ሩሲያ በቱርክ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች መባሏን አስተባበለች

የቱርክ የተቃዋሚ ፓርቲ እጩው ከማል ኪሊዳሮግሉ ሩሲያን በምርጫ ጣልቃ በመግባት መክሰሳቸውን ተከትሎ ክሬምሊን በቱርክ ምርጫ ጣልቃ እንዳልገባ አስተባብሏል።

የክሬምሊን ቃለ አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሩስያ በሌሎች አገራት ውስጣዊ ጉዳዮች ጣልቃ አትገባም ብለዋል።

“ለከማል ኪሊዳሮግሉ እንዲህ አይነት መረጃ አቅርበውላቸው ከሆነ እነሱ ውሸታሞች ናቸው” ሲሉ አክለዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ከማል ኪሊዳሮግሉ ለ20 ዓመታት በስልጣን ላይ ያሉትን አይነኬ የተባሉትን ኃያሉን ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋንን በአገሪቱ የዘንድሮው ምርጫ እየተፈታተኗቸው ይገኛሉ።

የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ሩስያን ስለከሰሱበት ጉዳይ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

ነገር ግን ሐሙስ ዕለት በሩስኪ ቋንቋ ጭምር በተጋራው ትዊተር መልዕክታቸው ሩሲያውያን “ በአገሪቱ ውስጥ በሚቀነባበሩ ሴራዎች፣ ሃሰተኛ መረጃዎች፣ ጽሁፎችና ቪዲዮዎች” ጀርባዎች አሉበት ሲሉም ከሰዋል።

ሩሲያ ቅዳሜና እሁድ ከሚደረገው ምርጫ በኋላ የቱርክን “ወዳጅነት” ከፈለገች “እጇን በቱርክ ጉዳዮች ጣልቃ ከማስገባት ልታወጣ ይገባል። አሁንም ቢሆን ትብብርና ወዳጅነትን እንፈልጋለን” ሲሉም የተቃዋሚ መሪው ተናግረዋል።

ዲሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው ሩሲያ ከቱርክ ጋር ያላትን ግንኙነት ከፍተኛ ዋጋ እንደምትሰጠው አበክረው ገልጸዋል።

“የቱርክ ሪፐብሊክ እስካሁን ድረስ በሁሉም ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ችግሮች ላይ በጣም ኃላፊነት የሚሰማው፣ ሉዓላዊነት በጠበቀ መልኩ እና የታሰበበት አቋም ወስዷል። ይህ አቋም በእኛ ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ አሳድሯል” ብለዋል።

በቱርክ ምርጫ ላይ ሩሲያ ጣልቃ እየገባች ነው የሚለው የተቃዋሚ መሪው የትዊተር ጽሁፍ ሩሲያ ላይ ያቀረቡት የመጀመሪያ ክስ አይደለም።

ከሳምንታት በፊትም የቱርክ መንግሥት ባለስልጣናት በምርጫው ጣልቃ ለመግባት “ዳርክ ዌብ” ብለው የጠሩትን ስምምነቶች እንዳይፈጽሙ አስጠንቅቀው ነበር።

በቱርክ መንግሥት በቢትኮይን ምንዛሪ ከሚከፈላቸው የውጭ የመረጃ መንታፊዎች ጋር ስምምነቶች ተደርገዋል ሲሉም ተናግረው ነበር።

የፕሬዚዳንቱ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ፋህረቲን አልቱን አስተያየቱን “ምክንያታዊ ያልሆነ ስም ማጥፋት” ሲሉ አጣጥለውታል።

የተቃዋሚው መሪ በቅርቡ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ካሸነፉ የቱርክን የውጭ ፖሊስ አቅጣጫ በመቀየር ከክሬምሊን ሳይሆን ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያስቀድሙ ተናግረዋል።

ነገር ግን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪያቸው ኡናል ሴቪኮዝ በሩሲያ መንግስት ለሚደገፈው ሩሲያ ቱደይ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት "ሩሲያን አስመልክቶ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደማይኖር እና የተቃዋሚው መሪ ከሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ጥሩ ግንኙነት ይኖራቸዋል” ብለው እንደሚያምኑ ነው።