ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተቃጠሉ የሰው ልጅ አካላት እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ጫማዎች የተገኙበት የሜክሲኮ "የግድያ ካምፕ"
የተቃጠሉ አጥንቶች፣ ጫማዎች፣ ቦርሳዎች፣ ልብሶች እና የስንብት ደብዳቤዎች. . . አሰሳ ላይ የተሰማሩ ተሟጋቾች ከውንብድና ጋር በተያያዘ አመጽ የጠፉ ሰዎችን ሲያፈላልጉ የደረሱባቸው አስደንጋጭ ግኝቶች ናቸው።
"ጉዌሬሮስ ቡስካዶሬስ ዴ ኸሊስኮ" በመባል የሚታወቀው የአሳሾች ቡድን፤ በምዕራባዊ ሜክሲኮ ጓደላሃራ ከተባለች የገጠር ወንደር ወጣ ብሎ በሚገኘው ኢዛጊሬ የእርባታ ቦታ "ለምልመላ እና ግድያ" እንደሚውል የተነገረለትን ስፍራ በቅርቡ አግኝቷል።
ስፍራው፤ ከሜክሲኮ ግዙፍ እና ታዋቂ የእፅ አዘዋዋሪ ቡድኖች አንዱ የሆነው "ኸሊስኮ ኒው ጀነሬሽን ካርቴል" ጠንካራ ይዞታ ነው።
ቦታው ከመስከረም አንስቶ በሀገሪቱ ፌደራል እና የክልል ባለስልጣናት ቁጥጥር ስር ተደርጎ ምርመራ ሲከናወንበት ነበር። በስፍራው ላይ የሰው ልጅ አካላት ቅሪቶች መገኘት የጀመሩት ግን የአሰሳ ቡድን አባላቱ ፍለጋ ማሄድ ሲጀምሩ ነው።
"ጉዌሬሮስ ቡስካዶሬስ ዴ ኸሊስኮ" ቃል አቀባይ ኢንዲራ ነቫሮ፤ "[ከዚህ ቀደም] የአደንዛዥ እጽ ማከማቻ ወደሆኑ ቤቶች ገብተን እናውቃለን፤ ለስልጠና እና ለግድያ የሚውል ስፍራ ግን አናውቅም" ስትል ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግራለች።
እ.አ.አ በ2015 በሶኖራ ግዛት የጠፋውን ወንድሟን ሄሱስ ሄርናን ነቫሮ ስታፈላልግ የከረመችው ኢንዲራ ነቫሮ፤ "ስፍራውን ያገኘነው ብዛት ያላቸው ማንነታቸው ካልታወቁ ሰዎች የሚመጡ ጥሪዎች ስለደረሱን ነው። እናም በመቃብር ውስጥ የተቃጠሉ የሰው ልጅ አካላት ቅሪቶችን አገኘን" ብላለች።
የኸሊስኮ አቃቤ ህግ ቢሮ ለቢቢሲ እንደገለጸው፤ በስፍራው ላይ የአጽም ቅሪቶች የተገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት "የቃጠሎ ምልክት" ተገኝቶባቸዋል። የሟቾች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ግን እስካሁን አልታወቀም።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ጫማዎች፣ ልብሶች እና ቦርሳዎች መገኘት ግን ስፍራው በርካታ ግድያዎች የተፈጸሙበት ሊሆን ይችላል የሚል ፍርሃትን ፈጥሯል።
ግኝቱ የፈጠራቸው ጥያቄዎች
የኸሊስኮ ግዛት አቃቤ ህግ ሳልቫዶር ጎንዛሌዝ፤ የወንጀል እንቅስቃሴ ሪፖርቶች መምጣታቸውን ተከትሎ የብሔራዊ ዘብ አባላት መስከረም ላይ በስፍራው ላይ ጸረ-ወንጀል ኦፕሬሽን አካሂዷል። በዚህም አስር ሰዎች በቁጥጥር ስር ሲውሉ፤ ታግተው የነበሩ ሁለት ሰዎች ነጻ ወጥተዋል። ሌሎች ደግሞ ከባለስልጣናት ጋር ከተፈጠረ ግብግብ በኋላ ከአካባቢው ሸሽተዋል።
ምርመራውን ሲያካሂድ የነበረው ብሔራዊ ዘቡ፤ ሰፊ አሰሳ እንዲያካሂድ ምክንያት የሆነን አስከሬን ቢያገኘም በወቅቱ ሌሎች አስከሬኖች እንዳልተገኙ ጎንዛሌዝ ተናግረዋል። ተሟጋቾቹ ወደ ስፍራው መጥተው የራሳቸውን ፍለጋ እስከሚያከናውኑ ድረስም ጉዳዩ በዚህ መልኩ ቀጥሏል።
