“ድምጼን ለዘላለም አጥቼ ነበር” ለሃምሳ ዓመታት የዘለቁት ታዋቂው የእግርኳስ ተንታኝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እግር ኳስን ለሚመለከቱ የማርቲን ታይለር ድምጽ አዲስ አይደለም።
አንደበተ ርቱዕ የሆኑት ማርቲን በእግር ኳስ ኮሜንታተርነት (ተንታኝነት) የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉ ናቸው።
ግማሽ ምዕተ ዓመትን በእግር ኳስ ኮሜንታተርነት ያሳለፉት ማርቲን፣ ለአንዳንድ ጨዋታዎች መደምደሚያ የሳቸው ድምጽ ማጀቢያ ሆኗል።
ለምሳሌ ያህል በአውሮፓውያኑ 2012 ማንችስተር ሲቲ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን 3 ለ 2 ሲያሸንፍ “አጉየሮኦኦኦ” [Agüeroooo!] በሚል የጮሁበት ድምጽ ይታወሳል።
ማንችስተር ሲቲ አሸናፊ የሆነበትን ጎል አርጀንቲዊው ሰርጂዮ አጉየሮ ነበር ያስቆጠረው።
ወደ ኢትዮጵያም ስንመጣ፤ ከአስርታት በፊት ኢትዮጵያ ከዚምባብዌ ጋር ባደረገችው የፍጻሜ ጨዋታ ላይ የስፖርት ጋዜጠኛው ደምሴ ዳምጤን ‘ዳኙ ገላግሌ...’ በምትለው ድምጽ በርካቶች ያስታውሱታል።
ወደ ዩናይትድ ኪንግደሙ የእግር ኳስ ተንታኝ እና ስፖርት ጋዜጠኛ ማርቲን እንመለስ።
ማርቲን በአውሮፓውያኑ 2022 ኳታር በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ በተለይም በፍጻሜ ጨዋታ ወቅት ድምጻቸውን ከልክ በላይ በመጠቀማቸው አንደበታቸው ሊዘጋ ጫፍ ደርሶ ነበር ይላሉ።
የህክምና ባለሙያዎች የድምጽ አውታሮቻቸው (vocal cords) በቋሚነት ሊጎዱ እንደሚችሉ የተነገራቸው ማርቲን ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ገቡ።
ነገር ግን በደቡብ ምዕራብ ለንደን በሚገኘው የሴንት ጆርጅ ሆስፒታል ሁለት ጊዜ ያህል የቀዶ ህክምና “አስገራሚ” የሚባል የንግግር ህክምና (ስፒች ቴራፒ) ከተደረገላቸው በኋላ አንደበታቸው ከመዘጋት ተርፏል።
በእግር ኳስ ዓለም የሚታወቀው ይህ ድምጽ ተመልሶ በየቴሌቪዥን መስኮት እንደገና መደመጥም ይዟል።
የቀድሞው የስካይ ስፖርት ተንታኝ ድምጻቸውን ሊያጡ እንደነበር ሲናገሩ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ድምጻቸው እንዳይጠፋ ላደረጉትም የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) ሠራተኞች ያላቸውን ምስጋና ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, St George's Hospital
“ድምጻቸውን ለመመለስ የተደረገው እርዳታ”
የ78ቱ ዓመት ታይለር ስለ ድምጻቸው ሲናገሩ “ድምጼ ማንነቴ ነው። የሕይወቴ ማዕከል ነው” ይላሉ።
“ከዚህ ቀደም ስለ ድምጼ አስቤ አላውቅም፤ ምንም ትርጉም አልነበረውም። አሁን ግን ድምጼን እንደ ቀላል ነገር አልወስደውም” ይላሉ።
በኳታር የዓለም ዋንጫ ኮሜንታተርነታቸውን አጠናቀው ከተመለሱ ከስድስት ሳምንታት በኋላ ነበር ችግር እንዳለ የተረዱት።
“ድምጼ ላይ ትክክል ያልሆነ እና ኃይሉም እንደቀነሰ” ማስተዋላቸውን ይናገራሉ።
በኳታር የነበረው ሞቃታማ የአየር ንብረት እና የአየር ማቀዝቀዣው (ኤሲ) አንደኛው ምክንያት ቢሆንም፣ በተጨማሪም በበርካታ ግጥሚያዎች ላይ ብቻቸውን ትንተና ሲሰጡ እንደነበርም አምነዋል።
እናም ምናልባትም አለርጂ ይሆናል በሚል ግምት ሁኔታውን ለማንም ሳይናገሩ ድምጻቸው እስኪመለስ እና እስኪያገግሙም ጠበቁ።
በጨዋታዎች ላይም አስተያየት ሳይሰጡ እስከ 90 ደቂቃ ከጠበቁ በኋላም መጨረሻ ላይ የጮሁበት አጋጣሚም እንደነበርም ይናገራሉ።
