ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፖላንድ ድንበር ላይ ብቻዋን ወልዳለች የተባለች ኤርትራዊትን ከድንበር አለመለስኩም አለች
አንዲት ኤርትራዊት ስደተኛ ፖላንድ እና ቤላሩስ ድንበር ላይ ብቻዋን ሆና ወልዳለች ከተባለ በኋላ ፖላንድ ስደተኛዋን ከድንበር አልመስኩም አለች።
አክቲቪስቶች ኤርትራዊቷ ስደተኛ ወደ ፖላንድ ለመግባት ጥረት ስታደርግ በፖላንድ መንግሥት ከድንበር ላይ “ተገፍታ ተመልሳለች” ይላሉ።
ክስተቱን ተከትሎ ስደተኛዋ ነብሰ ጡር ፖላንድ እና ቤላሩስ ድንበር ላይ ብቻዋን ሆና ልጇን ተገላግላለች።
የፖላንድ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ግን ድንበር ጠባቂዎች ነብሰ ጡሯን ሴት ከድንበር አልመለሱም ብለዋል።
ሚኒስትሩ ማሲኤጀ ዱስካሲከይክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ስደተኛዋ ወደ ፖላንድ ድንበር አዲስ ከተወለደ ጨቅላዋ ጋር ከመጣች በኋላ ወደ ሆስፒታል ተወስዳለች ብለዋል።
አክቲቪስቶች ግን ስደተኛዋ ወደ ፖላንድ ለመግባት ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ በመቅረቱ በደን በተሸፈነው የድንበር አካባቢ ለአንድ ወር ያክል ቆይታለች ብለዋል።
የመብት ተሟጋቾች የፖላንድ ድንበር ጠባቂዎች ከቤላሩስ ወደ ፖላንድ የሚሻገሩ ስደተኞችን አናሳልፍም በማለት ከድንበር ይመልሳሉ ይላሉ።
ፖላንድ በበኩሏ የሩሲያ አጋር የሆነችው ቤላሩስ ሆነ ብላ ስደተኞች በቤላሩስ አድርገው ወደ ፖላንድ እንዲገቡ ታበረታታለች ትላለች።
የፖላንድ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኤርትራዊቷ ሴት እጅግ ቀዝቃዛ በሆነው የድንበር አካባቢ አንድ ወር መኖር ቀርቶ ብቻዋን መውለድ ጨርሶ የሚታሰብ አይደለም በማለት የአክቲቪስቶቹን አስተያየት አጣጥለዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ከሆነ የአገሪቱ ድንበር ጠባቂዎች ኤርትራዊቷን ሴት አግኝተው በድንበር አቅራቢያ ወደሚገኝ ሆስፒታል ወስደዋታል።
ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ ስደተኞች ድንበር እንዲሻገሩ የሚረዳው የሰብዓዊ መብቶች ሠራተኞች ስብስብ የሆነው ግሩፓ ጋራኒካ ድርጅት ባልደረባ የሆኑት አዳም ብራዊንስኪ የ38 ዓመቷ ሴት ፖላንድ እንዳትገባ ተከልክላለች ይላሉ።
አዳም ኤርትራዊቷ ሴት ድንበር ላይ የተተከለውን የሽቦ አጥር አልፋ የፖላንድ ወታደሮችን እርዳታ ብትጠይቅም ወደ ፖላንድ እንዳትገባ መከልከሏን ለድርጅታችን ተናግራለች ብለዋል።
አዳም በስም መጠቀስ የማትፈለግው ኤርትራዊት ሴት ከቤላሩስ ተነስታ የፖላንድ ድንበር ከመድረሷ በፊት መኖሪያ የሚሆናትን ሰላማዊ ቦታ ለማግኘት በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ኡጋንዳ በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ለበርካታ ዓመታት መኖሯን ነግራናለች ብለዋል።
“ጫካ ውስጥ ብቻዋን ነው የወለደችው። ይህ መቆም አለበት። ማንም ሰው በእንደዚህ አይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መውለድ የለበትም” ብለዋል።
አክቲቪስቶች ኤርትራዊቷ ሴት ትናንት ቅዳሜ ሚያዚያ 19/2016 ዓ.ም. ከሆስፒታል ወጥታ ከልጇ ጋር ወደ አንድ የጋራ መኖሪያ ቤት መዘዋወሯን ገልጸዋል።
የፖላንድ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኤርትራዊቷ የጥገኝነት ጥያቄ ካቀረበች በኋላ በአውሮፓ ኅብረት ሕግ መሠረት ሂደቱን ጀምረናል ብለዋል።
“ታዳጊዎችን እና ሴቶች ለመጠበቅ የተቻለንን እያደረግን ነው። ባለፉት 4 ወራት 350 ስደተኞችን ተቀብለናል” ብለዋል።
የፖላንድ መንግሥት ስደተኞችን በድንበር በኃይል ይመልሳል እየተባለ በተደጋጋሚ ይወቀሳል።
የግሩፓ ግራኒካ ባልደረባ የሆኑት አይዎ ሎስ ባለፉት 5 ወራት 1ሺህ 700 ስደተኞች ከፖላንድ ድንበር እንዲመለሱ መደረጋቸውን ገልጸው ከእነዚህ መካከል 25 የደረሱበት አይታወቅም፤ አምስቱ ደግሞ መሞታቸው ተረጋግጧል ይላሉ።
ፖላንድ እአአ 2021 ላይ ቤላሩስ ከመካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ የሚመጡ ሰዎችን በቤላሩስ በኩል ወደ ፖላንድ እንዲያልፉ ታበረታታለች ስትል ትወቅሳለች።
የአውሮፓ ኅብረት እአአ 2021 ላይ የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ለተጣለባቸው ማዕቀብ የኅብረቱን አባላት ለመጉዳት ሆነ ብለው ወደ አውሮፓ ኅብረት አባል ወደ ሆነችው ፖላንድ ስደተኞችን ይልካሉ ብሎ ነበር።