የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተወያዩ

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ "የአፍሪካ ቀንድ ሰላም" እና "ቀጣናዊ መረጋጋትን" በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን የዋሽንግተን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታወቀ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው አጭር መገለጫ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውይይት የተደረገው ረቡዕ ኅዳር 24/2018 ዓ.ም. መሆኑን አመልክቷል።

ይህ የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ውይይት በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ ነው።

በውይይቱ ላይ ሁለቱ ባለሥልጣናት፤ ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ መረጋጋት ያላቸውን ቁርጠኝነት እና ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም መሠረት በመጣል ዙሪያ መነጋገራቸውን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መግለጫ አሳውቋል። የኢትዮጵያን ውስጣዊ ጉዳዮች በተመለከተ ንግግር ስለማድረጋቸው በመግለጫው ላይ አልተጠቀሰም።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮ መካከል የተደረገውን ውይይት በተመለከተ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ምክትል ቃል አቀባይ በኩል የተላለፈው መልዕክት በአንድ አረፍተ ነገር የተጠቃለለ እና ዝርዝር ጉዳዮችን ያልያዘ ነው።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረገውን ንግግር በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽሕፈት ቤት በኩል እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቀጣናዊ የሰላም ጉዳዮችን በተመለከተ ውይይት ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከአራት ወራት በፊት ባለፈው ዓመት ነሐሴ አጋማሽ ላይም ተመሳሳይ ውይይት አድርገው ነበር።

በወቅቱ በሁለቱ አገራት እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ተነስተው የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እንዲሁም የምጣኔ ሃብት ዕድገት ላይ መነጋገራቸው መገለጹ ይታወሳል።

ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም. በነበረው ውይይት ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በቀጣናው የውይይትን እና የመረጋጋት አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማንሳታቸውን መሥሪያ ቤታቸው አስታውቆ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የአፍሪካ፣ የአረብ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ማሳድ ቡሎስ ወደ አዲስ አበባ አቅንተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ተወያይተው ነበር።

በወቅቱ አማካሪው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ወይይት ኢትዮጵያ ከጎረነቤቶቿ ጋር ስላላት ግንኙነት እና በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት በማምጣት በኩል ስላላት ሚና ትኩረት ሰጥተው መነጋገራቸውን እንዲሁም በሁለቱ አገራት መካከል ስለሚኖር የንግድ ዕድሎች መነሳታቸውን በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረው ነበር።

ከአንድ ሳምንት በፊት ደግሞ የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ አዘዥ ጄነራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰን በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው ከአገሪቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተዘግቧል።

በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖቹ መካከል በተደረገው በዚህ ውይይት ላይ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋትን በመፍጠር በኩል የሁለቱ አገራት ትብብር እና ሚና መነሳቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።