የትራምፕን አወዛጋቢ ፖሊሲዎችን ከኋላ ሆኖ የሚዘውረው ብዙም ያልተነገረለት ሚለር ማን ነው?

ስቴፈን ሚለር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ስቴፈን ሚለር በፖለቲካ ውስጥ ካሳለፋቸው ጨለማ ቀናት የታደጉት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

ስቴፈን ሚለር ለዓመታት በዶናልድ ትራምፕ የፖለቲካ ምህዋር ውስጥ ወግ አጥባቂ ሆኖ ቆይቷል።

በዋይት ሐውስ የፖሊሲ አውጪ ኃላፊነት ያሳየው የማያወላውል አቋም እና የተገዳዳሪነት መንፈስ የፕሬዚዳንቱን ጠንካራ የኢሚግሬሽን አጀንዳ ወደፊት እንዲራመድ አስችሎታል።

ከዚህም ባለፈ የአሜሪካን ኃይል በምዕራባዊ ንፍቀ ክበብ በማስፋት ረገድ ተጽዕኖው እየጨመረ አንዲመጣ አድርጓል።

የትራምፕ አስተዳደር በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በ2026 ከፍተኛ ፍጥነት የጀመራቸው ፖሊሲዎች እጅግ ኃያል ፖለቲከኛ ሆኖ ቦታውን አንዲያጸና አግዞታል።

ከእርሱ በተቃራኒ ለቆሙ ግን ጠላት ነው።

በዋሺንግተን ዲሲ በሕዝብ መሰብሰቢያ ሥፍራዎች የተለጠፉ የእርሱ ምሥሎች ላይ "ፋሺዝም" የሚል ስላቅ ተጽፎባቸዋል።

ዲሞክራቶች ከኃላፊነቱ እንዲለቅ ጠይቀዋል። አንደንድ የራሱ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትም በይፋ ፖለቲካ ውሳኔዎቹን እና ብቃቱ ላይ ያላቸውን ጥያቄዎች አንስተዋል።

ባለፉት ሳምንታት ደግሞ ሚለር ራሱን ዝነኛ ባልሆነበት አካባቢ አግኝቶታል።

ከጀርባ ሆኖ የትራምፕን ፖሊሲዎች ያሽከረክር የነበረው ግለሰብ ድንገት ከፊት መጥቶ የዐይን ሁሉ ማረፊያ ሆኗል።

እያንደንዱ የሚናገራቸው ቃላት ተበጥረው እና ተነጥረው ይታያሉ፤ ይተነተናሉ።

'ሁሌም ክንደ ብርቱ፤ ሸብረክ ማለት የማያውቀው'

የፌደራሉ የኢሚግሬሽን ተቆጣጣሪዎች ባለፈው ወር በሚኒያፖሊስ አሌክስ ፕሬቲን ተኩሰው ከገደሉ በኋላ ሚለር በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ በርካታ ነገሮችን አጋርቷል።

ሚለር በእነዚህ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎቹ የሕክምና ባለሙያውን "የአገር ውስጥ አሸባሪ፤ አንዲሁም ነፍሰ በላ" ሲል ወንጅሎታል።

የትራምፕን የ2016 የምርጫ ዘመቻ በኃላፊነት ያገለግል ለነበረ ሰው ይህ የተለመደ የጥላቻ ንግግር ነበር።

ዴሞክራቶችን "የአመፅ እሳትን እያቀጣጠሉ ነው" ሲል ከሷቸዋል። የሰጣቸው አስተያየቶችም በተጨባጭ በሀሰተኛ መረጃ የተሞሉ ነበሩ።

የቪዲዮ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ፕሬቲ ምንም እንኳን ፈቃድ ያለው ሽጉጥ ቢይዝም፣ ዐይኑ ላይ የሚያቃጥል ፈሳሽ (ፔፐር ስፕሬይ) ተረጭቷል።

10 ጊዜ በጥይት ከመመታቱ በፊትም የጉምሩክ እና የድንበር ቁጥጥር ባለሥልጣናትን አላስፈራራም።

የተቃውሞ ሠልፈኞች በኒውዮርክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የተቃውሞ ሠልፈኞች በኒውዮርክ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከቀናት በኋላ ሚለር ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ አስተዳደሩ ግድያውን በሚመለከት "በቦታው ከተገኘ ሪፖርት ላይ የተመሠረተ" በሚል የሰጠውን መረጃ በተቃረነ ተቆጣጣሪዎቹ ተገቢውን መመሪያ "አልተከተሉ ይሆናል" ብሏል።

