በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚገኙ የምዕራባውያን ወታደራዊ ካምፖች ሲዘጉ ሥራ አጥ የሆኑት አፍሪካውያን

በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ የሚገኙ የምዕራባውያን ወታደራዊ ሠፈሮች ሲዘጉ ቢያንስ 2,000 ሲቪል ሠራተኞች ሥራ አጥ መሆናቸው ይነገራል።

ለብዙ አሥርት ዓመታት በወታደራዊ ካምፖች ውስጥ በተለያየ ሙያ ሲሠሩ የነበሩ በርካቶች ሕይወታቸው ወደ አልጠበቁት አቅጣጫ መቀየሩን በምሬት ይገልጻሉ።

እነዚህ ሠዎች ለረዥም ዓመታት ይሰሩበት ከነበረው ወታደራዊ ጦር ሠፈር ሲሰናበቱ ሌላ ሥራ ለማግኘት፣ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ለመቀጠር መቸገራቸውን ይናገራሉ።

በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ማሊ፣ቡርኪናፋሶ፣ኒጀር፣ቻድ፣ሴኔጋል እና ኮትዲቯር የፈረንሳይ ጦር ሰፈሮች ተዘግተው ወታደሮቻቸው ለቅቀው እንዲወጡ ሲወሰን በሺህዎች የሚቆጠሩ የአገሬው ዜጎች ሥራ አልባ ሆነዋል።

ወታደራዊ ካምፖቿን የዘጋችው ፈረንሳይ ብቻ አይደለችም።

በኒጀር የሚገኘውን የአሜሪካ ወታደራዊ ጦር ሰፈር እና የተባበሩት መንግሥታት ሁለገብ የተቀናጀ ተልዕኮ ማዕከል (MINUSMA) ከተዘጉት መካከል ይገኙበታል።

ቢቢሲ ያገኘው መረጃ በማሊ ብቻ 859 የሚጠጉ ሠራተኞች በጦር ሠፈሩ መዘጋት ምክንያት ሥራቸውን ማጣታቸውን ያሳያል።

በቻድ ደግሞ 400፣ በኒጀር 350፣ በሴኔጋል እና በኮትዲቯር 162 እና 280 ሠራተኞች ሥራ አጥ ሆነዋል።

በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ እና በቡርኪናፋሶ በእነዚህ ወታደራዊ ካምፖች መዘጋት ምክንያት ምን ያህል ሠራተኞች እንደተቀነሱ የሚያሳይ ቁጥር እስካሁን አልቀረበም።

ነገር ግን የውጪ ኃይሎች እየለቀቁ ሲሄዱ ከእነሱ ጋር ሲሰሩ የነበሩ የአገር ውስጥ ሠራተኞች ሙያቸውን እና ብቃታቸውን የሚጠቀሙበት ቦታ ማጣታቸው በሁሉም ቦታ ታይቷል።

እነዚህ ግለሰቦች ከራሳቸው አልፎ ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደርና ልጆቻቸውን ለማስተማር መቸገራቸውን ይገልጻሉ።

ሴኔጋላዊው ዲጂብሪል ንዲዬ ለቢቢሲ እንደተናገረው ሕይወቱ ያላሰበው መስመር ውስጥ የገባው 26 ዓመታት ያገለገለበት ወታደራዊ ካምፕ፣ፍሬድሪክ ጊይል፣ ተዘግቶ እርሱ እና 162 ሠራተኞች አውላላ ሜዳ ላይ ከተበተኑ በኋላ ነው።

ለወላጆቹ የበኩር ልጅ የሆነው፣ የአራት ልጆች አባቱ ንዲዬ በኮምፒዩተር እና በኔትዎርክ ጥገና ቴክኒሻንነት ሲሰራ የነበረ ሲሆን፣ የእርሱ እና ያስተዳድራቸው የነበሩ 21 ቤተሰቦቹ ችግር ላይ ወድቀዋል።

"ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ይማሩ የነበሩት ቤተሰቦቼ አደጋ ላይ ወድቀዋል" ሲል ንዲዬ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ከወታደራዊ ካምፖቹ መዘጋት ጋር በተያያዘ የተቀነሱት አብዛኛዎቹ ሠራተኞች የአይቲ ስፔሻሊስቶች፣ የቴሌኮም መሐንዲሶች፣ የሂሳብ ባለሙያዎች፣ መካኒኮች እና የምግብ ዝግጅት ባለሙያዎች ናቸው።

"በመንግሥት መሥርያ ቤቶች ውስጥ ተቀጥሮ ለመስራት የሚያስፈልጉን ነገሮች ሁሉ አሉን" ይላል ንዲዬ።

274 ሠራተኞች ሥራ አጥ በሆኑበት ኒጀር ደግሞ ከ20 ዓመታት በላይ በኒያሚ በሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ ቤዝ 101፣ በምግብ አዘጋጅነት የሰራው አቡባካር ኦስማን በተስፋ መቁረጥ ውስጥ መሆኑን ይናገራል።

