ከፍተኛ ጫና የበዛባቸው የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ከስልጣን መልቀቃቸው ተነገረ

ለሳምንታት የዘለቀውን ከፍተኛ ጫና እና በአገሪቱ እየጨመረ ያለውን የከፋ ነውጥ ተከትሎ የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪየል ሄንሪ ከስልጣን ለመልቀቅ መስማማታቸውን የካሪቢያን አገራት ቡድን ሊቀ መንበር አስታወቁ።

የቀጣናው መሪዎች በሄይቲ የፖለቲካ ሽግግር ላይ ለመምከር ሰኞ ዕለት በጃማይካ መገናኘታቸውንም ተከትሎ ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን ለመልቀቅ መስማማታቸው የተነገረው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት በታጠቁ ቡድኖች ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ በመከልከላቸው በፖርቶ ሪኮ ውስጥ ይገኛሉ።

ከቀድሞው የሄይቲ ፕሬዚዳንት ግድያ፣ ከአውሮፓውያኑ 2021 ጀምሮም አገሪቱን ሲመሩ ቆይተዋል።

በጃማይካ መዲና ኪንግስተን የተካሄደውንም ስብሰባ ተከትሎ የካሪቢያን አገራት ማህበረሰብ ሊቀመንበር እና የጋያና ፕሬዚዳንት ኢርፋን አሊ እንደተናገሩ “የሽግግር ፕሬዚዳንት ምክር ቤት መቋቋም፣ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሰየም እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን መልቀቃቸውን እናረጋግጣለን” ብለዋል።

በቅርብ ቀናት ውስጥ የታጠቁ ቡድኖች የሄይቲ መዲና ፖርቲ ኦ ፕሪንስን ጎዳናዎች በመቆጣጠር ያልተመረጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ከስልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል።

የታጣቂ ቡድኖች ጥምረት በፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር እንዲሁም ሁለቱን የሄይቲ ትላልቅ እስር ቤቶች መውረራቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአለም አቀፍ የጸጥታ ኃይል በአገራቸው እንዲሰማራላቸው ውል ለመፈረም በኬንያ ተገኝተው ነበር።

ከኬንያ ሲመለሱም ጠቅላይ ሚኒስትሩን የጫነው አውሮፕላን በተከተታይ ጥቃት ባስተናገደው የሄይቲ አለም አቀፍ አውሮፕላን እንዳያርፍ ተደረገ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሄይቲ የመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ቢገልጹም ይህንን ለማድረግ የአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ መሻሻል እንዳለበት በኪንግስተን ውይይት ላይ መነገሩን አሜሪካ አስታውቃለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሚደገፈው እና ኬንያ ትመራዋለች ተብሎ ለሚጠበቅ 1 ሺህ አባላት ያሉት የጸጥታ ኃጥል 100 ሚሊዮን ዶላር ይሰጣል ብለዋል።

አሜሪካ አጠቃላይ ለጸጥታ ኃይሉ 300 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለሰብዓዊ እርዳታ 33 ሚሊዮን ዶላር እንደምትመድብ አስታውቃለች።

የካሪቢያን አገራት መሪዎች የሆነው የካሪኮም ቡድን፣ ከአሜሪካ እና ከሄይቲ ተወካዮች ጋር በመሆን በፖለቲካው የሽግግር ማዕቀፍ ላይ ተወያይተዋል።

በሄይቲ የሚቋቋመው የሽግግር ፕሬዚዳንታዊ ምክር ቤት ሁለት ታዛቢዎች እና ሰባት ድምጽ ሰጪ አባላት ያሉት ሲሆን ከነዚህም መካከል የግሉ ሴክተር፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች፣ የጥምረት ተወካዮች እና አንድ የሃይማኖት መሪን ያካተተ እንደሚሆን ፕሬዚዳንት አሊ አስታውቀዋል።

ምክር ቤቱ “በፍጥነት” ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትርን የመሾም ስልጣን ተሰጥቶታል።

ምክር ቤቱ አገሪቱ በአውሮፓውያኑ 2026 ለምታደርገው ምርጫ መንገድ ይጠርጋል ተብሎ ይጠበቃል ።

ፕሬዚዳንት ጆቬኑል ሞይስ ከተገደሉ በኋላ ስልጣን የተቆናጠጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንሪ የጸጥታው ሁኔታ መሻሻል አለበት በሚል ምክንያት ምርጫውን በተደጋጋሚ አራዝመውታል።