እንደ ሚለር ላለ ተገዳዳሪ ረዳት እንዲህ ዓይነት መግለጫ ወደ ኋላ ማፈግፈግ እና ያልተለመደ ነው።

ነገር ግን ዲሞክራቶች የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ተቆጣጣሪዎች ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወስዱ ያበረታታል ሲሉ ይተቹታል።

የኮንግረስ አባሉ ዶን ቤየር በማኅበራዊ ሚደያ ገጻቸው ላይ "ለስቴፈን ሚለር የአሜሪካ ዜጎች በአይስ እና ሲቢፒ መገደላቸው ብቻ በቂ አይደለም፤ በኋላም ስለሞታቸው ሐሰተኛ መረጃ ይሰጣል" ሲሉ ኮንነውታል።

አክለውም "ሚለር ኢፍትሐዊ፣ ደም መጣጭ እና ጨካኝ ነው፣ እና ፖሊሲዎቹ በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ሕይወትን አደጋ ላይ ይጥላሉ" ብለዋል።

በግንቦት ወር ሚለር የኢሚግሬሽን ተቆጣጣሪዎች ሰነድ አልባ ግለሰቦችን ከአሜሪካ ከተሞች በቁጥጥር ሥር በማዋል ከአገር እንዲያባረሩ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ለፎክስ ኒውስ በቀን 3000 ሰነድ አልባ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል መታቀዱን ተናግሯል።

እንደ ዋሺንግተን ኤግዛማይነር ዘገባ ከሆነ ሚለር በአንድ ስብሰባ ላይ የፌደራል ተቆጣጣሪዎች በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች የሚገኙ ሰነድ አልባ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚጠበቅባቸውን አልሠሩም በሚል ክፉኛ አብጠልጥሏቸዋል።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እንደ ዋሺንግተን ዲሲ፣ ሻርለት፣ ቺካጎ እና ሚኒያፖሊስ ያሉ ትልልቅ የአሜሪካ ከተሞች እርምጃቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

የአገር ውስጥ መሥሪያ ቤት ኃላፊዋ ክርስቲ ኖም የትራምፕ አስተዳደር ሰነድ አልባ ስደተኞችን የማስወጣት እርምጃን በማስፈጸም ረገድ ከጀርባ አሉ በሚል ለሚቀርብባቸው ትችት ለአክሲዮስ የዜና ወኪል ሲመልሱ "የሠራሁትን ሁሉ ያደረግኩት በፕሬዚዳንቱ እና ስቴፈን ትዕዛዝ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

አሜሪካኖችን ያስከፋው እርምጃ

ሚለር ሰነድ አልባ ስደተኞችን ለማስወጣት የተነሳሳው በዘረኝነት እና በጭፍን ጥላቻ ተገፍቶ ነው በሚል የሚቀርብበትን ክስ ያስተባብላል።

የኢሚግሬሽን ፖሊሲው ትራምፕ ለመራጮቻቸው የገቡትን ቃል የሚፈጽሙበት እና ቃል ኪዳናቸውን የሚጠብቁበት አንዱ መንገድ ነው በማለትም ይከራከራል።

ሆኖም ትራምፕ ሁለት አሜሪካውያን በሚኒያፖሊስ በኢሚግሬሽን መኮንኖች መገደላቸውን ተከትሎ የሚወሰደው እርምጃ "ረገብ ማለት" ያስፈልገዋል ብለዋል።

ትራምም በኢሚግሬሽን ፖሊሲያቸው ላይ ያለቸው ተቀባይነት ወደ 39 በመቶ ወርዷል። ይህ ደግሞ ወደ ዋይት ሐውስ ከመጡ በኋላ ያገኙት ዝቅተኛው የሕዝብ አስተያየት ነው።

በርካታ ሰዎች 58 በመቶ ያህሉ የኢሚግሬሽን መኮንኖች ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአገር ለማስወጣት የሚወስዱት እርምጃ ተመጣጣኝ አይደለም ወይም ከተገቢው በላይ ነው ብለው ያምናሉ።

ይህ ቅሬታ ደግሞ ሚለርን በተቺዎቹ ፊት ለፊት ላይ ያለምንም መከላከያ ጋሻ ያስቀምጠዋል።

በትራምፕ የ2016 እና 2024 ምርጫ ዘመቻ ወቅት ስትራቴጂስት በመሆን የሠሩት ብራያን ላንዛ፣ ሚለር ሰነድ አልባ ስደተኞችን በጅምላ ከአገር ለማባረር የተቀረጸው ፖሊሲ አርቃቂ ነው ይላሉ።

