ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ከኔቶ ዋና ፀሐፊ ጋር ስለ ግብፅ እና [ሕዳሴ] ግድብ ምን አሉ?
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ በዩክሬን ግጭት ላይ በ50 ቀናት ስምምነት ላይ ካልደረሰች ማዕቀብ እንደሚጣልባት ባስፈራሩበት ንግግራቸው፤ የ[ሕዳሴ] ግድብን አገራቸው "በገንዘብ ደግፋለች" እንዲሁም ግድቡ "ወደ ናይል የሚሄደውን ውሃ የሚዘጋ" ሲሉ አወዛጋቢ ንግግሮችን አድርገዋል።
ትራምፕ ሰኞ፣ ሐምሌ 7/2017 ዓ.ም. ከኔቶ (የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት) ዋና ፀሐፊ ማርክ ሩቴ ጋር በዋይት ሐውስ ባደረጉት ውይይት ግብፅን እንዲሁም [የሕዳሴ] ግድብን አንስተው ተወያይተዋል።
በዚህ ንግግራቸው የኢትዮጵያን ስም ያልጠሩ ሲሆን "የግብፅ ጎረቤት፤ ጥሩ ጎረቤት" ሲሉ ነው የጠሯት።
ይህችን ጎረቤት ሲሉ የጠሯትን ኢትዮጵያን "ጓደኞቼ ናቸው" ሲሉም ትራምፕ ጠቅሰዋል።
"ከግብፅ እና ከአጎራባቿ፣ ጥሩ ከሆነችው ጎረቤቷ ጋር በተያያዘ ሠርተናል" ብለዋል።
"ጓደኞቼ ናቸው፤ ነገር ግን ናይል ተብሎ ወደሚጠራው ወንዝ የሚሄደውን ውሃ የሚዘጋ ግድብ ገነቡ" ብለዋል።
ትራምፕ በስም ያልጠሩት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ፣ ግብፅ በተደጋጋሚ ከናይል ወንዝ በምታገኘው የውሃ መጠን ላይ አደጋ የጋረጠ ስትል በተደጋጋሚ ክስ የምታቀርብበት ነው።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ መስከረም ወር ላይ ይመረቃል ብለዋል።
በግድቡ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ሕጋዊ እና አስገዳጅ ሦስትዮሽ ስምምነት ካልተፈረመ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባትም ስትወተውት የቆየችው ግብፅ ከሰሞኑም ይህንኑ በመድገም አስጠንቅቃለች።
በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው ግብፅ "የሕዳሴ ግድብን ልታፈነዳ ትችላለች" በሚል አወዛጋቢ ንግግር የተናገሩት ትራምፕ፤ በአሁኑም ለግብፅ ወገንተኝነታቸውን በግልጽ ባንጸባረቀ መልኩ ንግግር ከማድረግ በተጨማሪም አንዳንድ ንግግራቸውም አሳሳችና ግራ ያጋባ ሆኗል።
"የሕዳሴ ግድብ ወደ ናይል የሚሄደውን ውሃ የሚዘጋ ነው" የሚለው ንግግራቸው ከግብፅ በኩል እንኳን ውሃውን ይቀንሰዋል እንጂ "ይዘጋዋል" ወይም ናይልን ያደርቀዋል በሚል የሚቀርብ አይደለም።
ትራምፕ አክለውም "እኔ ግብፅን ብሆን በናይል ወንዝ ውስጥ ውሃ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ። እሱ ላይ እየሠራን ነው። ችግሩ መፍትሄ ያገኛል" ብለዋል።
ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመውና፣ የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት ሙጥኝ ብላ ታሪካዊ ተጠቃሚነት በሚል መርኅ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ተናግራለች።
ስምምነቱ ኢትዮጵያን ያላካተተ ከመሆኑ በተጨማሪ ግብፅ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንዲሁም ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ እንድታገኝ እና 86 በመቶ የናይልን ውሃ የምትገብረውን ኢትዮጵያ ያለ ውሃ የሚያስቀር አግላይ እና ኢፍትሃዊ እንደሆነም ይጠቀሳል።
በየዓመቱ ከሚፈሰው 84 ቢሊዮን ኩየቢክ ውሃ 12 በመቶው በትነት የሚያልቅ ሲሆን፣ ይህ ስምምነት በዋነኝነት ግብፅን ትገዛ የነበረችውን ብሪታንያን ለጥጥ ምርቷ በዋነኝነት ተጠቃሚ አድርጓታል።
