ማንቸስተር ሲቲ ከአርሰናል: ማን ሦስት ነጥቡን ይወስዳል? በሌሎቹ ጨዋታዎች እነማን ያሸንፋሉ?

በአምስተኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚር ሊግ መርሃ ግብር ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው አርሰናልን የሚያስተናግደበት ጨዋታ ይጠበቃል።

ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ዓመት ባከናወኑት ግጥሚያ ጨዋታው ያለምንም ግብ መጠናቀቁ ይታወሳል። መከላከልን መሠረት በማድረግ የተጫወተው አርሰናል ተመሳሳይ አጨዋወትን በድጋሚ ይመርጥ ይሆን?

የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን “ይህም ያለምንም ግብ የሚጠናቀቅ ጨዋታ እንደሚሆን አስባለሁ። ሆኖም ትልልቅ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ይጠናቀቃሉ ማለት አልፈልግም” ብሏል።

ለመሆኑ ይህንን ተጠባቂ ጨዋታ ጨምሮ ሌሎቹ መርሃ ግብሮች ምን ዓይነት መልክ ይዘው ይጠናቀቃሉ?

ቅዳሜ

ዌስት ሃም ከ ቼልሲ

ዌስት ሃም አሠልጣኝ ዴቪድ ሞዬስን ለማሰናበት የወሰነው ‘በዌስት ሃም መንገድ’ የሚጫወት አሠልጣኝ ለማስፈረም በሚል ነበር።

አሠልጣኝ ዩለን ሎፕቴጉ ከመቅጠራቸው በተጨማሪ በ130 ሚሊዮን ፓውንድ ተጫዋቾችን ቢያስፈርሙም ከሞዬስ የተሻለ ውጤት ስለማስመዝገባቸው ግን በሂደት የሚታይ ይሆናል።

ዌስት ሃም ጥሩ ካለመንቀሳቀሱም በላይ ቼልሲም አሳማኝ የሚባል አለመሆኑ ለመገመት የሚያስቸግር ጨዋታ ሆኗል።

የሚያሸንፈውን ቡድን ለመለየት አስቸጋሪ ይሆናል።

ግምት፡ 1 – 1

ውጤት፡ 0 - 3

አስተን ቪላ ከ ዎልቭስ

ዎልቭስ ከዚህ ጨዋታ ምንም ነጥብ ማግኘት ባይችልም ዘንድሮ ጥሩ ውጤት ያስመዘግባል።

የቪላው አሠልጣኝ ኡናይ ኤምሪ በሻምፒዮንስ ሊግ እና በፕሪሚየር ሊጉ በሚኖረው ፉክክር፤ የቡድናቸውን ሚዛን መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

ባለፈው ሳምንት ኤቨርተን ላይ የማሸነፊያዋን ግብ ያስቆጠረው ጆን ዱራን ቡድኑ ያለውን የተጫዋቾች ጥልቀት ማሳየት ችሏል።

በሻምፒዮንስ ሊግ ያንግ ቦይስን ካሸነፉ በኋላ በዚህ ጨዋታም ሦስቱን ነጥብ ያሳካሉ።

ግምት፡ 2 – 0

ውጤት፡ 3 - 1

ፉልሃም ከ ኒውካስል

ባለፈው የውድድር ዓመት ፉልሃም በሜዳው ካደረጋቸው 19 ጨዋታዎች ዘጠኝ ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ በስምንቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ኒውካስል ደግሞ ተገማች ያልሆነ ቡድን ሆኗል።

ቡድኑ እስካሁን እንደቡድን ነጥቦችን ከማግኘት ይልቅ በግል ጥረት ላይ ተንጠልጥሏል።

ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ይመስላል።

ግምት፡ 1 – 1

ውጤት፡ 3 - 1

ሌስተር ከ ኤቨርተን

ባለፈው ሳምንት ሁለቱም ቡድኖች 2 ለምንም መምራት ቢችሉም ሌስተር ከፓላስ ጋር አቻ ሲለያይ ኤቨርተን ደግሞ በቪላ ተሸንፏል።

በዚህ ጨዋታ የአሠልጣኝ ሾን ዳይሽ ቡድን ሦስቱን ነጥብ የሚያሳካበት ሳምንት ይመስላል።

አንዳንድ ደጋፊዎች አሠልጣኙ ላይ ያላቸው እምነት እየተሸረሸረ ነው።

በደረጃ ሰንጠረዥ ላይ በታችኛው ክፍል በሚገኝ ቡድን መሸነፍ ደግሞ ጫናውን ያበረታዋል።

ግምት፡ 1 – 2

ውጤት፡ 1 - 1

ሊቨርፑል ከ ቦርንመዝ

ከኖቲንግሃም ፎረስት ሽንፈት በኋላ ሊቨርፑሎች ኤሲሚላንን በማሸነፍ ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል።

ሞሐመድ ሳላህን ጨምሮ አንዳንድ ተጫዋቾቻው ከፎረስት ጋር ጥሩ ጊዜን አላሳለፉም።

ይህ ጨዋታ ለሊቨርፑል ቀላል ባይሆንም ከፎረስት ጋር እንደነበራቸው ግጥሚያ ተቀዛቅዘው አይቀርቡም።

ዕድሎችን ፈጥረው ይጠቀሙባቸዋል።

ግምት፡ 2 – 0

ውጤት፡ 3 - 0

ሳውዝሃምፐተን ከ ኢፕስዊች

ሁለቱም ቡድኖች በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያውን ድል ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ኢስዊች እስካሁን ሁለት ነጥቦችን ማሳካት ችሏል።

