'በፊቴ ምክንያት ካፌ ውስጥ አናስተናግድህም ተብዬ አውቃለሁ'

በልጅነቱ ከደረሰበት አሰቃቂ ሹፈት በተጨማሪ አሚት ጎስ አሁንም የሚያፈጡበት፣ ጣታቸውን የሚጠቁሙበት እና አስተያየቶችን የሚሰጡበት ብዙ ናቸው።
በፊቱ ገጽታ ምክንያት ካፌ ውስጥ አገልግሎት አንሰጥህምም ተብሏል።
የ35 ዓመቱ የበርሚንግሃም ወጣት በቅርቡ ለንደን ወደሚገኝ ካፌ ሲያመራ "ሁሉም ሰው እያየኝ ነበር። እናም ይህንን 'መንፈስ' ተመልከቱ የሚሉ ይመስላል" ሲል ገልጿል።
"የምታስተናግደኝ አየችኝና 'ኦ! ማስተናገድ አቁመናል' አለችኝ።"
"ዞራ ሄደች። ግን ሌሎችን እያስተናገዱ ነበር።"
አሚት የተወለደው ዓይነት ኒውሮፊብሮማቶሲስ (Neurofibromatosis type 1) ጋር ነው። ይህም የፊት ቅርጽን የሚለውጥ በሽታ ካንሰር አምጪ ያልሆኑ ዕጢዎች በነርቭ ላይ እንዲያድጉ ያደርጋል።
"የተሰጠውን መቀበልን" ከተማረ በኋላ አሁን ተማሪዎች "የራሳቸውን ሰብዕና እንዲቀበሉ እና ማንነታቸውን እንዲያከብሩ" ለመርዳት ታሪኩን በትምህርት ቤቶች ውስጥ አካፍሏል።

የፎቶው ባለመብት, Amit Ghose
በቅርብ የደረሰበት መጥፎ ገጠመኝ 'ቦርን ዲፍረንት' የተሰኘ የሕጻናትን መጽሐፍ እንዲሳያትም አነሳስቶታል።
"ፓርክ ውስጥ ሆኜ ሁለት ሰዎች ወደ እኔ መጥተው ፊቴ ላይ ምን እንደተፈጠረ ጠየቁኝ። የማወቅ ጉጉት ያላቸው መስሎኝ ነበር።"
"'አምላኬ ሆይ እንዳንተ ያለ ፊት ቢኖረኝ ከቤቴ እንኳን አልወጣም ነበር' እያሉ መሳቅ ጀመሩ።"
በአጋጣሚው "በእርግጥም ተበሳጨሁ" ካለ በኋላ "ስለራሴ አሰብኩ። በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ። ይህን መጽሐፍ ማሳተም አለብኝ። ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው" አለ።
"እንዲህ ያለ መጽሐፍ በልጅነቴ ባገኝ ኖሮ ይጠቅመኝ ነበር ብዬ አስባለሁ።"

የፎቶው ባለመብት, Amit Ghose
አሚት በ11 ዓመቱ የግራ ዓይኑን በቀዶ ሕክምና ተወገደ። ፊቱ የበለጠ ተቀየረ፤ ተጨማሪ እንግልት እና ሹፈት ተከተለው።
በአንድ በገና ሰሞን በሚከበር የሃሎዊን በዓል ወቅት አንድ ተማሪ በዓሉ ላይ ለመሳተፍ "የሃሎዊን ጭንብል አያስፈልግህም። ለዕድሜ ዘመን የሚበቃ አለህ" ሲል ተሳልቆበታል።
"አጋጣሚው ግራ ፊቴን እስከማልቀበልበት ደረጃ ድረስ ሰበረኝ" ብሏል።
"ለረጅም ጊዜ ፊቱን ደብቄ ነበር። ፊቴን ለዓለም ማሳየት ምቾት አይሰጠኝም ነበር።"
ወደ ኋላ መለስ ብሎ ሲመለከተው ያጋጠመውን የመንፈስ የጭንቀትና የድባቴ ጥልቀት እንደማይረዳው ተናግሯል።
"ሌሎች ልጆች አጠገቤ መጥተው መቀመጥ አለመፈለጋቸው ወይም ከወላጆቻቸው ጀርባ መደበቅ መፈለጋቸው በአእምሮዬ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል" ሲል ይናገራል።
በትምህርት ቤት ክሪኬት ስለሚወድ በመጫወት ነበር በመጨረሻም ጓደኞች ያፈራው።
"ክሪኬት አሚት እንድሆን ረድቶኛል። አስቂኝ ፊት ካለው አሚት ያ ክሪኬት የሚጫወተው ልጅ ወደሚል ቀይሮኛል" ሲል ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Amit Ghose
ካደገም በኋላ ቢሆንም "ሳያቋርጡ የሚያፈጡበት" መኖራቸውን ተናግሯል።
"በጣታቸው መጠቆም እና ከጎናቸው ያለውን ጓደኛ መታ መታ በማድረግ 'የዚያን ሰው ፊት አይተሃዋል' እያሉ መጠቆማቸው ቀጥሏል።"
"ደግነትም ግን አለ። ይህንን ማጉላት ያስፈልጋል።"
'ተቀበላቸሁ አልተቀበላችሁም እኔ ይኼው ነኝ'
ራስን "የመቀበል ጥበብ" ያስተማረችው ሚስቱ ፒያሊ እንደሆነች ገልጿል።
"በእውነቱ እኔ ራሴን መቀበል ያለብኝ ሌሎች ሳይቀበሉኝ ነው" ሲል አክሏል።
ታሪኩን በማኅበራዊ ሚዲያ ማካፈል እንዲጀምርም አሳመነችው።
"ቲክቶክ ስለ ዘፈን እና ዳንስ ብቻ ነው ብዬ አስቤ ነበር። እሷ ግን አሳመነችኝ።"
"ቪዲዮ ቀርጽኩ እና እንዲህ አልኩ 'ሁላችሁንም ለመርዳት እና ለመደገፍ እና የሕይወት ልምዶቼን ተጠቅማችሁ እንድተነሳሱ ላግዛችሁ እፈልጋለሁ።"
ቲክቶክን በ2023 መጀመሪያ ላይ ተቀላቀለ። ከዚያ ወዲህ ወደ 200 ሺህ የሚጠጉ ተከታዮችን እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ 'ላይኮች' ማግኘት ችሏል።
"ታሪኬን በማካፈል ሰዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መርዳቴ ራሴን የበለጠ እንድቀበል ረድቶኛል።"
"ለዓለም አሁን 'ተቀበላችሁ አልተቀበላችሁም እኔ ይኼ ነኝ'።"

የፎቶው ባለመብት, Amit Ghose












