የሱዳን ጦር የብሔራዊ ቴሌቪዥን ማሰራጫ ዋና ቢሮን መልሶ ተቆጣጠረ

የሱዳን ጦር በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ለወራት በቁጥጥር ስር ሆኖ የቆየውን የብሔራዊ ቴሌቪዥን ማሰራጫ ዋና መስሪያ ቤትን መልሶ ተቆጣጠረ።

ጦሩ በኦምዱርማን ከተማ የሚገኘውን ጣቢያ መልሶ መያዙ ለ11 ወራት በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ትልቅ ድል ተደርጎ ተመዝግቦለታል።

በጀነራል ሐምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ) የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የብሔራዊ ቴሌቪዥን ማሰራጫ ዋና መስሪያቤቱን የእርስ በእርስ ጦርነቱ እንደተጀመረ ነበር የተቆጣጠረው።

ማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተዘዋወሩ ያሉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች የሱዳን ጦር አባላት ከማሰራጫ ጣቢው ፊት ለፊት ደስታቸውን ሲገልጹ አሳይተዋል።

የአገሪቱም ጦር ኦምድሩማን ከተማ የሚገኘው ዋና መስሪያ ቤትን መልሶ መቆጣጠሩን “ትልቅ ድል” ብሎታል።

በአገሪቱ በሁለት የጦር ጀነራሎች የስልጣን ሹክቻ የተጀመረው የእርስ በእርስ ጦርነት አንድ ዓመት ሊደፍን ጥቂት ሳምንታት ብቻ ነው የሚቀሩት።

በዚህ ጦርነት ከ8 ሚሊዮን የማያንሱ ሱዳናውያን መኖሪያቸውን ጥለው የተሰደዱ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሕይወታቸውን አጥተዋል። በንብረት እና መሠረተ ልማት ላይ ደግሞ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል።

አሁን ላይ ጦርነቱ ከባድ የሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጥር እንደሚችል ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ ይገኛል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ምንም እንኳ ይህን ማሰራጫ ጣቢያ ለወራት ተቆጣጥሮት ቢቆይም አገልግሎት ላይ ማዋል ሳይቻለው ቀርቷል።

ብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች በማሰራጨት ሳያቋርጥ ቀጥሎ ቆይቷል።

የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ የአገሪቱ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መዲናዋን ካርቱም እና አጎራባች ከተሞችን ለቆጣጠር ትልቅ ውጊያ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክት ቤት በረመዳን የጾም ወር ላይ ሁለቱ ወገኖች ተኩስ እንዲያቆሙ ጥሪ ቢያቀርብም በካርቱም የተለያዩ አካባቢዎች ከባድ ውጊያዎች እየተካሄዱ ነው።

የሱዳን ጦርነት የተቀሰቀሰው የአገሪቱን መንግሥት ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማሸጋገር በነበረ ውጥን ላይ በየአገሪቱ ጦር መሪ ጀነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጀነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ መካከል አለመግባባት ከተፈጠረ በኋላ መሆኑ ይታወሳል።

ጦርነቱ የንፁሃንን ሕይወት ከመቅጠፉ እና ከማፈናቀሉ በተጨማሪ በተለይ ካርቱምን ወደ ፍርስራሽነት እየቀየራት ይገኛል።

ሁለቱ የጦር መኮንኖች ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ለማድረግ የተደረጉት ዓለም አቀፍ ጥረቶች ውጤት አልባ ሆነው ቆይተዋል።