቸዋል። በተለይ በዩኤስኤይዲ በኩል የሚሰጡት እርዳታዎች እና ድጋፎች የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ ከሦስት ወራት በኋላ የሚታወቅ ይሆናል።
ዩኤስኤይድ የሚሠራው ምንድን ነው?
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤይድ) የአገሪቱ መንግሥት በዓለም ዙሪያ የሚያካሂደውን የሰብአዊ እርዳታ መረሃ ግብሮችን እንዲያስተዳድር በ1960ዎቹ ነበር የተቋቋመው።
ከ60 በላይ በሚሆኑ አገራት ውስጥ መቀመጫ ያለው እና በበርካታ አገራት የሚሠራው ተቋሙ ወደ 10 ሺህ የሚሆኑ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ ከመካከላቸውም ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ከአሜሪካ ውጪ የሚገኙ ናቸው። አብዛኛው ሥራ የሚከናወነው ኮንትራት በሚወስዱ እና የገንዘብ ድጋፍ በሚሰጣቸው ሌሎች ድርጅቶች ነው።
ድርጅቱ እርዳታ ከማቅረብ በተጨማሪ በተለያዩ መስኮች ላይ ይሠራል። በስፋት ከሚታወቅበት የረሃብ አደጋ ባጋጠማቸው አገራት የምግብ ድጋፍ ከማቅረብ ባሻገር መረጃዎችን በመተንተን የምግብ እጥረት ሊከሰትባቸው የሚችሉ ቦታዎችን በመተንበይ ረሃብን የመለየት በዓለም ዋነኛ የሆነ ሥርዓትን ለመዘርጋት ችሏል።
አብዛኛው የዩኤስኤይዲ በጀት የሚውለው ለጤና መርሃ ግብሮች ሲሆን፣ ይህም የፖሊዮ በሽታ አሁንም ድረስ ባለባቸው አገራት ውስጥ ክትባቶችን ማቅረብ እና ወረርሽኝ ሊያስከትሉ የሚችሉ ቫይረሶች ሥርጭትን ለመግታት የተለያዩ ሥራዎችን ያከናውናል።
ዩኤስኤይድ ምን ያህል ያስወጣዋል?
የአሜሪካ መንግሥት መረጃ እንደሚያመለክተው በአውሮፓውያኑ 2023 አገሪቱ ለዓለም አቀፍ እርዳታ 68 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች።
ይህ አጠቃላይ የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ ወጪ ለበርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ተቋማት የሚደለደል ሲሆን፣ የዩኤስኤይዲ በጀት ከተጠቀሰው ገንዘብ ከግማሽ በላዩን ማለትም ወደ 40 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነውን ይሸፍናል።
ከዚህ ውስጥም አብዛኛው ገንዘብ ወጪ የተደረገው በእስያ፣ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት እንዲሁም በዩክሬን በዋናነት ለሰብአዊ እርዳታ ሥራዎች ነው።
አሜሪካ በተወሰነ ደረጃ ሌሎቹን በመብለጥ የምድራችን በዓለም አቀፍ ልማት ላይ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ድጋፍ በማድረግ ትልቋ ናት።
ትራምፕ በዩኤስኤይድ ላይ ለውጥ ማድረግ ፈለጉ?
ትራምፕ አሜሪካ በዓለም ዙሪያ ለእርዳታ የምታውለውን ገንዘብ በተመለከተ ለረዥም ጊዜ ትችት ሲሰነዝሩ የቆዩ ሲሆን፣ ይህም ወጪ ለአሜሪካ ግብር ከፋዮች ተገቢውን ጥቅም አላስገኘም ይላሉ። በተለይ ዩኤስኤይድን ለይተው ጠንካራ ትችት የሰነዘሩ ሲሆን፣ የተቋሙን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን "አክራሪ ቀውሶች" በማለት ዘልፈዋቸዋል።
ትራምፕ ድርጅቱን መዝጋት የሕዝብ ድጋፍን የሚያስገኝላቸው ሳይሆን አይቀርም። የሕዝብ አስተያየት መለኪያዎች የአሜሪካ መራጮች የውጭ እርዳታ ወጪ መቀነስን እንደሚደግፉ ሲጠቁሙ ቆይተዋል። የቺካጎ ካውንስል ኦን ግሎባል አፌርስ እንደሚለው፣ ከአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ ወዲህ ያሉ የሕዝብ አስተያየቶች የእርዳታ ወጪ ቅነሳ ሰፊ ድጋፍ እንዳለው ያመለክታሉ።
ትራምፕ ወደ ሥልጣን እንደተመለሱ ከወሰዷቸው እርምጃዎች መካከል ምርመራ ተደርጎ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ዓለም አቀፍ ወጪዎች ለ90 ቀናት እንዲታገዱ የፈረሙት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ አንዱ ነው። ይህንንም ተከትሎ የዩኤስኤይድ እንቅስቃሴ እንዲቋረጥ የሚያዝ ማስታወሻ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አማካይነት መተላለፉ ይታወሳል።
በዚህ ውሳኔ መሠረት አብዛኞቹ የድርጅቱ ሥራዎች እንዲቆሙ በመታዘዙ ሊከተል የሚችለውን ጉዳት በማንሳት ጥያቄ በመቅረቡ የተወሰኑ ተግባራት ከዚህ ውሳኔ ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል። ለዚህም ዋነኛው የኤችአይቪ ኤድስ ህክምና ድጋፍ ፔፕፋር ሥራው እንዲቀጥል ተደርጓል።
ትራምፕ ዩኤስኤይድን መዝጋት ይችላሉ?