አቡባካር የቤት ኪራይ ከከፈለ ሰባት ወር አልፎታል።

ሥራ አጥ በመሆኑ ወርሃዊ ደመወዙ መቋረጥ ብቻ ሳይሆን፣ የስንብት ጥቅማ ጥቅሙ እስካሁን ስላልተከፈለው መቸገሩን አልሸሸገም።

በኒያሚ በሚገኘው የፈረንሳይ የጦር ሰፈር የሂሳብ ባለሙያ የነበረው ለሪሳ ሳዲካን ሰሎም ሕይወቱ ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነው።

ሰሎም ለቢቢሲ ሲያስረዳ "ሁኔታው ለእኛ በጣም የተወሳሰበ ነው፤ ምክንያቱም ሥራ ማግኘት ለእኛ ቀላል አይደለም። አሁን ባለው ሁኔታ ለፈረንሣይ ጦር ኃይሎች ስናገለግል ቆይተን ሥራ ማግኘት አይታሰብም" ብሏል።

እንደ እሱ ገለጻ ቀጣሪዎች ለፈረንሣይ ጦር እንደሠሩ ሲያውቁ፣ ለመቅጠር ዳተኛ ይሆናሉ።

በቻድ 400 የሚጠጉ የፈረንሳይ ወታደራዊ ካምፖች የቀድሞ ሠራተኞች ከሥራቸው ሲሰናበቱ ፍርሃት አርዷቸዋል።

ቅዳሜ የካቲት 8 በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም አንዳንድ የቀድሞ ሠራተኞች በቂ ማካካሻ እና በቻድ የመንግሥት የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር ውስጥ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ በቂ ጥረት አለመኖሩን ተናግረዋል ።

እነዚህ ሰዎች ምን ይሆናሉ?

አብዛኛዎቹ እነዚህ ከሥራቸው የተሰናበቱ ግለሰቦች የሚገኙባቸው አገራት መንግሥታት ግለሰቦቹን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ስለመቀላቀል ያላቸውን ዕቅድ በይፋ አልገለፁም።

የፈረንሣይ ጦር በዚህ የበጋ ወቅት ከሥራ ለሚባረሩ 162 ሠራተኞች በአገር ውስጥ ኩባንያዎች ውስጥ ዕድሎችን ለማመቻቸት የሚያስችል አውደ ርዕይ አዘጋጅቷል።

በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ሰባ የሚሆኑ ኩባንያዎች የሚሳተፉ ሲሆን 300 ሥራዎችን ክፍት አድርገዋል።

በሴኔጋል የፈረንሳይ ጦር አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል አቬስ አውኒስ በተጨማሪም በሚቀጥለው ሰኔ ወር ሥራቸውን የሚያጡ 162 የሴኔጋል ሠራተኞችን በሚመለከት ማኅበራዊ ዕቅድ ማውጣታቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለእነዚህ ሠራተኞች የ1.5 ሚሊዮን ዩሮ ካሳ ይከፈላል ብለዋል።

ጄነራል አውኒስ የራሳቸውን ንግድ ለመጀመር እንዲሁም ሥራ ፈጣሪ ለመሆን ለሚፈልጉ አውደ ጥናቶች እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል።

ነገር ግን ንዲዬ "ሠራተኞች በመንግሥት ባለቤትነት በተያዙ ኩባንያዎች ወይም በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ እንዲሰማሩ እንጠብቃለንለ ምክንያቱም ልምድ ያላቸው ብቁ ሰራተኞች ናቸው" ይላል።

በኮትዲቯር አንድ የመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ የሚሰሩ ግለሰብ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከወታደራዊ ካምፖቹ ሥራቸውን የሚያጡ 280 ሲቪል ሠራተኞችን የመቅጠር እቅድ አለ።

ስሙን ለመግለጽ ፈቃደኛ ያልሆነ ሌላ ወታደራዊ ምንጭ ደግሞ "ከወታደራዊ ካምፖቹ ሠራተኞቹን የመቀነስ ዕቅድ በሂደት ላይ ነው። የፈረንሣይ እና አይቮሪኮስት ባለስልጣናት በዚህ ላይ እየሰሩ ነው። የተወሰኑ ሲቪል ሠራተኞችን ዳግም መዋቅር በመስራት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በተለይም በመከላከያ ሚኒስቴር ለማካተት በጥምረት እየተጠና ነው" ብሏል።

ቢቢሲ በኒጀር ከሚገኙ ባለስልጣናት፣ ከቻድ ሲቪል ሰርቪስና ከመካከለኛው አፍሪካ ባለሥልጣናት ይፋዊ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በማሊ እና ቡርኪናፋሶም ቢሆን እስካሁን ድረስ ከሥራቸው የተቀነሱ ግለሰቦችን መልሶ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ስለ ማካተት የታሰበ ነገር ስለመኖሩ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።