ፑቲን ከትራምፕ ጋር ባደረጉት የስልክ ልውውጥ የዩክሬን የኃይል ማመንጫን ላለመምታት ተስማሙ

ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በፍጥነት ተግባራዊ ይደረግ የተባለውን የተኩስ አቁም ስምምነት አልቀበልም ብለው ነገር ግን የዩክሬንን የኃይል ማመንጫዎች ላለመምታት ቃል ገቡ።

ፑቲን ይህ ያሉት ከአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ ጋር ካደረጉት የስልክ ልውውጥ በኋላ ነው።

የሩሲያው መሪ ለአንድ ወር የሚቆይ የተባለውን ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ውድቅ አድርገውታል። ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት በቅርቡ የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት በሳዑዲ አራቢያ ያረቀቁት ነው።

ፑቲን እንዳሉት ይህ ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም ሊሠራ የሚችለው የውጭ ኃይሎች ለዩክሬን የሚያደርጉት የመሣሪያ እና የመረጃ አቅርቦት ካቆሙ ብቻ ነው።

የዩክሬን አጋር የሆኑ አውሮፓውያኑ ሀገራት ከዚህ ቀደም ይህን የፑቲን ቅደመ ሁኔታ እንደማይቀበሉት አስታውቀው ነበር።

በሳዑዲ መዲና ጅዳ በዩክሬን ጉዳይ የሚደረገው ንግግር እንደሚቀጥል በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ ልዑክ የሆኑት ስቲቭ ዊትኮፍ ተናግረዋል።

ሩሲያ ከስድስት ወራት በፊት በዩክሬን ቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረውን የኩርስክ ግዛት በቅርቡ ባካሄደችው ዘመቻ ማስለቀቅ ችላለች።

ማክሰኞ ዕለት ትራምፕ እና ፑቲን ካደረጉት የስልክ ልውውጥ በኋላ አሜሪካ ባለፈው ሳምንት ስታሳይ የነበረውን አቋም የለወጠች ይመስላል። ነገር ግን ሁለቱ መሪዎች ጦርነቱን ለመግታት ተጨማሪ ንግግሮች እንደሚያሹ መስማማታቸው ተሰምቷል።

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጅዳ የተገኙት የአሜሪካ ልዑካን የዩክሬን ባለሥልጣናት "በፍጥነት ተግባራዊ የሚደረግ" ያሉትን የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈርሙ ማሳመናቸው ይታወሳል።

ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ለኦፊሴላዊ ጉብኝት ወደ ፊንላንድ መዲና ሄልሲንኪ ያቀኑ ሲሆን ዩክሬን የኃይል አማራጮችን ያካተተ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ተናግረው ነገር ግን ተጨማሪ መረጃዎች እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።

ዜሌንስኪ ከሰሞኑ በዩክሬን የድሮን ናዳ እያወረዱ ያሉት ፑቲን የተኩስ አቁም ማድረግ አይፈልጉም ሲሉ ወቅሰዋል።

ከሰሞኑ ሩሲያ ባካሄደችው የድሮን ጥቃት ዒላማ ከተደረጉት መካከል ሱሚ የሚገኝ ሆስፒታል እና በስሎቭያንስክ የሚገኙ የኃይል ማመንጫዎች ይገኙበታል።

"በሚያሳዝን ሁኔታ ዒላማ የተደረጉ ቦታዎች አሉ። በተለይ ደግሞ ለሰላማዊ ዜጋ ጥቅም ላይ የሚውሉ መሠረተ ልማቶች። ዛሬ ፑቲን የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደማይቀበሉት ተናግረዋል" ሲሉ ዜሌንስኪ በኤክስ ገፃቸው ፅፈዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ከፑቲን ጋር የነበራቸው የስልክ ልውውጥ "በጣም መልካም እና ውጤታማ" እንደነበር ፅፈው ለጊዜው የኃይል ማመንጫዎች ላይ ጥቃት እንዳይሰነዘር ከስምምነት እንደተደረሰ፤ በቀጣይ ደግሞ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ውይይት እንደሚቀጥል ፅፈዋል።

80 በመቶ የሚሆኑት የዩክሬን የኃይል ማመንጫ መሠረተ-ልማቶች በሩሲያ የቦምብ ጥቃቶች መውደማቸው ዜሌንስኪ ባለፈው መስከረም መናገራቸው ይታወሳል።