ውሳኔውን ተከትሎ በትራምፕ አስተዳደር ባለሥልጣናት እና በዩኤስኤይድ ኃላፊዎች መካከል ፍጥጫ ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ ኢላን መስክ በኤክስ ገጹ ላይ ይህንኑ ጉዳይ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በዝርዝር እንደተወያየበት እና "[ዩኤስኤይድን] እንድንዘጋው ከስምምነት ላይ ደርሰናል" ሲል ጽፏል።
የድርጅቱ ድረ ገጽ ከሰኞ ጀምሮ ከአገልግሎት ውጪ ተደርጎ ሠራተኞቹ ወደ ሥራ ቦታ እንዳይመጡ ተነግሯቸው ነበር። ከመጪው አርብ ጀምሮ ደግሞ ሁሉም ሠራተኞች የግዳጅ እረፍት እንዲወስዱ ታዘዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በዩኤስኤይድ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳላቸው ቢታወቅም፣ ድርጅቱን ለመዝጋት ያላቸው ሥልጣናቸው ግን ውስን ነው።
ድርጅቱ በአውሮፓውያኑ 1961 የተቋቋመው የአሜሪካ ምክር ቤት (ኮንግረስ) ለውጭ ድጋፍ በሚል ባወጣው ሕግ ነው። በዚህም ተቋሙ የአሜሪካ መንግሥት በሌሎች አገራት ውስጥ የሚያከናውናቸውን የእርዳታ ሥራዎች እንዲያስተዳድር እና እንዲቆጣጠር ሥልጣን ተስጥቶታል።
ከተመሠረተ ከአጭር ጊዜ በኋላም ደግሞ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ባወጡት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ አማካኝነት እንዲቋቋም ወሰኑ። በአውሮፓውያኑ 1998 ዩኤስኤይድ በራሱ የሚተዳደር ሥራ ፈጻሚ የመንግሥት አካል መሆኑን የሚያረጋግጥ ሌላ ሕግ ፀደቀ።
በዚህም ምክንያት ትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ በማስተላለፍ ብቻ የድርጅቱን ህልውና እንዲያበቃ ማድረግ አይችሉም። ይህንን ለማድረግ የሚሞክሩ ከሆነ በአገሪቱ ምክር ቤት እና በፍርድ ቤቶች ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል።
ዩኤስኤይድን ሙሉ ለሙሉ ለመዝጋት የትራምፕ ፓርቲ አባላት ጠባብ የበላይነት ያላቸው የአገሪቱ ምክር ቤቱ ሕግ ማውጣት ይጠበቅበታል።
ከዚያ ይልቅ ግን አሁን የትራምፕ አስተዳደር እያሰበበት ያለው ተቋሙን በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ስር በማድረግ በእራሱ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችለው ሥልጣኑን መግፈፍ እና ማዳከም ነው።
የዩኤስኤይድ መዘጋት ምን ዓይነት ተጽእኖ ይኖረዋል?
በዓለም ዙሪያ በሚካሄዱ ሰብአዊ እርዳታዎች ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የምታፈሰው አሜሪካ በዩኤስኤይድ ላይ የምታደርገው ማንኛውም ለውጥ ያለጥርጥር እርዳታው በሚደርሳቸው አገራት ውስጥ የራሱ የሆነ ተጽእኖ ይኖረዋል።
የእርዳታ ሥራውን የማቋረጥ ውሳኔ ይፋ ከተደረገ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ፣ የሚወጣው "እያንዳንዱ ዶላር ምክንያታዊ መሆን አለበት" በማለት ለዚህም ወጪው አሜሪካንን ደኅንነቷ የተጠበቀ፣ ጠንካራ እና የበለጠ የበለጸገች የሚያደርግ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕም በውጭ አገራት አሜሪካ የምታፈሰው ገንዘብ "ቅድሚያ ለአሜሪካ" ከሚለው አቋማቸው ጋር የሚጣጣም እንዲሆን እንደሚፈልጉ ግልጽ አድርገዋል።
የዲሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞች ይህንን ዩኤስኤይድን የማዳከም ብሎም የማፍረስ እርምጃን ሕገወጥ ከማለታቸው በተጨማሪ የአሜሪካንን ብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው በማለት ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።