ትራምፕ በዚህ ንግግራቸው "በናይል ወንዝ ውሃ እንዲኖር እየሠራን ነው" ያሉ ቢሆንም ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ በአውሮፓውያኑ 1971 በገነባችው እና በአፍሪካ ትልቁ በሚባለው አስዋን ግድብ 2100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ታመነጫለች።
ግብፅ ትራምፕ እንደሚሉት "በናይል ወንዝ ውሃ" ስለሌላት ወይም ደርቆ ሳይሆነ ድርሻዬ የምትለው 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንዳይቀንስ ነው እየጠየቀች ያለችው።
ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እና ግንባታው የግብፅ የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ እንደማይጋርጥ ስታስታውቅ ቆይታለች።
የአሜሪካው መሪ መፍትሄ ስላሉትም ጉዳይ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም።
ግድቡን በሚመለከት በተከታታይ ሲካሄዱ የነበሩ የሦስትዮሽ ድርድሮች አንዱ ወገን ሌላኛውን ለድርድሩ አለመሳካት ተጠያቂ በማድረግ ያለውጤት መበተናቸው ይታወሳል።
ትራምፕ በዚህ ንግግራቸው አንድም ጊዜ የኢትዮጵያን ስም ያልጠቀሱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ለማለትም "ከግብፅ ትንሽ ወጣ ብሎ" የሚል አገላለጽን መርጠዋል።
"ከግብፅ ትንሽ ወጣ ብሎ በዓለም ላይ ካሉ ትልልቅ ግድቦች አንዱን ገነቡ። ስለዚህ ጉዳይ ታውቃላችሁ። ይህ ትልቅ ችግር ሆኗል" ብለዋል።
ትራምፕ ይህ ትልቅ ችግር የሆነው ለማን እንደሆነ ከኔቶ ዋና ፀሐፊ ጋር በነበራቸው ውይይት ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጡም።
አክለውም "አላውቅም። አሜሪካ ለግድቡ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገች ይመስለኛል" ብለዋል።
ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም ለሕዳሴ ግድቡ የገንዘብ ድጋፍ እንዳደረጉ የገለጹት፣ ከዚህ ቀደምም እንዲሁ ከአንድ ወር በፊት አገራቸው ግድቡን በገንዘብ እንደረዳች እና የናይል ፍሰትን ይቀንሰዋል ሲሉ የተሳሳተ መረጃ ሰጥተዋል።
አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ የተበጀተለት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ የተገነባው ሕዝቡ ባወጣው ገንዘብ እና አገር ውስጥ ባለ ሃብት ሲሆን ይህም በተደጋጋሚ የተገለጸ ነው።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የትራምፕን ይህንን የገንዘብ ድጋፍን አስመልክቶ በይፋ ትክክል እንዳልሆነ እስካሁን የገለጹት ነገር የለም።
ትራምፕ በዚህ ንግግራቸው ናይል ለግብፅ "ሕይወት ነው" ያሉ ሲሆን፣ የናይል መነሻ የሆነችው እና የመጀመሪያዋን ግድብ በናይል ላይ የሠራችውን ኢትዮጵያን አልጠቀሱም።
"ግድቡን ከመገንባታቸው በፊት ይህንን ችግር ለምን እንዳልፈቱት አላውቅም፤ ነገር ግን ናይል ውሃ ሲኖረው ጥሩ ነው። አስፈላጊ የገቢ ምንጭ ነው፤ የግብፅ ሕይወት ነው እና ያንን መንጠቅ አስገራሚ ነው። ይህ በፍጥነት የምንፈታው ይመስለኛል" ብለዋል።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ግብፅ እና ኢትዮጵያ "በግዙፉ ግድብ ምክንያት ግጭት ውስጥ" እንደነበሩና በእሳቸው ጣልቃ ገብነት ምክንያት ሰላም መምጣቱን ጠቅሰዋል።
