የሊቨርፑሉ ሉዊስ ዲያዝ አጨቃጫቂ ጎል የተሻረበትን ሁኔታ የሚገልጸው ድምጽ ወጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሊቨርፑል ከቶተንሃም ጋር በነበረው ጨዋታ ሉዊስ ዲያዝ ያስቆጠረው ጎል የተሻረበትን ሁኔታ የሚገልጸው ድምጽ ይፋ ሆነ።
ሊቨርፑል በመጀመሪያው አጋማሽ በአጨቃጫቂ ሁኔታ የተሻረውን ጎል በሚመለከት ድምጹ እንዲሰጠው የፕሮፌሽናል ዳኞች ማኅበርን ጠይቆ ነበር።
የቪዲዮ ረዳት ዳኛው ዳረን ኢንግላንድ ዕይታውን “ትክክል” ቢሉም፣ ግቡ በስህተት ከጨዋታ ውጭ መባሉን ተከትሎ ሲበሳጩ ተደምጠዋል።
ማኅበሩ ስህተቱን “የትኩረት ማነስ እና ማጣት” ችግር መሆኑን አስታውቋል።
ፕሪሚየር ሊጉ አክሎም ስህተት የነበረው ውሳኔ “በቪዲዮ የተደገፈ ዳኝነት [ቫር] ሂደት ያጋጠመ ድክመት” ሲል ገልጾታል።
ዳኞቹ ምን ተባባሉ?
በቶተንሃም እና በሊቨርፑል መካከል የነበረው ጨዋታ ያለምንም ጎል እንደቀጠለ ነው። ከርቲስ ጆንስ በሠራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። 34ኛው ደቂቃ ላይ ዲያዝ ቀያዮቹን መሪ የምታድርግ ግብ አስቆጠረ።
ቫር፡ ዲያዝ ከጨዋታ ውጭ ሊሆን ይችላል።
ረዳት ዳኛ 1፡ ጓደኛዬ ከጨዋታ ውጭ ዕይታ፣
ቫር፡ ከጨዋታ ውጭ መሆኑ እየተጣራ ነው። ትንሽ ታገስ፣
የቫር ተቆጣጣሪዎቹ በዳርን ኢንግላንድ የሚመሩ ሲሆን፣ ምክትሉ ዳን ኩክ እና የመልሶ ዕይታ ባለሙያዎችን አካቷል። ኳሱ ከሞሐመድ ሳላህ እግር ሲወጣ እና ዲያዝ ኳሷን የተቀበለበትን ሁኔታ ማጥናት ያዙ።
ቫር፡ ኳሱ የሚሰጥበትን መነሻ አሳዩን።
ዳኛ፡ ምንም አታስብ ጓደኛዬ።
የመልሶ ዕይታ ባለሙያ፡ ይኼው።
ዳኛ፡ እሺ ቆዩኝ፣
የመልሶ ዕይታ ባለሙያ፡ ጠባብ የሆነ አቅጣጫ ነው ያገኘሁት፣
ቫር፡ ለዚህኛው የ2ዲ መስመር ስጠኝ እና ለሁለተኛው ምስልም አዘጋጅ፤
የመልሶ ዕይታ ባለሙያ፡ ሁለተኛው ምስል አለ?
ቫር፡ በጣም ጥሩ። ትክክል። 2ዲ መስመር ለግራ እግሩ እፈልጋለሁ፣
የመልሶ ዕይታ ባለሙያ፡ ሌሎች የዕይታ አቅጣጫዎችን ልቀይር፣
ቫር፡ ሮሜሮ ነው መሰለኝ?
የመልሶ ዕይታ ባለሙያ፡ ይህኛው አቅጣጫ የተሻለ መሰለኝ? በዚህኛው አቅጣጫ ደስተኛ ነህ?
