መጥፎ የአፍ ጠረን የሚከሰተው ለምንድን ነው? እንዴት መከላከል ይቻላል?

የአፍ ጠረኑን የሚከታተል ወንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአፌ ጠረን ጥሩ ላይሆን ይችላል በሚል ስጋት ወደ ሰዎች ቀረብ ብለው ማውራት ሰግተው ያውቃሉ? ይህ የተለመደ ክስተት ስለሆነ ስጋት አይግባዎት። መፍትሔ አለው።

ጥርስን ሁልጊዜ በምናፀዳበት ወቅት በጥርሶቻችን መካከል፣ በድዳችን እና በምላሳችን ላይ ተደብቀው ከሚቀመጡ ባክቴሪያዎች ጋር ማብቂያ የሌለው ጦርነት እናደርጋለን።

እነዚህን ባክቴሪያዎች ካላጠፋችኋቸው፣ እዚያው ሊራቡ እና አደገኛ የሆነ የድድ ሕመም ሊያስከትሉ ይችላሉ።

ነገር ግን ለዚህ ሁልጊዜም የመከላከያ መፍትሄ አለ።

መጥፎ የአፍ ጠረን መንስዔ ምንድን ነው?

በዓለም ዙሪያ ለመጥፎ የአፍ ጠረን ከሚዳርጉ ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ የድድ ሕመም ነው።

በእንግሊዝ በሚገኘው በርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ የጥርስ ሕክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ፕራቨን ሻርማ ለቢቢሲ "ግማሽ የዓለም ሕዝብ የተለያየ ዓይነት የድድ ሕመም አለበት" ይላሉ።

አክለውም "መጥፎ የአፍ ጠረን የሚመጣው ከአፋችን የሚወጣው አየር ደስ የማይል ሽታ ሲኖረው ነው" ብለዋል።

"ይህ ምናልባት 90 በመቶ መጥፎ የአፍ ጠረንን ይሸፍናል።"

ሌላው 10 በመቶ በሌሎች ምክንያቶች የሚከሰት ነው።

ዶ/ር ሻርማ "ተገቢው ቁጥጥር ያልተደረገበት የስኳር ሕመም በተወሰነ መልኩ ለአፍ ጠረን መለወጥ ምክንያት ይሆናል።"

"የጨጓራ እና የአንጀት ሕመም ያለባቸው ሰዎች፣ የጨጓራ ​​አሲድ መመለስ የአፍን ጠረን ከሚቀይሩ ምክንያቶች መካከል ናቸው፤ ስለዚህ በአፍ ውስጥ በሽታዎች ይፈጠራሉ።"

ስለዚህ፣ምን ማድረግ ይቻላል?

ጥርሷን በፍሎስ የምታጸዳ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጥርስ መካከል ያለውን ነገር ቆሻሻ ወይንም ምግብ ማስወገድ አስፈላጊ ነው

ችግሩን ከመሠረቱ ይለዩ

በጥርሶችዎ እና በድድዎ መካከል የሚቀመጡ ባክቴሪያዎችን ካላፀዱ ወደ ትንንሽ ቁስሎች እና ከዚያ በኋላ የድድ መድማትን ያስከትላሉ።

ይህ ቀላል የሆነ የድድ እብጠትን የሚያስከትለውን ጂንጁቫይተስ (gingivitis) የሚባለውን ሕመም ያስከትላል፤ ጥሩው ነገር ግን ይህንን ችግር በቀላሉ መቆጣጣር ይቻላል።

ዶ/ር ሻርማ "ጂንጁቫይተስ የድድ እብጠት ነው እና ይህንንም ጥርስዎን በሚያጸዱበት ወቅት ድድዎ ቀልቶ፣ አብጦ ሲደማ ይመለከታሉ።"

"ይህ ነው ወደ ፔሪየዶንቲቲስ (periodontitis) የሚያድገው" ይህም ከበድ ያለ የየድድ ሕመም ሲሆን፣ ጥርስ እና አጥንትን የሚጎዳ ነው።

ጥርስዎን በሚያፀዱበት ወቅት ድድዎ መቅላቱን፣ማበጡን ወይም እንደሚደማ ይፈትሹ፤ ነገር ግን ብዙ አይጨነቁ ምክንያቱም እርምጃ ለመውሰድ አሁንም ጊዜ አለ።

"ሕሙማን ከሚያደርጓቸው ነገሮች አንዱ ጥርሳቸውን በሚቦርሹበት ጊዜ የታመመውን ድድ ከመቦረሽ ይቆጠባሉ። ምክንያቱም "ኦ፤ እየጎዳሁት ነው፤ ስህተት እየሠራሁ ነው፤ ለዚያም ነው የሚደማው ብለው ስለሚያስቡ" ይላሉ ዶክተር ሻርማ።

"ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ነው፤ጥርስን በሚገባ ለመቦረሽ የድድ መድማትን እንደ ምልክት መጠቀም ይኖርብናል፤ ከዚህ በፊት በሚገባ ስላልቦረሽኩ አሁን የተሻለ መቦረሽ አለብኝ ማለት ይኖርብናል።"

የጥርስ እና ድድ ምሥል

አስተውለው ይቦርሹ

ዶ/ር ሻርማ በትክክል ለመቦረሽ ጊዜ መውሰድ አለብዎት ይላሉ።

"ሌሎች ነገሮችን እየሠሩ ጥርስን መቦረሽ ወይም ማፅዳት ተገቢ አይደለም።በመስታወትዎ ፊት ለፊት ቆመው አተኩረው መቦረሽ ያስፈልግዎታል።"

ቀኝ እጃቸውን አዘውትረው ለተለያዩ ተግባራት የሚጠቀሙ ሰዎች ሳያስተውሉ የግራ ጥርሳቸውን እና ድዳቸውን ረዘም ላለ ጊዜ ይቦርሹታል።

ግራኞች ደግሞ በተቃራኒው የቀኝ ጎናቸውን ረዘም ላለ ጊዜ ይቦርሻሉ። ይህ ደግሞ ብዙም ትኩረት በማይሰጠው ጎን ላይ ተጨማሪ እብጠት ያስከትላል።

የትኛውን እጅዎን እንደሚጠቀሙ ያስተውሉ እና ሁለቱንም ጎኖች በእኩል እና በጥንቃቄ ለመቦረሽ ይሞክሩ።

የጥርሶቹን መካከል የሚያጸዳ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጥርሳችንን እንዴት እንቦርሽ?

ዶ/ር ሻርማ በመጀመሪያ በጥርሶች መካከል ያሉ ቆሻሻዎችን በማጽዳት መጀመርን ይመክራሉ።

"በጥርሶች መካከል ያሉ ቆሻሻዎችን ለማስወገድ እና የድድ ጤናን ከመጠበቅ አንፃር በጥርስ መካከል ያሉ ቆሻሻዎችን ቀድሞ ማጽዳት የተሻለ ነው" ብለዋል።

የጥርስን መካከል ማጽዳት የሚያስችሉ ብሩሾችን ከተጠቀሙ በኋላ የጥርስ ብሩሽዎን በአፍዎ ውስጥ ሲያንቀሳቅሱ መቸኮል አያስፍለግም።

እያንዳንዱ ጥርስ ሦስት ገጽታዎች እንዳሉት ማስታወስ ተገቢ ነው።

ውጫዊ፣ የምናኝክበት የላይኛው ክፍል እና ውስጣዊ።

ሁሉም በጥንቃቄ መጽዳት አለባቸው። ብዙዎችን ሊያስገርም ይችላል፤ ነገርግን ጥርስን ለመቦረሽ የምንወስደው ትንሹ ሰዓት ሁለት ደቂቃ ነው።

ብዙ ሰዎች የጥርስ ብሩሻቸውን በ90 ዲግሪ ወደ ጥርሱ አድርገው በመያዝ ወደ ኋላ እና ወደ ፊት በመጫን ይቦርሻሉ። ነገር ግን ይህ ዘዴ የድድ መድማትን ያስከትላል።

የጥርስ ብሩሽን ወደ ጥርሱ በ45 ዲግሪ አቅጣጫ ይያዙ እና በቀስታ ይፋቁ።

ጥርስዎን ሲፍቁ የታችኛውን ጥርስ ወደ ላይ፣ የታችኛውን ጥርስ ደግሞ ወደ ታች ይቦርሹ።

ይህ በድድ መስመር ስር ተደብቀው የሚገኙ ባክቴሪያዎችን ለማስወገድ ይረዳል።

እናትና ልጅ ከጥርስ ሐኪም ጋር ተቀምጠው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በትክክለኛው ጊዜ ይቦርሹ

ከተመገብን በኋላ ጥርሳችንን መቦረሽ እንዳለብን ብዙዎቻችን ተምረን ይሆናል። ግን እንደገና እናስብ።

"በተለምዶ ቁርስ ከመብላታችን በፊት መቦረሽ አለብን" ይላል ዶክተር ሻርማ።

"አሲዳማ የሆነ ነገር ከወሰዱ በኋላ መቦረሽ አይፈልጉም፤ በጥርሳችን የሚነራል መዋቅር ላይ፤በኢናሜል እና በዴንታይን፤ የራሱ የሆነ የማለስለስ ተጽዕኖ አለው።"

