የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ወሳኝ ርዕስ መሆኑን አማካሪያቸው ተናገሩ

የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "በጣም አስፈላጊ እና ወሳኝ" መሆኑን ከፍተኛ አማካሪያቸው ማሳድ ቡሎስ ተናገሩ።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የአፍሪካ፣ የአረብ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ከፍተኛ አማካሪው ለሳዑዲው አል አረቢያ እንደተናገሩት፤ ትራምፕ ከመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው አንስቶ በግድቡ ዙሪያ የበኩላቸውን ሲያከናውኑ ነበር።

ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከዓባይ ወንዝ በምታገኘው የውሃ መጠን ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል በሚል ከሱዳን ጋር በመሆን በግድቡ የውሃ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ አስገዳጅ ስምምነት እንዲደረስ ስትጠይቅ የቆየችው ግብፅ፤ በተደጋጋሚ በጉዳዩ ላይ አሜሪካ ጣልቃ እንድትገባ ስትጠይቅ ቆይታለች።

ፕሬዝዳንት ትራምፕም በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በማቀረራብ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ከመሞከራቸው ባሻገር በተለያዩ ጊዜያት ግድቡን በተመለከተ አነጋጋሪ አስተያየት በመስጠት ይታወቃል።

የፕሬዝዳንቱ አማካሪ፤ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የትራምፕ ትኩረት እንዳለው በመጥቀስ ወሳኝ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።

"በመጀመሪው የፕሬዝዳንትንት ዘመናቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከስምምነት እንዲደረስ ጥረት ማድረጋቸው ይታወቃል" በማለት በአገራቱ መካከል ቴክኒካዊ ስምምነት ሊፈረም ተቃርቦ በተወሰኑ ችግሮች ምክንያት መደናቀፉን አስታውሰዋል።

በወቅቱ በአሜሪካ እና በዓለም ባንክ አማካይነት በተደረገው ድርድር የተዘጋጀው ሰነድ ይፈረማል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ኢትዮጵያ የቀረበው ሰነድ ጥቅሟን አሳልፎ የሚሰጥ መሆኑን በመጥቀስ ከስምምነቱ ወጥታለች።

በዚህ የተቆጡት ፕሬዝዳንት ትራምፕ አገራቸው ለኢትዮጵያ ትሰጥ ከነበረው ድጋፍ ወደ አምስት መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚደርሰው እንዲቋረጥ አድርገው ነበር።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በውሃ ሙሌት እና በግድቡ አስተዳደር ላይ በሦስቱ አገራት ባለሥልጣናት መካከል ከመቋጫ ያልደረሱ ድርድሮች ሲካሄዱ እንደነበር ይታወሳል።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ ከአንድ ወር በፊት ወደ አካባቢው በመምጣት ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳን እና ከግብፅ ባለሥልጣናት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው ነበር።

ቡሎስ ሰኞ ዕለት ለአል አረቢያ፤ ሁለቱ አገራት "ወደ ግጭት ማምራት የሌለበት ታሪካዊ ትስስር አላቸው" በማለት አሁንም አሜሪካ በአዲስ አበባ እና በካይሮ መካከል ሰላማዊ ትብብር እንዲኖር እንደምታበረታታ ጠቅሰዋል።

ቡሎስ "ጉዳዩ በግልጽ ቴክኒካዊ ከመሆኑ አንጻር በተለይ በቴክኒካዊው ነጥብ ሁሉንም የሚያስማማ መፍትሄ ለማግኘት እየሠራን ነው" ሲሉ ለአል አረቢያ ተናግረዋል።

በሕዳሴ ግድብ ምክንያት በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብፅ መካከል የተከሰተውን ውዝግብ "የሞት እና የሕይወት" ጉዳይ በማለት የገለጹት ከገፍተኛ አማካሪው፤ የግድቡ ግንባታ ተጠናቅቆ ከተመረቀ በኋላ "አሁን ተጨባጭ እውነታ ሆኗል" በማለት "መፍትሄውም ከዚሁ እውነታ በመነሳት መገኘት አለበት" ብለዋል።

ከ14 ዓመታት በላይ በግናባታ ላይ የነበረው እና ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ ግንባታው ተጠናቅቆ የተመረቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ በአፍሪካ ትልቁ ግድብ ነው።

በግብፁ ፕሬዝዳንት እና በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር መካከል ንግግር እንዲካሄድ ትራምፕ ጥረት ያደርጉ እንደሆነ በአል አረቢያ የተጠየቁት ቡሎስ፤ "እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሁለቱን [መሪዎች] አብረው እናያቸው ይሆናል። ለዚያም እየሠራን ነው" በማለት መልሰዋል።

ጨምረውም እንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት "በአፍሪካ ማዕቀፍ፣ ምናልባትም ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በሚዛመዱ ዝግጅቶች ላይ ሊካሄድ ይችላል" በማለት አሜሪካ ቀውሱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረጉ ማንኛውንም ጥረቶች እንድምትደግፍ ገልጸዋል።

የሕዳሴው ግድብ ውዝግብ ለኢትዮጵያ፣ ለግብፅ እና ለሱዳን "የሞት ሽረት" ጉዳይ በመሆኑ ሰላማዊ መፍትሄ ያስፈልገዋል ብለዋል።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪው ማሳድ ቡሎስ ለሳዑዲው አል አረቢያ እንደተናገሩት፤ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት በአገራቱ መካከል የተከሰተውን ውዝግብ ከፖለቲካዊ ይልቅ በቴክኒካዊ መንገድ ለመፍታት አሜሪካ ፍላጎት እንዳለት አመልክተዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በሚካሄድባቸው ዓመታት በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ላይ ክስ በማቅረብ ጉዳዩን ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት፣ለአፍሪካ ኅብረት እና ለአረብ ሊግ ያቀረበችው ግብፅ የግንባታውን መጠናቀቅ ተከትሎ ተመሳሳይ ክስ ለመንግሥታቱ ድርጅት አቅርባለች።

ከቀናት በፊት የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ ከኢትዮጵያ ግድብ አንጻር የአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም አና የውሃ ደኅንነቷን ለማስጠበቅ አስፈላጊ የሆኑ ሁሉንም እርምጃዎች እንደሚወስዱ ተናግረው ነበር።

ለዚህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር ኢትዮጵያ በሰጠችው ምላሽ፤ ግብፅ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ እያካሄደች እንደሆነ እና የዓባይ ወንዝን በበላይነት ለመቆጣጠር እየሞከረች ነው በሚል የቀረበባትን ክስ አጣጥላለች።

ኢትዮጵያ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ በማውጣት የገነባችው ግዙፉ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃን የማያዝ አቅም አለው።

በዓለማችን በርዝመቱ የሚታወቀው የዓባይ ወንዝ ከ85 በመቶ በላይ ውሃውን የሚያገኘው ከኢትዮጵያ ሲሆን፣ የወንዙን አብዛኛውን ውሃ የምትጠቀመው ግብፅ በኢትዮጵያ የተገነባው ግድብ በበላይነት ስትጠቀምበት የነበረውን የውሃ መጠን ያሳጣኛል የሚል ስጋት ፈጥሮባታል።

ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመው እና አብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት በመጥቀስ፤ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት አላት በማለት ኢትዮጵያ ይህ ሁኔታ መለወጥ እንዳለበት ስትከራከር ቆይታለች።

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እንደምትሻ ገልጻለች።

በተጨማሪም የሕዳሴ ግድቡ የግብፅ የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ እንደማይጥል በተደጋጋሚ ገልጻለች።