ሚለር በላስቬጋስ ንግግር ሲያደርግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሚለር በትራምፕ ዑ2016 የምረጡን ዘመቻ ወቅት ንግግር ሲያደርግ

በዓመታት ውስጥ ግን ሚለር የሚቀርቡበትን ክሶች እና ውንጀላዎች በድል ሲወጣ ታይቷል።

ንግግር አዋቂ የሆነው ሚለር ከሁለተኛ ደረጃ ተማሪነቱ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በፖለቲካው መድረክ ከጀርባ በመሆን ብዙ ነገሮችን አከናውኗል።

በተለይ በትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ላይ መሳተፉ ከጀርባ ለሚኖር የተቀናቃኝ ቡድን ግፊያ እና ጉሸማ አዲስ አንዳይሆን አድርጎታል።

በአውሮፓውያን 2019 ለዋሺንግተን ፖስት ትራምፕ ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ ስሰማ "ነፍሴ አንዳች ንዝረት ተሰማት" ሲል ስሜቱን ተናግሮ ነበር።

ሚለር ፕሬዚዳንት ትራምፕ በ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሲሸነፉም፣ በካፒቶል ሂል ትችት ሲዘንብባቸው እንዲሁም ዋሺንግተንን ለቅቀው ሲሄዱ ከጎናቸው ነበር።

ባለፈው ዓመት ትራምፕ ወደ ሥልጣን ሲመለሱ እርሱም አብሮ መጥቷል።

ላንዛ "ስቴፈን ሚለር የትራምፕ ጭንቅላት ነው" ይላሉ። "ሁልጊዜ . . . በማንኛውም ጉዳይ ላይ አቋሙን እንደሚደግፍ በስቴፈን ላይ ሊተማመንበት ይችላል" ሲሉ አክለዋል።

ለፕሬዚዳንቱ የሚናገረው

ሚለር በዋይት ሐውስ ያለው ይፋዊ ሥልጣን የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ምክትል እና የአገር ውስጥ ደኅንነት አማካሪ የሚል ነው።

የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮላይን ሌቪት ለቢቢሲ "ስቴፈን ሚለር ፕሬዝዳንት ትራምፕን ለዓመታት በታማኝነት አገልግሏል። ምክንያቱም አስተዋይ፣ ታታሪ እና ታማኝ ነው" ስትል ተናግራለች።

"ስቴፈን እያንዳንዱን የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ፖሊሲ በከፍተኛ ፍጥነት መተግበሩን ለማረጋገጥ ሁሉንም የመንግሥት ጫፎች ያሰባስባል። ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበው ውጤት ስለእርሱ ይናገራል።"

ባለፈው ዓመት ሚለር የዋይት ሐውስ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ይሆናል የሚል ወሬ ተናፍሶ ነበር። ነገር ግን ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሚናፈሰውን ወሬ ውድቅ አድርገዋል።

"ስቴፈን ከዚያ በላይ ከፍ ብሎ በሰንደቁ ላይ የሚውለበለብ ግለሰብ ነው" ነበር ያሉት።

ባለፈው መጋቢት ወር ዩናይትድ ስቴትስ በየመን የሁቲ አማፂያን ላይ የአየር ጥቃት ለመሰንዘር በዝግጅት ላይ ሳለች፣ የአትላንቲክ አርታኢ ጄፍሪ ጎልድበርግ የደረሰው የሲግናል የጽሑፍ መልዕክቶች ሚለርን በዋይት ሐውስ ዕቅዶች ውስጥ ማዕከል መሆኑን አሳይተዋል።

"እንደሰማሁት የፕሬዚዳንቱ ይሁንታ ተገኝቷል። እርምጃውን ውሰዱ" ሲል ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስን፣ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴትን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮንን ጨምሮ ለከፍተኛ ረዳቶች ቡድን ባሉበት የመልዕክት መለዋወጫ ላይ ጽፏል።

ስቴፈን ሚለር በርቀት ይታያል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከጥቂት ወራት በፊት ሚለር በካሪቢያን አካባቢ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ንብረት ናቸው በሚል የተጠረጠሩ ጀልባዎችን ለማውደም የተካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ የመቆጣጠር ኃላፊነት ተጥሎበት እንደነበር ተዘግቧል።

ይህም በጥር ወር መጀመሪያ ላይ የቬንዙዌላውን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ከሥልጣን እስከ ማንሳት ድረስ ተስፋፍቷል።

