160 ሺህ ገደማ የሆሊውድ የፊልም ባለሙያዎች አድማ መቱ

የሆሊውድ የፊልም ባለሙያዎች አድማው ላይ የነበሩትን ፀሐፊያን በመቀላቀል በኢንዱስትሪው ታሪክ ከፍተኛውን አድማ መቱ።

ሳግ ወይም ያም ስክሪን አክተርስ ጊልድ የተሰኘው ማሕበር ፊልም የሚያሰራጩ ድርጅቶች የተሻለ ይክፈሉን ሲል ነው አድማ የጠራው።

አድማው በሎስ አንጀለስ ሰዓት አቆጣጠር ትናንት እኩለ ሌሊት ጀምሯል።

ይህ ማለት በርካታ የፊልምና የቴሌቪዥን ድራማዎች ቀረፃ አሊያም አርትዖት ያቆማሉ ማለት ነው።

በቅርቡ ለዕይታ የሚበቃው ኦፕንሃይመር የተሰኘ ግዙፍ ፊልም ተዋንያንም ፊልሙን ለንደን እያስተዋወቁ ሳለ አድማው በመመታቱ ሥራቸውን በአጭሩ ቀጭተዋል።

160 ሺህ ገደማ የሆሊውድ የፊልም ባለሙያዎች ጥያቄያችን መልስ እስኪያገኝ ፍንክች አንልም ብለዋል።

ባለሙያዎቹ ካሊፎርኒያ በሚገኘው የኔትፍሊክስ ዋና ቢሮ ፊት ተሰባስበው ድምፃቸውን ለማሰማት ቆርጠዋል።

ቀጥሎ ደግሞ ፓራማውንት፣ ዋርነር ብሮስ እና ዲዝኒ ወደተሰኙት ፊልም የሚያሰራጩ ድርጅቶች ይሄዳሉ።

ስክሪን አክተርስ ጊልድ የተሰኘው ድርጅትና የአሜሪካ ቲቪና ራድዮ አቅራቢዎች ፌዴሬሽን በጋራ አንድ ሌላ ጥያቄ ይዘዋል።

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ [ሰው ሰራሽ አስተውሎት] ያቀናበራቸው ድምፆች ተዋንያንን እንዲተኩ አይፈልጉም።

ግዙፎቹን የፊልም ስቱዲዮዎችን የሚወክለው ድርጅት ግን ተቃውሞውን አጣጥሎታል።

“ማሕበራቱ በዚህ ኢንዱስትሪ ላይ ጥገኛ የሆኑ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሰዎችን ኪስ የሚጎዳ ውሳኔ ነው የወሰኑት” ብሏል።

ወደ ኤአይ ስንመጣ የፊልም ስቱዲዮዎች ማሕበሩ፤ የተዋንያን ፈቃድ ሳይጠይቅ ምንም ዓይነት ምስልም ሆነ ድምፅ አስመስዬ እንደማልሠራ ቃል ገብቻለሁ ይላል።

ሌላኛው የተዋንያን ማሕበር ጥያቄ ደግሞ ተዋንያን አንድ ፊልም አሊያም የቴሌቪዥን ድራማ በሚታይበት መጠን ሊከፈለን ይገባል ነው።

ይህ ማለት አንድ ሥራ ሠርተው አንድ ጊዜ ከሚከፈላቸው ይልቅ ከታየውንና ካስገባው ገቢ ደርሻ ኖሯቸው እንዲከፈላቸው ይፈልጋሉ ማለት ነው።

አድማ የመቱት ረብጣ ዶላር የሚከፈላቸው ብቻ ሳይሆኑ በተነፃፃሪ አነስተኛ ገንዘብ የሚያገኙ ተዋንያን ጭምር ናቸው።

ራይተርስ ጊልድ ኦፍ አሜሪካ የተሰኘው የፊልም ፀሐፊያን ማሕበር ካለፈው ግንቦት ጀምሮ አድማ ላይ ነው።

ይህ ማሕበር 11 ሺህ 500 አካባቢ አባላት አሉት።

ተዋናያንና እና ፀሐፊያን በጋራ አድማ ሲመቱ ከ1960 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር።

በወቅቱ አድማውን የመሩት ሮናልድ ሬገን ሲሆኑ ይህ ትወና ትተው ወደ ፖለቲካ ገብተው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ከመሆናቸው በፊት የሆነ ነው።

ለመጨረሻ ጊዜ ተዋንያን ብቻቸውን አድማ የመቱት ደግሞ በፈረንጆቹ 1980 ነበር።

ዳይሬክተርስ ጊልድ ኦፍ አሜሪካ የተሰኘው የዳይሬክተሮች ማሕበር ባለፈው ሰኔ የተሳካ ድርድር በማድረጉ በአመፁ አይሳተፍም።

ይህ አድማ ማለት ሆሊውድ ሙሉ በሙሉ ፀጥ አለ፤ ሂደት ላይ የነበሩ ሥራዎች ይቆማሉ ማለት ነው።

ታዋቂ የሆሊውድ ፈርጦች አዲስ የሠሩትን ሥራ ማስተዋወቅም አይችሉም።

ኤሚ አዋርድስ የመሳሰሉ ሽልማቶች አይካሄዱም። ዓለም አቀፍ የሽልማት ሥነ-ሥርዓቶች ቢካሄዱም የሆሊውድ ተዋንያን አይሳተፉም።