ከምርጫው ፉክክር እንድወጣ ሊያሳምነኝ የሚችለው “ሁሉን ቻይ የሆነው ጌታ ብቻ ነው”፡ ፕሬዚዳንት ባይደን

በቅርቡ በተደረገ የምርጫ ክርክር ሃሳባቸውን መግለጽ ሲሳናቸው የታዩት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከፕሬዚዳንታዊ ፉክክሩ እንድወጣ ሊያሳምነኝ የሚችለው “ሁሉን ቻይ የሆነው ጌታ ብቻ ነው” ሲሉ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንት ባይደን ይህንን የተናገሩት በእሳቸው ላይ እየተነሱ ካሉ ስጋቶች አንጻር ዲሞክራቶችን ለማረጋጋት በሚል ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።

ከፕሬዚዳንታዊ ፉክክሩ እንዲወጡ ጫና የበዛባቸው ባይደን ባልተለመደ መልኩ ከኤቢሲ ሚዲያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በመራጮቻቸው ዘንድ ጥያቄ ውስጥ የገቡት ፕሬዚዳንቱ በመጪው የሥልጣን ዘመን ለማገልገል ብቁ እንደሆኑ ለማረጋገጥ የግንዛቤ ፈተና ለመውሰድም ሆነ ውጤቱን ይፋ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም።

“በየቀኑ የግንዛቤ ፈተና ላይ ነኝ። በየቀኑ ያ ፈተና አለብኝ። የማደርገው ነገር ሁሉ ፈተና ነው” ሲሉም ለኤቢሲው ጆርጅ ስቴፋኖፖሎስ ተናግረዋል።

የ81 ዓመቱ አዛውንት ባለፈው ሳምንት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ባደረጉት የምርጫ ክርክር ሃሳባቸውን መግለጽ ሲሳናቸው ከታዩ በኋላ ወጣት ዕጩ እንዲተካቸው በአንዳንድ የዲሞክራቶች እንዲሁም በለጋሾች የቀረበውን ሃሳብ አልተቀበሉትም።

ከፕሬዚዳንቱ ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ የኤቢሲው ጋዜጠኛ ስቴፋኖፖሎስ ባይደን በመጪው የሥልጣን ዘመን ለማገልገል ምን ያህል ብቁ ነዎት? የሚለውን ጥያቄ አጥብቆ ጠይቋቸዋል።

ፕሬዚዳንቱን “ጤንነትዎት ያለበትንም ሁኔታ እንዲሁም አሸንፋለሁ ብለው ማሰብዎት ራስዎን እየካዱ አይደለም ወይ?” ሲልም ተደምጧል።

እሳቸውም በምላሻቸው “ከእኔ የበለጠ ፕሬዚዳንት ለመሆን ወይም ይህንን የምርጫ ውድድር ለማሸነፍ ብቁ የሆነ ሰው ያለ አይመስለኝም” ብለዋል።

በቅርቡ የነበረው የምርጫ ክርክር “ከፍተኛ ድካም ተሰምቶኝ እና ከባድ ጉንፋን ይዞኝ” ስለነበር ነው በማለት ባለፈው ሳምንት የገጠማቸውን ለማስረዳት ሞክረዋል።

ፕሬዚዳንቱ ከኤቢሲ ጋር ለ22 ደቂቃ ያህል ቆይታ ያደረጉ ሲሆን በዚህም፦

  • ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር ከነበረው ክርክር በኋላ ፍርሃት የገባቸውን ዲሞክራቶችን ለማረጋጋት የሞከሩ ሲሆን፣ የሰበሰቧቸው የሕዝብ አስተያየቶችም ፉክክሩ ገና መሆኑን ያሳዩ እንደሆኑ አጽንኦት ሰጥተዋል።
  • አጋሮቻቸው ከምርጫው ፉክክር ራሳቸውን ገሸሽ እንዲያደርጉ ሊጠይቋቸው ይችላሉ የሚለውንም አስተያየት “በፍጹም አይሆንም” ብለዋል።
  • ባይደን ከምርጫው ፉክክር እንዲወጡ ሊያስገድዳቸው ስለሚችሉ ጉዳዮች ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ውድቅ ያደረጉ ሲሆን፣ “ሁሉን ቻይ የሆነው ጌታ ወርዶ ጆ ከውድድሩ ውጣ ካለኝ እወጣለሁ። ሁሉን ቻይ አምላክ ወደ መሬት አልወረደም” ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ አሁን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ባለፈው ሳምንት በነበረው የምርጫ ክርክር መድረክ ከነበራቸው አቋም በተሻለ ሁኔታ ላይ ሆነው ግልጽ ምላሽ የሰጡ ቢሆንም ድምጻቸው ደከም ያለ እና አልፎ አልፎም ሸካራነት ነበረው።