ሆኖም ትራምፕ በ2013 ዓ.ም. በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ማጠናቀቂያ ወራት ላይ ግብፅ ግድቡን "ልታፈነዳ ትችላለች" የሚል ንግግር ማድረጋቸው በርካቶችን ያስቆጣ ሲሆን ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የትራምፕ ንግግር የቆጠረው "በሥልጣን ላይ ባለ" የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንደተደረገ "የጦርነት ቅስቀሳ" ነበር።
ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዳሴው ግድብ ሙሌትን ማከናወኗም ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር እርምጃ ያስከተለ ጉዳይ ነበር።
አሜሪካ ሙሌቱ ተከናወነው ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር ስምምነት ሳይደረስ መሆኑን በመግለጽ ለኢትዮጵያ ልትሰጥ የነበረው እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ እርዳታ ለማቋረጥ እንደወሰነች ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቦ ነበር።
በትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና ግብፅ ሲደረግ የነበረውን የሦስትዮሽ ድርድር ወደ ዋሽንግተን መወሰዱ ይታወሳል።
የሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮች እንዲሁም የሕግ እና የውሃ ጉዳይ የቴክኒክ ባለሞያዎች በዋሽንግተን ዲሲ ሲደራደሩ በነበረበት ወቅት በዓመታት የተራዘመ ድርቅ እንዲሁም በተራዘመ ዓመታት አነስተኛ የውሃ ፍሰት ላይም መሠረታዊ መግባባት ተደርሷል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ያለምንም ውጤት መቋረጡ ይታወሳል።
በወቅቱም ግብፅ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቴን ይቀንሰዋል እንዲሁም ለእርሻ የሚያስፈልገኝ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በየዓመቱ ይገባኛል ስትል የቆየች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በበኩሏ 31 ቢሊዮን ኪዩቡክ ውሃ በዓመት ለመልቀቅ ሃሳብ አቅርባ ነበር። ነገር ግን አሜሪካ በበኩሏ 37 ቢሊዮን ኪዩብክ ሜትር እንዲለቀቅ መጠየቋ ተነግሮ ነበር።
ኢትዮጵያ ወንዙ በግድቡ ስፍራ እንደሚኖረው ዓመታዊ የፍሰት መጠን ከ4 አስከ 7 ዓመታትን በሚወስድ ጊዜ የሙሌት ደረጃ ግድቡን የመሙላት ዕቅድን ብታቀርብም ግብፅ በበኩሏ ጥቅሜን የሚጋፋ ነው በማለት ከ12 እስከ 21 ዓመታት መውሰድ አለበት ብላለች።
ኢትዮጵያ ዋሽንግተን ሲካሄድ የነበረውንም ድርድር ያቋረጠችበት ምክንያት በግብፅ ፍላጎት ታዛቢ እንዲሆኑ የገቡት አሜሪካና የዓለም ባንክ ለግብፅ ከመወገን አልፈው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ላይ ጫና ለማሳደር ሞክረዋል በማለት ኢትዮጵያ መውቀሷ የሚታወስ ነው።
አሜሪካ፣ የዓለም ባንክ ከግብፅ ጎን ቆመው ነበር በተባለው በዚህ ድርድር ላይ ከመጀመሪያው ሙሌት በኋላ ኢትዮጵያ ለምትጠቀመው ውሃ ለግብፅ የተጠራቀመ የውሃ ጉድለት ማካካሻ እንድትሰጥ የሚያስገድድ እንደሆነም ተገልጾ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ የግብፅ ሃሳብ በአባይ ወንዝ ላይ ተፈጥሯዊ መብት እንዳይኖራት ወይም ምንም ዓይነት የውሃ ልማት ያልተገነባበት ፍሰት እንዲኖር የሚጠብቅ ነው በማለትም ትተቻለች።
በአምስት ዓመታት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከአስር ዓመታት በላይ አስቆጥሮ በመጪው አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ በይፋ እንደሚመረቅ የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።