ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሁለት የዩኬ ዜጎችና አንድ ሞሮኳዊ ለዩክሬን በመዋጋታቸው ሞት ተፈረደባቸው
ሁለት የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች እና አንድ ሞሮኳዊ ለዩክሬን ሲዋጉ ከተያዙ በኋላ በሩሲያ ሞት ተፈረደባቸው።
የሩሲያ ብሔራዊ ቴሌቭዥን እንዳለው፣ አይደን አስሊን እና ሿን ፒነር የተባሉት የዩኬ ዜጎች እንዲሁም ብራሒም ሳዑዳን የተባለው ሞሮኳዊ ቅጥረኛ ገዳዮች ናቸው።
በሦስቱ ግለሰቦች ሞት የፈረደው የሩሲያው ፍርድ ቤት፣ መደበኛ ፍርድ ቤት ሳይሆን በፍርድ ቤት አምሳያ የተቋቋመ ፍርድ ሰጭ ነው።
በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድም ዕውቅና የለውም።
ዩኬ እና ዩክሬን የሞት ፍርዱ ዓለም አቀፍ የጦር ምርኮኞችን ሕግ ይጻረራል ሲሉ ተቃውመዋል።
የዩኬ ተወላጆቹ ቤተሰቦች እንደሚሉት፣ ግለሰቦቹ በሩሲያ መከላከያ ውስጥ ለዓመታት ያገለገሉ ወታሮች እንጂ ቅጥረኛ ገዳዮች አይደሉም።
የሩሲያው ታስ መገናኛ ብዙኃን የግለሰቦቹን ጠበቃ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ አቤቱታ ማሰማት ይፈልጋሉ።
ሦስቱም ፍርድ ቤት የቀረቡት ቅጥረኛ ገዳይ በመሆን፣ በጉልበት ሥልጣን ለመገርሰስ በመሞከር እና የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሥልጠና በመውሰድ ነው።
የዩኬ መንግሥት ግለሰቦቹን ለማስለቀቅ ከዩክሬን ጋር እየሠራ መሆኑን ከዳውኒንግ ስትሪት የተሰጠ መግለጫ ይጠቁማል።
“የጦር ምርኮኞች ለፖለቲካ ዓላማ መበዝበዝ የለባቸውም። በጄኒቫ ስምምነት መሠረት ውጊያ ላይ ለነበሩ ሰዎች የሚሰጥ ከለላ ሊደረግላቸው ይገባል” ተብሏል።
የዩኬ የውጭ ጉዳይ ኃላፊት ሊዝ ትረስ “ሕጋዊ መሠረት የሌለው የውሸት ፍርድ” ሲሉ ኮንነዋል።
ከዩክሬን የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ጋር ከሰሞኑ ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዩኬ ጉዳዩን ዩክሬን እንድትፈታው ከመተው ይልቅ በቀጥታ ሩሲያ ጋር ግብግብ ውስጥ ከገባች፣ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ይፈጠራል ብለው ይሰጋሉ።
ዩኬ ጣልቃ የምትገባ ከሆነ ግለሰቦቹ ‘ቅጥረኛ ገዳይ’ ናቸው የሚል መልዕክት ሊያስተላልፍም ይችላል።
ግለሰቦቹ በእስረኛ ልውውጥ ወቅት ሊለቀቁ የሚችሉበትም ዕድል ቢኖርም ከዚህ ቀደም የተደረጉ ሙከራዎች ተስፋ ሰጪ አልነበሩም።
የሩሲያው ፍርድ ቤት ዳኛ አሌክሳንደር ኒኩሊን በፍርዱ ወቅት “ፍርዱ ሕግን የተከተለ ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊም ነው” ማለታቸው ተዘግቧል።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለቢቢሲ እንደገለጸው፣ በዩክሬን ግዛት የሚዋጉ የሌሎች አገራት ዜጎች ባጠቃላይ በዓለም አቀፍ ሕግ እንደ ጦር ምርኮኛ መብታቸው ይከበራል።
“ግለሰቦቹ በፍርድ ሂደቱ ወቅት ስቃይ ውስጥ መሆናቸው ታይቷል። ዩክሬንን የተከላከሉ ሰዎችን ነጻ ለማስወጣት እንሠራለን” ብለዋል።
አንድ የዩኬ ወግ አጥባቂ የምክር ቤት አባል “ፍርድ ቤቱ የእውነት ፍርድ ቤት አይደለም። ዳኞቹም የደንብ ልብስ ለብሰው እያስመሰሉ ነው። ሦስት ንጹሐን እየተንገላቱ ይገኛሉ” ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ የሚገኘው ራሷን ዶንቴስክ ፒፕልስ ሪፐብሊክ ብላ በምትጠራው ግዛት ነው።