በኢትዮጵያ የነዳጅ ምርቶች ዋጋ በምን ያህል ጨመረ?

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ትናንትና መስከረም 18/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በነዳጅ ምርቶች ላይ ከመስከረም 18/2015 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የዋጋ ማሻሻያ መደረጉን አሳውቋል።

በአገሪቱ ለነዳጅ ሲደረግ የነበረውን ድጎማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው ተከታታይይ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ማስቀጠል አለመቻሉን የገለጸው ሚኒስቴሩ፣ ድጎማውን “ደረጃ በደረጃ ለማስቀረት” እየሰራ እንደሆነ ጠቁሟል።

ድገማውን የማንሳት ተግባር ከሦስት ወራት በፊት የተጀመረ ሲሆን ይህም በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችን በማይጎዳ እና “በበቂ ጥናት ዝግጅት” እየተከናወነ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጻል።

የነዳጅ ድጎማው በየሦስት ወሩ እየተቀነሰ ከጊዜ በኋላ ሙሉ በሙሉ ተነስቶ በተጠቃሚዎች የሚሸፈን ይሆናል።

በዚህ መሠረትም የመጀመሪያው ዙር የድጎማ ቅነሳ ከሐምሌ 2014 እስከ መስከረም 2015 ዓ.ም ተግባራዊ የሆነ ሲሆን “ከውስን ክፍተቶች በስተቀር በአጥጋቢ ሁኔታ ሲከናወን ቆይቷል” ብሏል - ሚኒስቴሩ።

በመጀመሪያው ዙር የነዳጅ ድጎማ ቅነሳ ላይ የቤንዚን፣ የነጭ ናፍጣና የኬሮሲን ዋጋ ላይ ሲደረግ የነበረው ድጎማ 75 በመቶ በመንግሥት መከፈሉን ቀጥሎ 25 በመቶው ደግሞ በተጠቃሚዎች ሲከፈል ቆይቷል።

ሆኖም የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ የሚደረገው ድጎማ ቀጥሎ ከ65 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተሽከርካሪዎች ከ310 ሚሊዮን ብር በላይ መከፈሉን ሚኒስቴሩ አመላክቷል።

ባለፉት ሦስት ወራት በመንግሥት ሲደረግ የቆየው ድጎማ ላይ ለውጥ የተደረገ ሲሆን ይህም የነዳጅ ምርቶች ዋጋ ላይ ለውጥ አምጥቷል።

በዚህ መሰረትም አንድ ሊትር ቤንዚን 57 ብር ከ05 ሳንቲም፣ ነጭ ናፍጣ 59 ብር ከ90 ሳንቲም፣ ኬሮሲን 59 ብር ከ90 ሳንቲም የሚሸጥ ይሆናል።

አንድ ሊትር የአውሮፕላን ነዳጅ 76 ብር ከ87፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 43 ብር ከ89 ሳንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ 43 ብር ከ06 ሳንቲም የሚሸጥ ሲሆን፣ ቀድመው ሲሸጡበት በነበረው ዋጋ ቀጥለዋል።

ለመሆኑ አዲሱ የነዳጅ ዋጋ ከባለፈው ጋር ሲነጻጸር በምን ያህል ጨመረ?

የነዳጅ ምርቶች ዋጋ በሐምሌ እና መስከረም

እስከ መስከረም 18/2015 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ድረስ ሲተገበር በቆየው የነዳጅ ዋጋ የቤንዚን፣ የነጭ ናፍጣ እና የኬሮሲን ዋጋን መንግሥት 75 በመቶ ሲደጉም የቆየ ሲሆን፣ ለቀጣዮቹ ወራት የሚያደርገውን ድጎማን ለውጥ ተደርጎ የቤንዚን ድጎማ ወደ 50 በመቶ፣ የነጭ ናፍጣ ደጎማ ደግሞ ወደ 66.77 በመቶ ዝቅ ተደርጓል።

ከአጠቃላይ ማስተካካያው ዝቀተኛ ጭማሪ የተደረገው ቤንዚን ላይ ሲሆን የ9 ብር ከ22 ሳንቲም ጭማሪ ተደርጎበታል።

በነዳጅ ምርቶቹም ላይ ባለፉት ሦስት ወራት ከነበረበው ዋጋ ከ16 በመቶ እስከ 18 በመቶ ጭማሪ ታይቷል።

በዚህ መሠረትም አንድ ሊትር ቤንዚን 47 ብር ከ83 ሳንቲም ሲሸጥ ከነበረበት 16 በመቶ ወይም በ9 ብር ከ22 ሳንቲም ከፍ ብሎ በ57 ብር ከ05 ሳንቲም ይሸጣል።

ነጭ ናፍጣ ከሐምሌ 2014 እስከ መስከረም 2015 ዓ.ም 49 ነጥብ 02 በሊትር የሚሸጥበት ዋጋ ወደ 59 ብር ከ90 ሳንቲም አሻቅቧል።

ይህም ካለፈው መሸጫ ዋጋ የ10 ብር ከ 88 ሳንቲም ወይም የ18 በመቶ ጭማሪን ያሳየ ነው። እስከ ትላንት አንድ ሊትር ኬሮሲን ወይም ነጭ ጋዝ በ49 ብር ከ02 ሳንቲም ሲሸጥ የነበረ ሲሆን ከነጭ ናፍጣ ዋጋ ጋር በእኩል በመጨመር የ10 ብር ከ 88 ሳንቲም ወይም የ18 በመቶ ጭማሪን ተደርጎበት 59 ብር ከ90 ሳንቲም መሸጥ ጀምሯል።

የነዳጅ ምርቶች ዋጋ በሐምሌ 2014 እና መስከረም 2015 በሊትር

  • ቤንዚን፡ ከ47 ብር ከ83 ሳንቲም ወደ 57 ብር ከ 05 ሳንቲም [የ16 በመቶ ወይም የ9 ብር ከ22 ሳንቲም ጭማሪ]
  • ነጭ ናፍጣ፡ ከ49 ነጥብ 02 ሳንቲም ወደ 59 ብር ከ90 ሳንቲም [የ10 ብር ከ 88 ሳንቲም ወይም የ18 በመቶ ጭማሪን]
  • ኬሮሲን፡ ከ49 ነጥብ 02 ሳንቲም ወደ 59 ብር ከ90 ሳንቲም [የ10 ብር ከ 88 ሳንቲም ወይም የ18 በመቶ ጭማሪን] 

ንግድና ቀጠናዊ ሚኒስቴር በአውሮፕላን ነዳጅ፣ በቀላል ጥቁር ናፍጣ እና በከባድ ጥቁር ናፍጣ ላይ እየተደረገ ስለነበረው ድጎማ መጠን ሳይጠቅስ የነዳጅ ምርቶቹ ባሉበት ይቀጥላሉ ብሏል።