ትራምፕ በማር-አ-ላጎ ሪዞርት ውጤታማ ወታደራዊ ዘመቻ መካሄዱን እና ማዱሮ መያዛቸውን ይፋ ሲያደርጉ በዙሪያቸው ከነበሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ሚለር ነበር።

ላንዛ ሚለር በውጪ ፖሊሲ ላይ ያለው ሚና ያልተለመደ ነው ይላሉ።

በተጨማሪም "ስቴፈን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተለመደውን መንገድ የሚከተሉ ፕሬዚዳንት አለመሆናቸውን በሚገባ ያውቃል፤ ስለዚህ በዙሪያቸው ለምክር እና ለግብዓት ማን እንደሚፈለግ በሚገባ ይረዳል" ሲሉ ተናግረዋል።

"ስቴፈን በፕሬዚዳንቱ ዙሪያ በመሆን እና ግብዓቶችን በመስጠት ጥሩ ሥራ ሠርቷል። ስቴፈን የተለመደውን ሕግ በሚከተል ፕሬዚዳንት ስር ቢሆን ኖሮ ይህንን ያህል ውጤታማ አይሆንም ነበር።"

ካቲ ሚለር ከስቴፈን ሚለር ጎን ቆማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካቲ ሚለር፣ የስቴፈን ሚለር ባለቤት ወግ አትባቂ ሴቶችን ለመሳብ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ፖድካስት ታዘጋጃለች

ከትራምፕ ጋር እስከ መጨረሻው የሚቆዩት ሚለር

ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ በተመለሱበት የመጀመሪያ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሚለር በአስተዳደሩ ታላላቅ የፖለቲካ ሥራዎች ውስጥ ተሳትፏል። ይህም ያለውን ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳይ ነው።

ከቬንዙዌላ ወረራ በኋላ፣ ሚለር የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር በምዕራቡ ንፍቀ ክበብ ላይ የበላይ ለመሆን የያዘውን አቋም ለመከላከል በሲኤንኤን ላይ ቀርቦ ነበር።

ዝነኛ ፖድካስተር የሆነችው የሚለር ባለቤት በበኩሏ በኤክስ ገጿ ላይ የግሪንላንድ ካርታ ላይ የአሜሪካን ሰንደቅ ዓላማ በማኖር ካጋራች በኋላ ፕሬዚዳንቱ ደሴቲቱን ለመቆጣጣር ያላቸው ፍላጎት በስፋት መነጋገሪያ ሆኗል።

እናም ይህንን የፕሬዚዳንቱን ፍላጎት እና አቋም ከካሜራ ፊት ለፊት ቆሞ የሚያስረዳው፣ የሚያብራራው እና የሚከላከለው ስቴፈን ሚለር ነበር።

በ2025 ሊብራል የሆነ ቡድን በብሎጉ ላይ "ስቴፈን ሚለር የትራምፕ አስተዳደርን አጀንዳዎች በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ሚና አለው" ብሎ ጽፎ ነበር።

"መንግሥት ስደተኛ ቤተሰቦች ላይ እርምጃ እንዲወስድ በማድረግ በመንግሥት ውስጥ የነጭ የበላይነት የሚለው አስተሳሰብ እንዲቀነቀን፣ እስካሁን ያሳለፈው የሥራ ዘመን ጭፍን ጥላቻ ተቋማዊ አቅም ሲያገኝ ምን አንደሚፈጠር ማሳያ ነው" ሲል ይደመድማል።

ሚለር ለቀሰቀሰው የትኛውም ውዝግብ ከትራምፕ ጋር ያለው የቅርብ ወዳጅነት የረዳው ሲሆን፣ በዙሪያቸው ካሉ ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ እንዲሆን አድርጎታል።

ባለፈው ሳምንት የሳውዝ ካሮላይናዋ ሴናተር ሊንድሲ ግርሃም "ዶናልድ ትራምፕን እናሳምነዋለን ብላችሁ ለምታምኑ ባልደረቦቹ ስቴፈን ሚለር የእርሱ ቀኝ እጅ መሆኑን አትዘንጉ፤ መልካም ዕድል " ብላለች።

"የትራምፕ ዘመን ማብቂያ ደርሶ ሰዓቱ 12 ሲያሳይ ጥቂት ሰዎች ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በመሆን ቢሮውን ለቅቀው ይወጣሉ። ስቴፈን ሚለር ከእነዚያ መካከል አንዱ ይሆናል" ሰትልም ፕሬዚዳንቱ እና ረዳታቸው ያላቸውን ቅርበት ገልጻለች።