አቃቤ ህግ ጎንዛሌዝ፤ "የአሁኑን ግኝት ስንመለከት የተከናወነው ስራ በቂ እንዳልነበር [ግልጽ ሆኗል]። ይህንን ተከትሎም፤ በየትኛው ባለስልጣን ተፈጥሮ ሊሆን የሚችልን ጉድለት ለመለየት እና ኃላፊነቱን ለማሸከም ምርመራ ከፍተናል" ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ከተከናወነው የመነሻ ስራ አንስቶ ሌላ እንቅስቃሴ አለመደረጉን የሚናገሩት ጎንዛሌዝ፤ በተሟጋቾች የተገኙት የሰውነት አካል ቅሪቶች የቅርብ ጊዜ ተጎጂዎች ሊሆኑ የሚችሉበት እድል አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሼንባውም፤ የምርመራ ስራውን የሀገሪቱ ብሔራዊ አቃቤ ህግ እንዲይዘው አዝዘዋል።
አሰቃቂ ግኝት
ኢዛጊሬ የእርባታ ቦታ የሬክታንግል ቅርፅ ያለው መሬት ሲሆን ጥቂት ህንጻዎች ያሉት እና በግንብ የታጠረ ነው። ስፍራው፤ በቴውቺክላን ከተማ ውስጥ በሚገኘው የእርሻ መሬት መሃል ላይ የሚገኝ ነው።
አሳሾች እንደሚናገሩት ወደ ስፍራው ሲገቡ እንደ ጫማ፣ ልብስ እና ቦርሳዎች ያሉ የሰዎች እቃዎችን አግኘተዋል። ይህም በርካታ ሰዎች በስፍራው ብዙ ሰዎች ስለማለፋቸው እንዳመላከተ ገልጸዋል።
የቡድኑ ቃል አቀባይ ኢንዲራ ነቫሮ፤ "ከጅምሩ አንስቶ እጅግ ብዙ ልብሶችን አግኝተናል። ጫማዎችንም አግኝተናል። ሰዎች፤ እነዚህን ግኝቶች ከጥንት ጊዜ፣ ከጦርነት እና ከግድያ ስፍራዎች ፎቶዎች ጋር ሲያነጻጽሯቸው ስለነበረ ብዙ ሰው ጋር ደርሷል። የሰዎችን ህይወት እዚሁ ሲቀጥፉ ስለነበር ይህ ቦታ በትክክልም የግድያ፣ የምልመላ እና የድምሰሳ ስፍራ ነው" ስትል ከኤኤፍፒ ተናግራለች።
ቀጥሎም፤ የምልምሎች ሊሆኑ የሚችሉ ቅፅል ስሞችን የያዙ ማስወሻ ደብተሮችን እና ፎቶግራፎችን አግኝተዋል። 100 ገደማ የጥይት ቀለሃዎችን አግኝተዋል።
በተጨማሪም የአሰሳ ቡድኑ፤ "የእኔ ፍቅር፤ ምንአልባት አንድ ቀን ካልተመለስኩ፣ የምጠይቅሽ ብቸኛ ነገር ምን ያህል እንደምወድሽ እንድታስታውሺ ነው። እናም፤ ንዴቴ፣ ብስጭት እና ቅናቴ ሄዷል ብለሽ ተናገሪ" የሚል መልዕክት የተጻፈበት ደብዳቤ አግኝቷል።
ደብዳቤው ፊርማ ያረፈበት እንዲሁም የትውልድ ቀን እና ስፍራ የተጻፈበት ነው።
በኋላ ላይ የግዛቱ አቃቤ ህግ ቢሮ የደብዳቤው ጸሀፊ "በህይወት እንደሚገኝ" እና "ከጥቅምት 2024 ጀምሮ" ወደ ቤተሰቡ መመለሱን አስታውቋል።
ተሟጋቾቹ ከዚህ ቀደም ፍለጋ ካከናወኑባቸው ስፍራዎች ካገኙት ልምድ በመነሳት የሞቱ ሰዎችን የሚያሳይ ምልክት ለመፈለግ ቁፋሮ ጀምረዋል። በዚህ ቁፋሮም የአጽም ቅሪቶች ያገኙ ሲሆን የተወሰኑት ለእሳት ተጋልጠው እንደነበር የሚያሳይ ምልክት ያለባቸው ናቸው።
ነቫሮ እንደምትገልጸው፤ ይህ ስፍራ ከዚህ በፊት አይተውት በማያውቁት ሁኔታ "ለምልመላ እና ግድያ" ይውል ነበር።
የኸሊስኮ ግዛት አቃቤ ህግ ቢሮ ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ በስፍራው ላይ ተገድለዋል የተባሉ ሰዎች ቁጥር እስካሁን አልታወቀም። የምን ያህል ሰዎች አጽም ቅሪት እንደተገኘ ለማረጋገጥ የፎረንሲክ ምርመራ ያስፈልጋል።
ይሁን እንጂ፤ "ስድስት ቦታዎች የተከፋፈሉ አጥንቶች በአራት ጉድጓዶች ውስጥ" መገኘታቸውን ባለስልጣናት አረጋግጠዋል።
በፍለጋው የተገኙት የግል ንብረቶች "በህገ ወጥ እንቅስቃሴ" የተሳተፉ ሰዎች እንዲሁም በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ሰለባ ሆኑ ተጎጂዎች ሊሆኑ ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው።
የምልመላ ስፍራ
ተሟጋቾች፤ ኢዛጊሬ የእርባታ ቦታ የተደራጀ ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎችን ለመመልመል ያገለግል እንደነበር የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሳይተዋል።
