ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አወዛጋቢው ተጽእኖ ፈጣሪ አንድሩ ቴት የእስር ማዘዣ ወጥቶበት ሩሜኒያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለ
አወዛጋቢው ተጽእኖ ፈጣሪ አንድሩ ቴት እና ታናሽ ወንድሙ ትሪስታን ቴት በዩናይትድ ኪንግደም የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው በኋላ ሩሜኒያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ሁለቱ ወንድማማቾች በዩኬ የእስር ማዘዣ የወጣባቸው ብሪታኒያ ውስጥ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ፈጽመዋል የሚል ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ነው።
የ37 ዓመቱ አንድሩ ቴት እና የ35 ዓመቱ ወንድሙ የቀረቡባቸውን ክሶች “ሙሉ በሙሉ ውድቅ” እንደሚያደርጉ ተወካያቸው ገልጸዋል።
ሁለቱ ግለሰቦች በሩሜኒያ ፖሊስ ከተያዙ በኋላ ማክሰኞ ከሰዓት ላይ በመዲናዋ ቡካሬስት ወደሚገኝ ፍርድ ቤት ሲወሰዱ ታይተዋል።
የብሪታኒያ እና የአሜሪካ ጥምር ዜግነት ያለው አወዛጋቢው አንድሩ ቴት በሰዎች የሕገ-ወጥ ዝውውር እና ከአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ሩሜኒያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረ ሲሆን ከእስር ቤት ወጥቶ በቁም እስር ለረዥም ጊዜ ቆይቷል።
ይህ ራሱን “ለሴቶች ጥልቅ ጥላቻ ያለው ሰው” አድርጎ የሚገልጸው ግለሰብ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሚያጸባርቃቸው አመለካከቶች ተጽእኖ ፈጣሪነቱ ባለፉት ዓመታት እጅጉን ጨምሯል።
ከዚህ ቀደም በነበረው የስፖርት ሕይወቱ አራት ግዜ የኪክቦክስ የዓለም ሻምፒዮና መሆን የቻለው ቴት በተለይ በቲክቶክ አማካይነት ሴቶችን በተመለከተ የሚሰጣቸው “አጸያፊ እና አስነዋሪ” የተባሉት አስተያየቶቹ ዝነኛ አድርገውታል።
አንድሩ ቴት ሴቶችን በተመለከተ በሚሰጣቸው አስተያየቶች ምክንያት ከፌስቡክ፣ ከኢንስታግራም እና ከዩቲዩብ ታግዷል።
ሁለቱ ወንድማማቾች ከዩኬ ዐቃቤ ሕግ ከቀረበባቸው ክስ በተጨማሪ በሩሜኒያ መንግሥት ከአስገድዶ መድፈር፣ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና አደገኛ ቡድን መመስረት በሚሉ ወንጀሎች ምርመራ እየተደረገባቸው ነው።
ወንድማማቾቹ ጾታዊ ግንኙነቶች መዝናኛ ተደርገው በሚሰራበት ኢንዱስትሪ ውስጥ ሴቶችን የሚበዘብዝ የወንበዴ ቡድን በመመስረት ክስ ይቀርብባቸዋል። ይሁን እንጂ ቴት እና ወንድሙ በሩሜኒያ መንግሥት የቀረበባቸውን ክስ ውድቅ ያደርጋሉ።
በአንድ የዩቲዩብ ቪዲዮ ላይ ቴት እራሱን “የለየለት በሴቶች ጥላቻ ያበደ ሰው” አድርጎ እንደሚመለከት ገልጾ ነበር።
አንድሩ ቴት በዚሁ ቪዲዮ ላይ ሴቶችን “የለየላቸው ሰነፎች” ሲል ከገለጸ በኋላ “እራሷን የቻለች ሴት” ብሎ ነገር የለም ይላል።
ቴት ሴቶችን ከኮምፒዩተር ፊትለፊት አስቀምጦ በኢንተርኔት አማካይነት ወንዶችን እንዲያማልሉ በማድረግ ከወንዶች በሚቀበለው ገንዘብ ሃብት እንዳፈራ ይነገራል።
ቴት “ቤቴ ሆኜ በቪዲዮ ካሜራ አማካኝነት እራሴን ሚሊየነር ማድረግ የቻልኩ ሰው ነኝ” ይላል።
“በአራት ቦታዎች ላይ ያሉ 75 ሴቶች ለእኔ እየሰሩ በየወሩ 600 ሺህ ዶላር አገኛለሁ” ሲል ቃለ መጠይቅ ሰጥቶ ነበር።
ቴት በተደጋጋሚ የሩሜኒያ ዐቃቤ ሕግ በእርሱ ላይ ምንም አይነት ማስረጃ ማቅረብ እንደማይችል የሚናገር ሲሆን ክሶች በተደጋጋሚ የሚቀርቡብኝ እኔን ዝም ለማሰኘት ነው ይላል።