በምግብ ውስጥ ያለው አሲድ በጥርሶች ላይ ያለውን መከላከያ ኤናሜል እና ከስር ያለውን ዴንታይን እንዲለሰልስ ያደርገዋል።

ስለዚህ ከምግብ በኋላ ወዲያውኑ ጥርስን መቦረሽ የጥርስዎን ኢናሜል ይጎዳል።

"ቁርስዎን ከበሉ በኋላ መቦረሽ የሚመርጡ ከሆነ፤ በቁርስዎ እና ጥርስዎን በሚፍቁበት መካከል የተወሰነ ክፍተት መተው አለብዎት" ብለዋል ዶክተር ሻርማ።

አፍዎን ታጥበው ትንሽ መጠበቅ አለብዎት።

እንዲሁም በቀን ሁለት ጊዜ ጥርስዎን ለሁለት ደቂቃዎች ያህል መቦረሽ ጥሩ ቢሆንም፣ አንዳንድ ሰዎች በቀን አንድ ጊዜ በትክክል መቦረሽ በቂ ሆኖ ሊያገኙት ይችላሉ።

በሚተኙበት ጊዜ የምራቅዎ ፍሰት ይቀንሳል፤ በዚህም ወቅት ባክቴሪያዎች በምሽት ጥርስዎ ላይ የበለጠ ጉዳት እንዲያደርሱ ያስችላቸዋል።

ስለዚህ፣ በቀን አንድ ጊዜ ጥርሶችዎን በደንብ ለማጽዳት ከፈለጉ በጣም ጥሩው ጊዜ ምሽት ላይ ነው።

ትክክለኛውን ብሩሽ መጠቀም

መካከለኛ ጥንካሬ ያለው የጥርስ ብሩሽ ይጠቀሙ።

የጥርስ ሳሙናዎች ውድ መሆን የለባቸውም።

"በውስጡ ፍሎራይድ እስካለው ድረስ ደስተኛ ነኝ" ሲሉ ዶ/ር ሻርማ ተናግረዋል።

ፍሎራይድ የጥርስ መስተዋትን (ኢናሜልን) በማጠንከር መበስበስን የበለጠ ይቋቋማል።

ጥርስዎን ከቦረሹ በኋላ ይትፉ።አፍዎን አይታጠቡት። ምክንያቱም የጥርስ ሳሙናው እና ፍሎራይዱ በአፍ ውስጥ በመቆየት የጥርስ መበስበስን ለመከላከል ይረዳል።

የድድ በሽታ የመጀመሪያ ምልክቶች ካጋጠምዎ የአፍን ማጠቢያዎችን (Mouthwash) መጠቀም ጠቃሚ ነው።

ምክንያቱም የባክቴሪያ ክምችትን ለመቀነስ እና መድማትን ለመከላከል ይረዳል። ነገር ግን ጥርስዎን በጥርስ ሳሙና ካጸዱ በኋላ አይጠቀሙት።

ምክንያቱም በሳሙና ውስጥ የሚገኘውን ፍሎራይድ ጠራርጎ ያጠፋዋል።

የበሰበሱ የሕፃን ጥርሶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ብዙ ጣፋጭ ምግቦችን እና መጠጦችን መጠቀም የልጆችንም ሆነ የአዋቂዎች ጥርስ እንዲበሰብስ ያደርጋል

ከባድ የድድ ሕመም ለይተው ይወቁ

የድድ መድማት (periodontitis) እየበረታ ከሄደ በጥርሶች መካከል ክፍተቶች መፈጠር ይጀምር እና ጥርሱን የያዘው አጥንት እየተሸረሸረ ጥርሶቹ ሲላሉ ያስተውላሉ።

ይህ ሁኔታ በፍጥነት ካልታከመ የአጥንት መቦርቦር ተከስቶ ጥርሶች ሊወልቁ ይችላሉ። እንዲሁም የማያቋርጥ መጥፎ የአፍ ጠረን ሊያጋጥም ይችላል። እነዚህ ምልክቶች ከታዩ ወዲያውኑ የጥርስ ሐኪም ጋር ይሂዱ።

በመጨረሻም፣ ጥሩ የአፍ ጠረን እንዲኖርዎ አንዳንድ ምክሮች እነሆ፡

  • አፍዎ ሲደርቅ ባክቴሪያ በቀላሉ ሊራባ ስለሚችል ብዙ ውሃ ይጠጡ።
  • ምላስዎን በምላስ መፋቂያ ያጽዱ። ይህም መጥፎ የአፍ ጠረን የሚያስከትሉትን የምግብ ቅንጣቶችን፣ ባክቴሪያዎችን እና የሞቱ ሴሎችን ያስወግዳል።
  • የትንፋሽዎ ጠረን ትክክል ካልመሰልዎት ለጓደኛዎ ወይም ለቤተሰብ አባልዎ ያስፈትሹ። ግን ማንን እንደሚጠይቁ በጥንቃቄ መምረጥዎን ያረጋግጡ!