ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሐማስ በእስራኤል ከባድ ሽንፈት ቢገጥመውም ጋዛን እንደገና እየተቆጣጠረ ነው
ባለፈው ጥቅምት የተደረሰው አሜሪካ መራሹ የተኩስ አቁም ስምምነት በጋዛ ጦርነትን ጋብ ሲያደርግ ሐማስ ራሱን ለማዳን ከእስራኤል ጋር ያደርግ የነበረውን ውጊያ አካባቢውን ወደ መቆጣጠር ለውጦታል።
ጦርነቱ የሐማስ ጠንካራ ወታደራዊ ክፍሎችን ወደ ደፈጣ ታዋቂዎች ያንኮታኮተ ሲሆን አብዛኞቹ መሪዎች ተገድለዋል።
የጋዛ ሕንፃዎች እና መሠረተ ልማቶች በአመዛኞ ወድመዋል፤ አብዛኛው የሕዝብ ቁጥር ተፈናቅሏል እንዲሁም የኢኮኖሚ መስመሩ ተመቷል።
በግጭቱ ከ72 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን በእስራኤል መገደላቸውን ሐማስ መሩ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ከተኩስ አቁስ ስምምነቱ አራት ወራት በኋላ በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ሐማስ ቁጥጥሩን በደኅንነት፣ የታክስ ገቢ እና የመንግሥት አገልግሎት አስፋፍቷል ብለዋል።
ይህም የረጅም ጊዜ ስልት እና ቡድኑ ትጥቁን ለመፍታት እና ሥልጣኑን ለማስረከብ ተዘጋጅቷል ወይስ አልተዘጋጀም በሚሉ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎች እንዲነሱ አድርጓል።
በጋዛ የመብት ተሟጋች የሆኑት ሞሐመድ ዲያብ ሐማስ 90 በመቶ የሚሆነውን አካባቢ ዳግም መቆጣጠሩን ይናገራሉ።
"የፖሊስ እና የደኅንነት ተቋማቱ ዳግም ተመልሰዋል። እና አሁን በመንገዶች ይንቀሳቀሳሉ፤ ወንጀልን መከላከል እና ተባባሪ ናቸው የሚሏቸውን እና ሀሳብ ያላቸውን ሰዎች ያስሳሉ። ሰዎች መታወቂያ ወይም የጤና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሐማስ ባለሥልጣናት መሄድ አለባቸው። በፍትህ ስርዓቱ እና በፍርድ ቤቶች ዳግም ቁጥጥሩን እያሰፋ ነው" ይላሉ።
በመላው ጋዛ ገበያዎች ነጋዴዎች መደበኛ የፖሊስ ቁጥጥር እና ይፋዊ ክፍያ እና ታክሶች ጠንከር ብለው ዳግም መመለሳቸውን ገልፀዋል።
አንድ ቸርቻሪ "ገበያዎች ፀጥ ብለዋል። ነገር ግን የማዘጋጃ ቤት ተቆጣጣሪዎች ኪራይ እንድንከፍል ማሳደዳቸውን ቀጥለዋል" ይላል።
በጋዛ ስለ ሐማስ ቁጥጥር ቢቢሲ ያነጋገራቸው በሙሉ ማንነታቸውን እንዲደበቅ ጠይቀዋል።
"በእያንዳንዱ ቀን ጠንከር ብለው ይመጣሉ። የማትከፍል ከሆነ እኛን እና ሸቀጦቻችንን መንገድ ላይ አውጥተው እንደሚጥሉን በተመሳሳይ ቁርጠኝነት አዘውትረው ይጠይቃሉ። የሚጠይቁት 700 ሽክልስ (225 ዶላር) ነው፤ ማናችንም የማንችለው ገንዘብ ነው።"
በጋዛ ከተማ ባልደረባችንን ያናገረ አንድ ነጋዴ 12 አባላት ያሉት ቤተሰቦቹ ሱቅ ከነበራቸው አካባቢ መፈናቀሉን ይናገራል። አሁን ይክ አካባቢ የፍርስራሽ ክምር ነው።
"በየቀኑ የማዘጋጃ ቤት ሰዎች ይመጣሉ" ይላል በአካባቢው ሲጋራ የሚሸጥ ሌላ ቸርቻሪ። "ምን ያህል እንደሸጥኩ ሲጋራ በሲጋራ ይቁጠሩ፤ ንገረኝ እስኪ ልከፍላቸው ይገባል? ወይስ ልጆቼን ልመግብ?"
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተደረሰ በኋላ ምግብ እና ሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦች በነፃ ወደ ጋዛ እየገቡ ነው። ፈቃድ ያላቸው እና ከእስራኤል ወደ ጋዛ የሚያስገቡ ጥቂት ቁልፍ ነጋዴዎች ሐማስ የገቢ ሸቆጦች ላይ ታክስ ለመጣል ጥብቅ ቁጥጥር እንደገና መጣሉን ተናግረዋል።
ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ ነጋዴ መክፈል አሻፈረኝ ያሉ ሰዎች ላይ የኃይል እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጿል።
"በሐማስ የሚጣለው ታክስ በሸቀጡ መጠን እና አይነት ላይ የተመሠረተ ነው። አንድ ነጋዴ አልከፍልም ካለ ኃይል ጥቅም ላይ ይውላል፤ እና በአንዳንዶች ላይ እገታ አሊያም ዛቻ ይፈፀማል" ይላል።
ነጋዴዎች ሐማስ ገንዘብ እየወሰደ እንደሆነ እስራኤል እንዳታውቅ ስለታክስ በሚስጢራዊ ቋንቋ እንደሚነጋገሩ ጠቁመዋል።
የሐማስ ቃል አቀባይ ሀዜም ቃሲም የጋዛ ሰርጥ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር እንደሆነ እና "ልዩ እርምጃዎች" አስፈላጊ ናቸው ብለዋል።
የጋዛ መንግሥት ከ2007 ጀምሮ በሐማስ ይመራል።
ገንዘብ ደሞዝ ለመክፈል እና እንደ እስራኤል ከሆነ ደግሞ የጦርነት አቋሙን መልሶ ለመገንባት ለቡድኑ ፈርጣማ ሥልጣን ወሳኝ ነው።