በሕዝባዊ በዓላት ላይ የሚታዩ ሰንደቅ ዓላማዎች ዓይነት በሕግ እንዲወሰኑ ተጠየቀ

የሕዝብ በዓላትን እና የበዓላት አከባባርን ለመወሰን የወጣው ረቂቅ አዋጅ ሃይማኖታዊ እና ብሔራዊ የሕዝብ በዓላት ላይ የሚታዩ ሰንደቅ ዓላማዎችን ዓይነት በግልጽ እንዲያስቀምጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ተጠየቀ።

ጥያቄው የተነሳው የሕዝብ በዓላትን እና የበዓላትን አከባባር ለመወሰን ወጣው ረቂቅ አዋጅ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 3/2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት ነው።

ረቂቁ ለምክር ቤቱ የቀረበው ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ ለመምራት ነው።

በተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ አዋጁ እና ማብራሪያ በንባብ ካሰሙ በኋላ አዋጁ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ ሊመለከታቸው ይገባሉ የተባሉ ጉዳዮች ከምክር ቤቱ አባላት ተነስተዋል።

አስተያየት ከሰጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል የብልጽግና ፓርቲን ወክለው ወንበር ያገኙት ዶ/ር ከፈና ኢፋ አንዱ ናቸው።

“አብዛኞቹ በዓላት በሚከበሩበት ጊዜ የሕዝብን ክብር [እና] ስብዕና የሚነኩ ባህሎች [ትዕይንቶች] ይታያሉ” ያሉት ዶ/ር ከፈና፣ በአዋጁ ቢካተቱ ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል።

ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ደንዲ 2 ምርጫ ክልል የተመረጡት ዶ/ር ከፈና በአዋጁ ቢካተት ያሉት፣ በሕዝባዊ በዓላት ላይ የሚታየውን የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ የሚመለከት ድግጋጌን ነው።

“ኢትዮጵያ በሕግ የተደነገገ ሰንደቅ ዓላማ አላት በእነዚህ [ሃይማኖታዊ እና ብሔራዊ] በዓላት ላይ መታየት ያለባቸው እነዚህ ሰንደቅ ዓላማዎች በግልጽ [በአዋጁ] መቀመጥ አለባቸው” ሲሉ አብራርተዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከበሩ ሕዝባዊ በዓላት ላይ የበዓሉ አክባሪዎች በሚይዟቸው ሰንደቅ ዓላማዎች እና ሌሎች አርማዎች ምክንያት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ውዝግ አለፍ ሲልም ግጭት ውስጥ ሲገባ ተስተውሏል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ የፀጥታ ኃይሎች ያልተፈቀደ ያሉትን ሰንደቅ ዓላማ ይዘዋል የተባሉ ሰዎች በበዓላት ላይ እንዳይገኙ ከመከልከል በተጨማሪ በቁጥጥር ሥር እስከማዋል ደርሰው እንደነበር ይታወሳል።

ዶ/ር ከፈና አክለውም በአንዳንድ ሃይማኖታዊ እና ብሔራዊ በዓላት ላይ “የሌሎችን ብሔር ብሔረሰቦች ክብር እና አጠቃላይ ሁኔታ የሚያጎድፉ ነገሮች” እንደሚታዩም አንስተውል።

“አንዳንድ ጊዜ የሰውን ሥነ ልቦና የሚነኩ [በጦር] መሳሪያ ጭምር የታገዙ የሕዝብ በዓላት የሚከበሩበት ሁኔታ አለ” ያሉት የሕዝብ እንደራሴው፤ “እነዚህ ነገሮች በግልጽ መቀመጥ ያለባቸው ይመስለኛል” ብለዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ የምክር ቤት አባል አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው፤ አዋጁ ክልሎች የራሳቸውን ክብረ በዓል በተመለከተ ሕጎችን እንዲያወጡ የሚደግፍ ድንጋጌ እንዲካተትበት ጠይቀዋል።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው አዋጅ በፌደራል ደረጃ የሚከበሩ ብሔራዊ በዓላትን የሚመለከት መሆኑን የጠቆሙት አራሬ፤ “ክልሎች ሕገ መንግሥት እና ምክር ቤት እንዳላቸው ሁሉ፤ በዚያው ልክ ደግሞ የራሳቸው የሆነ ክብረ በዓላት አሏቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

የምክር ቤት አባሏ አክለውም፤ “ክልሎች የራሳቸውን በዓል እንዲያከብሩ አዋጅም እንዲያወጡለት ቢደረግ ጥሩ ነው” ብለዋል።

ይህንን ለማድረግም “በፌደራል ደረጃ [አዋጅ] ባናወጣ ራሱ በክልል ደረጃ ክልሎች ለራሳቸው ብሔራዊ ክብረ በዓል [አዋጅ] እንዲያወጡ የሚደግፍ አንቀጽ [ይኼኛው] አዋጅ ቢገባባት” ሲሉ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።

ምክር ቤቱም ሁለቱን አስተያየቶች ካዳመጠ በኋላ አዋጁን ለዝርዝር ዕይታ በዋናነት ለጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም በተባባሪነት ለሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቶታል።

ይህ ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላለፉት 49 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየው የሕዝብ በዓላትን እና የእረፍት ቀንን ለመወሰን የወጣውን አዋጅ የሚተካ ነው።

አሁን በሥራ ላይ ያለው እና በደርግ ዘመነ መንግሥት የወጣው አዋጅ 13 ብሔራዊ እና የሃይማኖታዊ በዓላትን የደነገገ ነበር።

አዋጁ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ አንድ ጊዜ ብቻ ማሻሻያ ተደርጎበታል።

ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የድል ቀን ላይ ብቻ ማሻሻያ በማድረግ አዋጁን መተግበር ቀጥሏል። ይህ ማሻሻያ የድል (የአርበኞች) ቀንን ቀደም ሲል ይከበርበት ከነበረው መጋቢት 28 ወደ ሚያዝያ 27 ቀን የቀየረ ነው።