ሳፋሪኮም በድሬዳዋ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከነሐሴ ወር ጀምሮ በድሬዳዋ ውስጥ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታወቀ።

በኬንያው ሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት በዛሬው ዕለት ሐሙስ ሰኔ 30/2014 ዓ.ም. ይፋዊ በሆነው የትዊተር ሰሌዳው ላይ ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ የሚሰጠው የቴሌኮም አገልግሎት በመጪው ነሐሴ 2014 ዓ.ም ይጀምራል ብሏል።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የቴሌኮም አገልግሎቱን በድሬዳዋ ቢጀምርም፣ እስከ ሚቀጥለው ሚያዚያ 2015 ድረስ ለ25 ከተሞች የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት እቅድ ማስቀመጡን አስታውቋል።

በአፍሪካ ውስጥ ግዙፍ ከሚባሉት ጥቂት የቴሌኮም ተቋሞች መካከል አንዱ የሆነው ሳፋሪኮም፣ በኢትዮጵያ ሥራውን ከመጀመረ አንስቶ ፈቃዱን ለማግኘት የከፈለውን ጨምሮ አንድ ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጉን ገልጿል።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በይፋዊ የትዊተር ገፁ ላይ እስካሁን ድረስ፣ ለ320 ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል መፍጠሩንም ጨምሮ ገልጿል።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በ07 መነሻ መለያ ቁጥር አገልግሎት እንደሚሰጥ ከዚህ በፊት ማሳወቁ ይታወሳል።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በጥር ወር ሥራ እጀምራለሁ ብሎ የነበረ ቢሆንም በተለያየ ምክንያት እስከ አሁን ድረስ አገልግሎት መስጠት ሳይችል ቆይቷል።

ኩባንያው ለዚህ በምክንያትነት የጠቀሰው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተጀመረው የቴሌኮም መሠረተ ልማት ኪራይ ዋጋ ላይ ከስምምነት አለመድረስ፣ የኔትወርክ ዝርጋታ እና ሌሎች የመሠረተ ልማቶች ሥራ በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ እና ሌሎች ምክንያቶችን ነው።

ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመት በፊት የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንደምታደርግ ካሳወቀች በኋላ ሁለት ፈቃዶችን ለዘርፉ ተሳታፊዎች በጨረታ አቅርባ ነበር።

ኅዳር 18/2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን በአገሪቱ የቴሌኮም ዘርፍ ውስጥ ለመሰማራት ፍላጎቱ ላላቸው ኩባንያዎች ይፋዊ የጨረታ ጥሪ አቅርቦ፣ ሚያዝያ 16/2013 ዓ.ም ሁለት ተቋማት በጨረታው ተሳታፊ መሆናቸውን ማሳወቁ ይታወሳል።

ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ የተባለውና የስድስት ኩባንያዎች ጥምረት የሆነው ተቋም ኢትዮጵያ፣ ለጨረታ አቅርባቸው ከነበሩት ሁለት የቴሌኮም ፈቃዶች ውስጥ አንዱን በማሸነፍ በዘርፉ እንዲሰማራ መመረጡ ይታወሳል።

የኬንያው ሳፋሪኮም፣ የዩናይትድ ኪንግደም ቮዳፎን እና ሲዲሲ ግሩፕ፣ የደቡብ አፍሪካ ቮዳኮም፣ የጃፓኑ ሱሚቶሞ እንዲሁም ዲኤፍሲ ናቸው በአገሪቱ በኢትዮ ቴሌኮም ከ120 ዓመታት በላይ በብቸኝነት ተይዞ ወደነበረው ዘርፍ ለመግባት ፈቃድ ያገኙት።

ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ የተባለው ተቋም 850 ሚሊዮን ዶላር በማቅረብ ነበር ጨረታውን ያሸነፈው።

በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑት የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎች መካከል አንዱ በሆነው በኢትዮ ቴሌኮም ከ120 ዓመት በላይ በብቸኝነት ተይዞ ወደ ነበረው ዘርፍ በመግባት ሳፋሪኮም ቀዳሚው ነው።

ከሳፋሪኮም በተጨማሪ በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ለመግባት የሚያስችል ሁለተኛ ፈቃድ እንደሚሰጥ መንግሥት መግለጹ ይታወሳል።