ቫር፡ አዎ።
የመልሶ ዕይታ ባለሙያ፡ የ2ዲ መስመር እግሩ ላይ ሆኗል። ጥሩ።
ቫር፡ እና አቁመው።

በዚህ ወቅት የቫር ዳኛው ኢንግላንድ ለመሃል ዳኛው ዕይታው መጠናቀቁን ገለጹ። በዚህም ግቡ ከጨዋታ ውጭ መባሉ እና ጨዋታው በቶተንሃም የመልስ ምት እንዲጀመር መወሰኑ ትክክል መሆኑን አስታወቀ።
ቫር፡ ማጣራቱ ተጠናቋል! ማጣራቱ ተጠናቋል! ትክክል። ከጨዋታ ውጭ።
ዳኛ፡ አመሰግናለሁ ጓደኛዬ።
ቫር፡ አመሰግናለሁ።
ዳኛ፡ ድንቅ ነበር ጓደኞቼ። ምርጥ ሥራ ነው።
ዲያዝ ከጨዋታ ውጭ መሆኑን ጠቁመው ሁፐር ጨዋተው እንዲቀጥል ወሰኑ።
ሂደቱ ስህተት መሆኑን ማወቅ የቫር ቡድኑ ኃላፊነት ነበር።

ዲያዝ ከጨዋታ ውጭ በመባሉ ምክንያት የመልሶ ዕይታ ባለሙያው ለኢንግላንድ አሳውቆ ሂደቱን ለማጤን ነበር። የቫር ምክትል ዳኛው ኩክ ውሳኔው ስህተት መሆኑን አረጋገጡ።
የመልሶ ዕይታ ባለሙያ፡ ቆይ፣ ቆይ፣ ቆይ። በሜዳ ላይ ከጨዋታ ውጭ ተብሏል። በዚህ ደስተኛ ነህ?
የቫር ምክትል፡ አዎ።
የመልሶ ዕይታ ባለሙያ፡ በዚህ ደስተኛ ነህ?
የቫር ምክትል፡ ከጨዋታ ውጭ ጎል። ስህተት ነው።
ቫር፡ ምን?
የመልሶ ዕይታ ባለሙያ፡ በሜዳ ላይ ከጨዋታ ውጭ ተብሏል። በዚህ ምስል ደስተኛ ነህ? አዎ ከጨዋታ ውጭ አይደለም። የሰጠናቸው ምስል ከጨዋታ ውጭ አይደለም።
የመልሶ ዕይታ ባለሙያ፡ ከጨዋታ ውጭ ሆኗል።
ቫር፡ ወይኔ. . .

ኢንግላንድ ስህተት መሥራታቸውን ባወቁበት ጊዜ ሊቨርፑል በአንዲ ሮበርትሰን እና በዲያዝ እያጠቃ ነበር።
ክርስቲያን ሮሜሩ ኳሷን አቋርጦ የመልስ ውርወራ ለሊቨርፑል ተሰጠ።
የቫር ማዕከል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት እና ከቫር ቡድኑ ተለይተው ሌላ ክፍል ውስጥ የነበሩት ኦሊ ኮሁት ውሳኔው እንዲስተካከል ጨዋታው እንዲዘገይ ሃሳብ አቀረቡ።
የመልሶ ዕይታ ባለሙያ፡ ይዘግይ፣ ይዘግይ። ኦሊ እንዲዘገይ እየጠየቀ ነው። ኦሊ እንዲዘገይ እየጠየቀ ነው።
ቫር፡ ይቅርታ. . .
የመልሶ ዕይታ ባለሙያ፡ ኦሊ ጨዋታው እንዲዘገይ እየጠየቀ ነው። ውሳኔው ከጨዋታ ውጭ አልነበረም።
ቫር፡ ምንም ማድረግ አይቻልም
የመልሶ ዕይታ ባለሙያ፡ ኦሊ እንዲዘገይ እየጠየቀ ነው። ኦሊ እንዲዘገይ እየጠየቀ ነው።
ቫር፡ ኦሊ?
አራተኛ ዳኛ፡ አቤት. . .
የመልሶ ዕይታ ባለሙያ፡ ጨዋታውን አዘግዩት። ለማዘግየት ጨዋታውን አቋርጡት።
ቫር፡ ጨዋታው በድጋሚ ተጀምሯል። ምንም ማድረግ አይቻልም። ምንም ማድረግ አይቻልም።
ረዳት ዳኛ፡ አዎ ጀምረውታል።
ቫር፡ ምንም ማድረግ አይቻልም።
ረዳት ቫር፡ ምንም. . .
