የቻይናው ፕሬዚዳንት አሜሪካ ለታይዋን የጦር መሣሪያ ስታቀርብ 'ጥንቃቄ ማድረግ አለባት' ሲሉ ትራምፕን አሳሰቡ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለታይዋን የጦር መሳሪያ ሲያቀርቡ "ጥንቃቄ የተሞላበት" እንዲሆን ማሳሰባቸውን የአገሪቱ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ረቡዕ ዕለት ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በስልክ ውይይት ያደረጉት ፕሬዚደንት ዢ ደሴቷን "በቻይና እና በአሜሪካ ግንኙነት ውስጥ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ" ሲሉ ጠርተዋታል።

በተጨማሪም ከዋሽንግተን ጋር ላላቸው ግንኙነት "ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡ" እና ሁለቱም ወገኖች ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት መንገዶችን እንደሚፈልጉ ተስፋ እንደሚያደርጉ መናገራቸው ተዘግቧል።

ትራምፕም የስልክ ውይይቱን "እጅግ በጣም ጥሩ" እና "ረጅም እና ጥልቅ" ሲሉ ገልጸውታል።

የረቡዕ የስልክ ውይይት የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመርን ጨምሮ የበርካታ አገራት መሪዎች በዓለም ሁለተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላት ቻይና ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማደስ ተስፋ በማድረግ ወደ አገሪቱ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ የመጣ ነው።

ትራምፕ በሚያዝያ ወር ቻይናን ለመጎብኘት ያቀዱ ሲሆን ይህንንም ጉዞ "በጣም በጉጉት እጠብቃለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም ቤጂንግ አሁን ካለው 12 ሚሊዮን ቶን በላይ እስከ 20 ሚሊዮን ቶን የአሜሪካን አኩሪ አተር ለመግዛት እያሰበች መሆኑን አስታውቀዋል።

"ከቻይና ጋር ያለን ግንኙነት እና እኔ ከፕሬዝዳንት ዢ ጋር ያለኝ የግል ግንኙነት እጅግ በጣም ጥሩ ነው፤ እናም ሁለታችንም በዚህ መንገድ መቀጠል ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንገነዘባለን" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ድረገጽ ልጥፋቸው ላይ ጽፈዋል።

ሁለቱ መሪዎች ባለፈው ኅዳር ወር በስልክ ስለ ንግድ፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ስለፈጸመችው ወረራ፣ ፌንታኒል እና ታይዋንን በተመለከተ መነጋገራቸውን የትራምፕ እና የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች ይፋ አድርገው ነበር።

ትራምፕ እና ዢ ረቡዕ ዕለት ባደረጉት የስልክ ውይይት ከታይዋን እና ከአኩሪ አተር ግዢ በተጨማሪ ሩሲያ በዩክሬን ስለምታካሂደው ጦርነት፣ በኢራን ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ እና ቻይና ከአሜሪካ ስለምትገዛው ነዳጅ እና ጋዝ በተመለከተ መወያየታቸውን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጽፈዋል።

ዢ በበኩላቸው ታይዋንን በተመለከተ "ራሷን የምታስተዳድረው ደሴት የቻይና ግዛት ናት" ሲሉ ቤጂንግ "የታይዋንን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መጠበቅ አለባት" ብለዋል።

"ዩናይትድ ስቴትስ ለታይዋን የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ጉዳይን በጥንቃቄ መያዝ አለባት" ሲሉ ማሳሰባቸውን ዢንዋ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ቻይና ከታይዋን ጋር "እንደገና ለመዋሃድ" ለረጅም ጊዜ ስትገልጽ የነበረች ሲሆን ይህንን ለማድረግም ኃይል የመጠቀም አማራጭን ውድቅ አላደረገችም።

አሜሪካ ከታይዋን ይልቅ ከቤጂንግ ጋር መደበኛ ግንኙነት እንዲሁም ለአስርተ ዓመታት የዘለቀ ጥብቅ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አላት።

ነገር ግን አሜሪካ የታይዋን ጠንካራ አጋር ስትሆን የደሴቲቱ ትልቁ የጦር መሳሪያ አቅራቢም ነች።

በታኅሳስ ወር የትራምፕ አስተዳደር ለታይዋን ወደ 11 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ግዙፍ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማካሄዱን አስታውቋል።

ይህም የተራቀቁ የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን፣ ራሳቸው የሚንቀሳቀሱ ሃዊትዘር እና የተለያዩ ሚሳኤሎችን ያካተተ ነው።

ቤጂንግ በወቅቱ "የታይዋንን ነፃነት ለመደገፍ የተደረገው ይህ ሙከራ"፤ "በታይዋን የባሕር ሰርጥ ላይ ያለውን ሁኔታ ወደ አደገኛ ግጭት ይገፋል" ብላ ነበር።

"ዩናይትድ ስቴትስ የራሷ ስጋት እንዳላት ሁሉ ቻይናም በበኩሏ ስጋቶች አሏት" ሲሉ ዢ ረቡዕ ዕለት ለትራምፕ ተናግረዋል።

"ሁለቱ ወገኖች በእኩልነት፣ በመከባበር እና በጋራ ጥቅም መንፈስ በተመሳሳይ መንገድ ቢሰሩ፣ የእርስ በርስ ስጋቶችን ለመፍታት መንገዶችን በእርግጠኝነት መፈለግ እንችላለን" ብለዋል።

ዢ ከትራምፕ ጋር ከመገናኘታቸው ከጥቂት ሰዓታት በፊት ከሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ጋር በቪዲዮ የተወያዩ ሲሆን የቤጂንግ እና የሞስኮ ግንኙነት መጠናከሩን በማንሳት አድንቀዋል።