ሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ለሩሲያ ሰጥታለች ስትል አሜሪካ ከሰሰች

ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በምታደርገው ጦርነት የመትጠቀምበት ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ሰጥታለች ሲሉ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ሰሜን ኮሪያን ከሰሱ።

የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ እንዳሉት፣ ሰሜን ኮሪያ በአንድ ሺህ ኮንቴይነሮች የተሞሉ “የጦር መሳሪያዎች እና ጥይቶችን በቅርብ ሳምንታት ውስጥ” ወደ ሩሲያ ልካለች በማለት የፎቶ ማስረጃዎችን አቅርበዋል።

ባለፈው መስከረም ወር የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከሩሲያ ጋር ስለሚኖራቸው ወታደራዊ ትብብር ለመነጋገር ሩሲያን ጎብኝተው ነበር።

ከዩክሬን ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት ከፍተኛ መጠን ያለውን መሳሪያዋን ጥቅም ላይ ያዋለችው ሩሲያ፣ ክምችቷን ለማሟላት የሰሜን ኮሪያን ድጋፍ ልትፈልግ ትችላለች ብለዋል ተንታኞች።

ሰሜን ኮሪያ ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል የጦር መሳሪያ ክምችት ቢኖራትም የጥሬ እቃ እጥረት ስላለበት ብዙውን ለወዳጆቿ አሳልፎ መስጠቷ አጠራጣሪ ነው ሲሉም አክለዋል።

የአሜሪካ የስለላ ተቋማት ባገኙት መረጃ መሠረት ደቡብ ኮሪያ ከመስከረም ወር መጀመሪያ ሳምንት አንስቶ አስከ ጥቅምት መጀመሪያ ድረስ በባሕር እና በባቡር ወደ ደቡባዊ ሩሲያ የጦር መሳሪያዎችን ልካለች።

ጆን ኪርቢ ሰሜን ኮሪያ ምን አይነት መሳሪያዎችን ለሩሲያ እንደሰጠች በዝርዝር ያልገለጹ ሲሆን፣ ነገር ግን ቀደም ሲል ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ ሮኬቶችን እና የመድፍ ጥይቶችን ገዝታለች ስትል አሜሪካ ከሳ እንደነበር ይታወሳል።

ሩሲያ ከአንድ ዓመት በፊት በዩክሬን ላይ ወረራ ከከፈተችበት ጊዜ አንስቶ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ ጥይቶችን እያቀረበች ነው በማለት በተደጋጋሚ ሲከሱ ነበር።

ኪርቢ ጨምረውም “ከአጋሮቻችን ጋር ጉዳዩን በተደጋጋሚ በመንግሥታቱ ድርጅት ስብሰባ ላይ የምናነሳው” ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ማቅረቧ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብን የሚጥስ በመሆኑ ነው ብለዋል።

ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ አሜሪካ በቢሊዮኖች ዶላሮች የሚገመቱ ዘመናዊ የጦር ማሳሪያዎችን ለዩክሬን እያስታጠቀች መሆኗ ይታወቃል።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ የሩሲያው የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ ወታደራዊ ልዑካንን በመምራት ሰሜን ኮሪያን በጎበኙበት ጊዜ ከፕሬዝዳንት ኪም ጋር ተገናኝተው ነበር። በዚህም አህጉር አቋራጭ ሚሳኤልን እና ሌሎች በርካታ የጦር መሳሪያዎችንም አስጎብኝተዋቸዋል።

ሩሲያ ያረጁ የጦር መሳሪያ ክምችቷን እየጨረሰች መሆኑን የሚገልጹት የአሜሪካ ባለሥልጣናት፣ አሁን ከሰሜን ኮሪያ ያገኘችው የጦር መሳሪያ እና ተተኳሾች በጦርነቱ ላይ የጎላ ለውጥ አያመጡም ይላሉ።

ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ለዩክሬን ስታቀርብ የቆየችው አሜሪካ፣ በምክር ቤቷ ውስጥ በተነሳ የበጀት ውዝግብ ምክንያት ልትሰጣት ያሰበችው 6 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ ወታደራዊ ድጋፍ ለጊዜው ተደናቅፏል።

ፕሬዝዳንት ባይደንም ዩክሬንን ለመርዳት ሌሎች አማራጮችን እንሚፈልጉ ገልጸዋል።