ቫር፡ ምንም ማድረግ አይቻልም። ምንም ማድረግ አይቻልም።
ጨዋታው በመልስ ውርወራ ሲቀጥል ከሁለት ደቂቃ በኋላ ሰን ሁንግ ሚን ስፐርስን ቀዳሚ አደረገ።
ኮዲ ጋክፖ በመጀመሪያው አጋማሽ ሊቨርፑልን አቻ ማድረግ ቻለ። ቀያዮቹ ዲያጎ ጆታን በቀይ ከማጣት ባለፈ፣ ጆዬል ማቲፕ ራሱ ላይ ባስቆጠረው ጎል ለመሸነፍ ተገደዋል።

ድምጹ ለምን ይፋ ተደረገ?
የቅዳሜውን ጨዋታ ተከትሎ ሊቨርፑል “ስፖርታዊ ታማኝነት ተጎድቷል” ሲል መግለጫ አወጣ።
“የመሻሻል እና የመፍትሄ ፍላጎትን ከግምት ውስጥ በማስገባት ያሉትን አማራጮች እንመረምራለንም” ብሏል።
የዳኞች ማኅበር በበኩሉ ግቡ እንዳይጸድቅ የተደረገውን ውሳኔ “ትልቅ የሰው ስህተት” ነው ብሏል።
ሊቨርፑል ጆንስ የተሰጠውን ቀይ ካርድ አስመልክቶም ይግባኝ ጠይቆ ነበር። ከቫር ዕይታ በኋላ በተሰጠው ቀይ ካርድ ምክንያት ተጫዋቹ ሦስት ጨዋታዎች ያመልጡታል።
ይህ በቫር ላይ ለውጥ ያስከትላል?
ማኅበሩ የቅዳሜው ጨዋታ ተጠናቆ ብዙም ሳይቆይ ነው ስህተቱን አምኖ ደረጃዎቹ “ከሚጠበቁት በታች ወድቀዋል” ያለው።
ለሊቨርፑል እና ለሌሎቹ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ያጋራውን “ቁልፍ ትምህርቶች እና አፋጣኝ እርምጃዎች” ጨምሮ ዝርዝር ዘገባ አክሎ አውጥቷል።
“ወደፊት ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ይቀንሳል” ያላቸው “ቁልፍ ትምህርቶች” የሚከተሉት ናቸው፡
ለቪዲዮ ዳኞች የሚሰጠውን መመሪያ ውጤታማነት አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሰጥቷል።
በሜዳ ላይ ከሚደረጉ ውሳኔዎች ጋር በተያያዘ በዳኛው እና በቫር ቡድን መካከል ያለውን ግንኙነት ግልጽ ለማሳደግ አዲስ የቫር ኮሙኒኬሽን ፕሮቶኮል ይዘጋጃል።
ቫር የመጨረሻውን ውሳኔ በሜዳ ላይ ላሉ ዳኞች ከማሳወቁ በፊት ውጤቱን ከቫር ተቆጣጣሪዎች ጋር ያረጋግጣል።
ፕሪሚየር ሊጉ የማኅበሩን ምክረ ሃሳቦች መቀበሉን ገልጿል። ከዳኞች ጋር “ወጥ የሆነ ከፍተኛ የቫር አፈጻጸም ደረጃዎችን ለማውጣት” አጠቃላይ ግምገማ ለማካሄድ ማቀዱንም ገልጿል።
ይህ ክስተት በ2019-20 የውድድር ዘመን መጀመሪያ ላይ ከፕሪምየር ሊግ ጋር በተዋወቀው በቫር ውጤታማነት እና በጨዋታ ወቅት ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ላይ ስላሳደረው ተጽዕኖ የበለጠ ጥያቄ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።
ቫር በርካታ ጠንካራ ጎኖች እንዳሉት በማንሳት ድጋፋቸውን የሰጡ አሉ።
በሌሎች ሊጎች የሚደረጉ ጨዋታዎችን ለመምራት ወደ ውጭ አገር እንዲሄዱ የሚፈቀድላቸው የፕሪሚየር ሊግ ዳኞችም ይገመገማሉ ተብሏል።
በቅዳሜው ጨዋታ አራተኛ ዳኛ የነበሩት ኩክ፣ ኢንግላንድ እና ማይክል ኦሊቨር በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ሐሙስ ዕለት የተደረገን የሊግ ጨዋታ በበላይነት የመራው የዳኞች ቡድን አካል ነበሩ።