ጉዌሬሮስ ቡስካዶሬስ ዴ ኸሊስኮ እና ሌሎች ድርጅቶች፤ ሜክሲኮ ውስጥ ወጣቶች እንደ "ኸሊስኮ ኒው ጀነሬሽን ካርቴል" ባሉ እፅ አዘዋዋሪዎች በሚቀርብላቸው አጓጊ ደመወዝ ያለው አሳሳች የስራ እድል ተታልለው ወደ እንደዚህ አይነት ስፍራዎች ሲወሰዱ እንደነበር ለበርካታ ዓመታት ሲጠቁሙ ቆይተዋል።
ቃል አቀባይ ነርቫሮን ያነጋገረ አንድ ተጎጂ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ ስፍራው ከተወሰዱ በኋላ ስቃይ እና "ተቀጣሪዎች" አንዳቸው አንዳቸውን እንዲጎዱ ማድረግ ጨምሮ ለተለያዩ ኢሰብአዊ ለሆኑ ድርጊቶች ተጋልጠዋል።
ባለስልጣናቱ ይህንን ማረጋገጥም ሆነ ማስተባበል እንደማይችሉ ተናግረዋል። ነገር ግን በስፍራው ላይ "የታክቲክ ማሰልጠኛ እና የአካል መገንቢያ ስፍራዎች" እንዳሉ እንዲሁም መሳሪያዎች፣ ሰደርያዎች እና የጥይት ማህደሮች መገኘታቸውን ገልጸዋል።
ምርመራውን በተመለከተ "ግልጽነት" እንደሚኖር የሚናገሩት አቃቤ ህግ ጎንዛሌዝ፤ የእርሱ ቢሮ ተጎጂዎች በዘመዶቻቸው እንዲለዩ መረጃዎችን እና በስፍራው ላይ የተገኙ እቃዎች ፎቶግፍ እንዲለጠፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
የሜክሲኮ አቃቤ ህግ አሌሃንድሮ ገርትዝ እንደሚገልጹት የአካባቢው ባለስልጣናት በተሟጋቾቹ የተገኙትን ማስረጃዎች አላገኙትም የሚለው ሃሳብ የሚያስኬድ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
"ይህ አይነት መልክ ያለው ሁኔታ በከተማው እና በግዛቱ ባለስልጣናት አይታወቅም የሚለው የሚታመን አይደለም" ብለዋል።
የኸሊስኮ ግዛት ገዢ ፓብሎ ሌሙስ ለዚህ በሰጡት ምላሽ፤ "ማንም እጁን አይታጠብም። ኃላፊነቶችን እንፈታለን፣ ግልጽ እናደርጋለን። ሜክሲኮ ውስጥ ያለው የሰዎች መጥፋት ቀውስ ሁሉም መንግስታት ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆን አለበት" ብለዋል።
ኤል ዩኒቨርሳል የተባለ ጋዜጣ፤ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የሜክሲኮ ባለስልጣናት የተለያዩ የወንጀል ድርጅቶች ሰዎችን ለመግደል እና አካላቸውን ለማስወገድ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ቢያንስ አምስት በተለያዩ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ ተመሳሳይ ስፍራዎችን አግኝተው እንደነበር ዘግቧል።
እ.አ.አ በ2009፤ ቲሁአና ካርቴል የተባለው የእፅ አዘዋዋሪ ቡድን መሪዎች አንዱ የሆነው ሳንቲያጎ ሜዛ ሎፔዝ፤ በቲሁአና ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ስፍራ ላይ የ300 ገደማ ሰዎች አስከሬን "ኮስቲክ ሶዳ" በመጠቀም እንዲሟሟ መደረጉን መናዘዙ መላ ሀገሪቱን አስደንግጦ ነበር። እንደ ጋዜጣው ዘገባ፤ ወንጀሉ የተፈጸመው በዘጠኝ ዓመታት ውስጥ ነው።
ለዓመታት በዚህ አይነቱ ቀውስ ስትፈተን በቆየችው ሜክሲኮ፤ ከ110 ሺህ በላይ ሰዎች እንደተጠፉ ተመዝግቧል።
የኸሊስኮ ግዛት 15 ሺህ የጠፉ ሰዎችን በመመዝገብ በዚህ ክስተት ከሀገሪቱ በቀዳሚነት መቀመጡን የግዛቱ መንግሥት ይፋዊ መረጃ ያሳያል።
ፍለጋውን ያካሄዱት ተሟጋቾች ወዳጆቻቸውን የሚመለከቱ ማስረጃዎችን ለማግኘት ሲሉ ከኢዛጊሬ የእርባታ ስፍራ የተገኙ መረጃ እና ፎቶዎችን እያገላበጡ ነው።
"እነዚህ ምርመራዎች መካሄድ በሚገባቸው መንገድ እንዲካሄዱ እንጠይቃለን። ይህ ክስተት አስደንግጦናል፤ እኛን ብቻ ሳይሆን መላው ዓለም አስደንግጠወል ብዬ አስባለሁ" ስትል ነቫሮ ተናግራለች።