ቡድኖቹ ባለፈው ዓመት በሻምፒዮንሺፑ ሲወዳደሩ ኢፕስዊች በሜዳው እና ከሜዳው ውጭ አሸንፎ ስድስት ነጥቦችን አሳክቷል።

ሁለቱም ቡድኖች ለሦስት ነጥቡ ቢጫወቱም ጨዋታው አቻ ይጠናቀቃል።

ግምት፡ 1 – 1

ውጤት፡ 1 - 1

ቶተንሃም ከ ብሬንትፎርድ

ይህ ለቶተንሃም አስቸጋሪ የሚሆን መርሃ ግብር ነው።

ብሬንትፎርዶች ጠንካራ አደረጃጀት እንዳላቸው ባሳዩበት የማንቸስተር ሲቲ ጨዋታ ዮአን ዊሳ በጉዳት ከሜዳ ወጥቷል።

ቶተንሃም እንደባለፈው ዓመት በተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ውስጥ ውጤታማ አለመሆኑ በስጋት ይነሳል።

በዚህ ጨዋታ ተጠናክረው መቅረብ የሚኖርባቸው ሲሆን፣ በሜዳቸው ስለሚጫወቱም የአሸናፊነት ግምት ያሰጣቸዋል።

ግምት፡ 2 – 1

ውጤት፡ 3 - 1

ክሪስታል ፓላስ ከ ማንቸስተር ዩናይትድ

ባለፈው ዓመት ፓላሶች በሜዳቸው ማንቸስተር ዩናይትድን 4 ለምንም ቢያሽንፉም ሁለት ግብ ያስቆጠረላቸውን ማይክል ኦሊሴን ሸጠውታል።

አሠልጣኝ ኦሊቨር ግላስነር ወደ ቡድኑ ሲመጡ ጥሩ ውጤት ቢያስመዘግቡም ዘንድሮ ግን ጉዞው አልጋ በአልጋ አልሆነላቸውም።

በማጥቃት ላይ የተመሠረተው አጨዋወታቸው ደግሞ ለማንቸስተር ዩናይትድ የተመቸ መሆኑን ቀያዮቹ ሰይጣኖች ባለፈው ሳምንት ከሳውዝ ሃምፕተን ጋር በነበራቸው ጨዋታ አሳይተዋል።

በጨዋታው አንድሬ ኦናና ፍጹም ቅጣት ምት ካዳነ በኋላ ቡድኑ የተሻለ ከመሆኑም በላይ አጥቂው ማርከስ ራሽፎርድም ጥሩ መንቀሳቀስ ችሏል።

ከጨዋታው ዩናይትድ ሦስት ነጥብ ያሳካል። የቴን ሃግ ጉዳይ አስተማማኝ ባይሆንም ቡድኑ በትክክለኛ መንገድ ላይ ይመስላል።

ግምት፡ 1 – 2

ውጤት፡ 0 - 0

እሑድ

ብራይተን ከ ኖቲንግሃም ፎረስት

ፎረስት ካለው የተከላካይ መስመር እና ባለፈው ሳምንት ሊቨርፑልን ከማሸነፉ አንጻር ይሸነፋል ብሎ መገመት የስቸግራል።

የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾቹ ከሚያሳዩት ብቃት በተጨማሪ ተቀያሪ ተጫዋቾቹ ተጽዕኖ መፍጠር እንደሚችሉ አሳይተዋል።

ብራይተን ግብ ማስቆጠር የሚችል ቡድን ነው።

ቡድኑ በሜዳው እንደማይሸነፍ ከገመትን ደግሞ ጨዋታው በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል ብለን እናስባለን።

ግምት፡ 1 – 1

ማንቸስተር ሲቲ ከ አርሰናል

አርሰናል ባለፈው ዓመት ማንቸስተር ሲቲ ግብ እንዳያስቆጥርባቸው ያሳዩት ብቃት ቢያስወድሳቸውም በሁለት ነጥብ ልዩነት ሊጉን ዋንጫ አጥተዋል።

በጨዋታው ያሳዩት መከላከል ዋንጫውን አሳጣቸው በሚልም የሚተቿቸው አልጠፉም።

በሻምፒዮን ሲጉ ኢንተር ሚላን እንዴት ማንቸስተር ሲቲን በመቋቋም መጫወት እንደሚቻል አሳይቷል።

አርሰናል ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ገንብቷል። በመልሶ ማጥቃት ሲቲን መፈተን እንደሚቻል ከኢንተር መማር ይቻላል።

በኢንተሩ ጨዋታ ኤርሊንግ ሃላንድ ጥሩ ካለመጫወቱም በላይ ጉዳት ያጋጠመው ኬቪን ደብሩይን በዚህ መርሃ ግብር ላይ ላይሰለፍ ይችላል።

ሲቲ ከግብ አልባው የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ በኋላ ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

ግምት፡ 2 – 1