ነገር ግን በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንደማይችሉና እርዳታ ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸው ተገነዘቡ።
የሴንት ጆርጅ ዶክተሮች ባደረጉት ምርመራ በጉሮሯቸው ውስጥ ኬራቶሲስ የተባለውን ፕሮቲን ክምችት አገኙ።
በአብዛኛው ጊዜ በፀጉር እና በቆዳዎች ላይ የሚገኘው ይህ ፕሮቲን በታይለር ጉሮሮ የድምጽ አውታሮች ላይ ተከማችቶ ቁስለትን ፈጥሮ ነበር። የተሳካ ህክምና ቢያደርጉም ድምጻቸውን ወደ ቀደመ ሁኔታ ለመመለስ በመሠረታዊነት የንግግር ህክምና አስፈላጊ ነበር።
“ስልክ መመለስ ተቸገርኩ፤ አንድ ዓረፍተ ነገር እንኳን መናገር አልቻልኩም” ይላሉ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውሱ ታይለር።
ምንም እንኳን በጭራሽ ህመም ባይሰማቸውም “ከቀዶ ህክምናው ለማገገም የነበረው ሂደት ዝግ ያለ ነበር” ይላሉ።
በተለይም ከጓደኞቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር መነጋገር አለመቻላቸው ታይለርን በበለጠ አስፈራቸው።
እንዲህም ባሉበት ሁኔታ የንግግር ባለሙያዋ (ስፒች ቴራፒስት) ኤሊሳ ፊን በራስ መተማመናቸውን ለመጨመር እንደሚሻላቸው እንዲያምኑ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች ይላሉ።
“ውሃ ላይ አረፋዎች እንዳወጣ እንዲሁም ሁሉንም ዓይነት እንግዳ ድምጾች እንዳወጣ አደረገችኝ” ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“ኤሊሳ እና ሌሎች ሰዎችም ከምጠብቀው በላይ ድጋፍ አድርገውልኛል” በማለት ያስረዳሉ።
ኤሊሳ ድምጻቸውን ማጣታቸው “አስፈሪ ነገር” ሊሆን እንደሚችል ትነግራቸው እንደነበር ያስረዳሉ።
ለእሳቸው ብቻ ሳይሆን በሙያዊ ሥራቸው ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ድምጻቸውን ለሚጠቀሙ እንደ መምህራን፣ ዘፋኞች እና የሕግ ባለሙያዎች ምክር እና የድምጽ ህክምና ትሰጣለች።
ታይለርም ከቀዶ ህክምናቸው በኋላ ብዙም ሳይቆዩ የትንፋሽ እና ሌሎች የድምጽ ህክምናዎች ይሰጣቸው ነበር። ባለሙያዋ አብዝተው ውሃ እንዲጠጡ፣ በእንፋሎት ውስጥ እንዲተነፍሱ ወይም እንዲታጠኑ እንዲሁም ለድምጻቸው እረፍት እንዲሰጡትም ትመክራቸው ነበር።
አንድ ሰው ድምጹን ሊያጣ የሚችልባቸው በርካታ ምክንያቶች እንዳሉም ባለሙያዋ እንዳስረዳቻቸው ይናገራሉ። ደረቅ የአየር ሁኔታዎች፣ አለርጂዎች፣ ረጅም በረራዎች ድምጽ ላይ ተጽእኖ የሚፈጥሩ ሲሆን፣ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።
በጥቅምት ወር የእግር ኳስ ትንታኔያቸውን ወደሚሰጡበት ሳጥናቸው ተመልሰዋል። በፕሪሚየር ሊግም 45 ጨዋታዎች ላይ ኮሜንታተር በመሆን አጠናቀዋል።
የፕሪሚየር ሊግ አዘጋጆችም በድምጻቸው ምክንያት ሥራቸውን ማከናወን ሲያቅታቸው ከጎናቸው እንደቆሙ እና እስኪያገግሙ ድረስም ለመጠበቅ ደስተኞች እንደነበሩም ታይለር ገልጸዋል።
ቼልሲ ኤቨርንተንን 6 ለ0 ባሸነፈበት ወቅትም ኮሜንታተር የነበሩት ታይለር፤ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ቤት ሲመለሱ ድምጻቸውን እንዴት እንደሚጠብቁ እያሰቡ ነበር።
ብዙ ውሃ እንደሚጠጡ እና ለቀጣዩም ጨዋታ የተለመደ የድምጽ ዝግጅታቸውን እንደሚያደርጉም ያስረዳሉ።
ለሃምሳ ዓመታት የዘለቁት ታይለር ታዲያ እስከ መቼ በኮሜንታተርነታቸው ይቀጥሉ ይሆን? “የሚያቆመኝ ድምጼ አይሆንም” የሚሉት ታይለር “በጣም ዕድለኛ ነኝ” ሲሉም አጠቃለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Martin Tyler












