ኮል ፓልመር - ለጥቁር አያቱ መታሰቢያ ጫማ የሚያደርገው የዩናይትድ ደጋፊው ምትሀተኛ

በካሬቢያኗ ትንሽዬ ሀገር ሴይንት ኪትስ ኤንድ ኔቪስ ከውቅያኖሱ አናት የሚመጣው ነፋስ የተጨናነቀ መንፈስ የማቅለል ኃይል አለው።

ነገር ግን የቫይብስ ቢች ባር ተስተናጋጆች ጭንቀት ይዟቸዋል።

ወሩ ታኅሣሥ ዕለቱ እሑድ ከሰዓት 8፡30 ገደማ ነው። "ዳኛ፤ ፊሽካውን ንፋው እንጂ" ሲል የቼልሲው ደጋፊ ክሊፍ ብራውን ጩከቱን አሰማ።

በአነስተኛዋ የባሕር ዳርቻ መጠጥ ቤት ግድግዳውን የሸፈነ ቴሌቪዥን ተሰቅሏል።

ከዚህ ሥፍራ 6400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ለንደን ደግሞ የቼልሲ ደጋፊዎች ብርዱን መቋቋም ተስኗቸዋል። ጓንት፣ ስካርፍ፣ ወፍራም ጃኬት. . . ያልደረቡት ነገር የለም።

ጨዋታው ደርቢ ነው። ቼልሲ ከቶተንሀም ሆትስፐርስ የሚያደርጉት ጨዋታ። የስፐርሱ አምበል ሶን ሁዌንግ-ሚን በጭማሪ ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ የቼልሲ ደጋፊዎችን ልብ ምት ከፍ አደረገው።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የክሊፍ ምኞት ተሳክቶ ዳኛው ፊሽካውን ነፉ። ቼልሲ ጨዋታውን 4-3 ረታ። አራተኛ ተከታታይ ድሉ ማለት ነው።

ክሊፍ ብራውን እና ሌሎች የአካባቢው ሰዎች ጭፈራውን አቀለጡት።

ማንቸስተር የተወለደው የቼልሲ ተጫዋች የእግር ኳስ ጫማው ላይ የሴይንት ኪትስ ኤንድ ኔቪስ ባንዲራ ለጥፏል። ለወንድ አያቱ ሀገር ነው ይህን የሚያደርገው።

"እውነት ለመናገር ኮል ፓልመርን አይተህ ሴይንት ኪትስ ኤንድ ኔቪስ አትመጣልህም" ይላሉ የሀገሪቱ ስፖርት ሚኒስትር ሳማል ዳጊንግስ።

"ነገር ግን ትክክለኛውን ማንነታቸውን የሚያሳይ ነው። እኛ የሁሉም ዘር ተዋፅኦ ነን።"

የኮል ፓልመር ወንድ አያት ስቴሪ የተወለዱት በሴይንት ኪትስ ኤንድ ኔቪስ በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 27/1953 ነው።

በ1955 የስቴሪ እናት አባት ኢስቴል ዋርድ እና ጄምስ ፓልመር ልጆቻቸውን ጥለው ለቤተሰባቸው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ለመሰደድ ወሰኑ።

በወቅቱ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት እያገገመች ያለችውን ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ለማገዝ በርካቶች ከካሬቢያን ሀገራት ይመጡ ነበር።

የዩኬ መንግሥት ምጣኔ ሀብቱን ለማንሰራራት የሰው ኃይል ይፈልጋል። የካሬቢያን ሀገራትም በወቅቱ ችግር ላይ ነበሩ። ኑሮ የከበዳቸው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም አቅንተው ሕይወታቸውን ይቀይራሉ።

በ1960 ስቴሪ በስድስት ዓመታቸው ወደ እንግሊዝ አቀኑ። መጀመሪያ በጀልባ ወደ ባርቤዶስ ከዚያም ወደ ሳውዝአምፕተን።

የስቴሪ ወላጆች በማንቸስተሯ ሞስ ሳይድ መንደር የተደላደለ ኑሮ መሥርተው ጠበቋቸው።

ፓልመር ከልጅነቱ ጀምሮ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ ነበር። ሲያድግ መሆን የሚፈልገው ዌይን ሩኒን ነበር። ባደገበት ሰፈር ኳስ ሲያንቀረቅብ ያዩት ብዙዎች ትልቅ ደረጃ እንደሚደርስ አልተጠራጠሩም።

"ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ?" ለሚለው ጥያቄ ሁሌም መልሱ "እግር ኳስ ተጫዋች" የሚል ነው።

ፀባዩ ሸጋ ነው። አባቱ "እሱ ታዋቂ መሆን አይፈልግም። ኮከብ መባል አያሳስበውም። ኳስ መጫወት ብቻ ነው የሚፈልገው" ሲሉ ይመሰክራሉ።

በአንድ ወቅት ከጨዋታ በኋላ ምን መመገብ ደስ ይልሀል ተብሎ ተጠይቆ "የድንች ጥብስ" በማለቱ የማኅበራዊ ሚድያ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በየጊዜ ቤተሰቡን ጥየቃ ወደ ማንቸስተር ይመላለሳል።

አባቱ ጄርሜይን (የስቴሪ ልጅ) እና እናቱ ሜሪን ሳይጎበኝ መሰንበት አይችልም።

ምንም እንኳ በሴይንት ኪትስ ኤንድ ኔቪስ ተወዳጁ ስፖርት ክሪኬት ቢሆንም ስቴሪ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከመጣ በኋላ ለእግር ኳስ ያለው ፍቅር እየጨመረ መጣ።

ስቴሪ ከዘመዱ ኦሲ ማርቲን ጋር በመሆን ዌስት ማንቸስተር ቦይስ ለተባለ ቡድን መጫወት ጀመሩ።

"ክረምትም ሆነ አልሆነ ሁሌም እሑድ ከሰዓት ወጥተን እንጫወት ነበር" ሲል ኦሲ ማርቲን ያስታውሳል።

ስቴሪ ማንቸስተር ከተማን ቤቱ አደረጋት። ወደፊት ቤተሰቡን የሚያሳድግባት ከተማ እንደምትሆን አያውቅም ነበር።

ስቴሪ አሁን የ71 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ነው። የልጅ ልጁ ባሳከው ነገር የሚሰማው ኩራት ወደር የለውም። የልጅ ልጁ እንግሊዝ አሉኝ ከምትላቸው እግር ኳስ ተጫዋቾች ተርታ ተመድቧል።

ፓልመር ከአባቱ ጋር ኳስ እየተጫወተ ነው ያደገው። አባቱ ጀርሜይን በእሑድ ሊግ የሚጫወተው ብላክቦይ ኤፍሲ ተጫዋች ነው። ጀርሜይን ሲጫወት ፓልመር በአባቱ ጃኬት ተጠቅልሎ ይመለከታል።

ፓልመር ገና ስምንት ዓመት ሳይሞላው በማንቸስተር ሲቲ መልማዮች ዓይን ውስጥ ገባ።

በአውሮፓውያኑ መስከረም 2023 ከሲቲ ቼልሲን የተቀላቀው ፓልመር ለሰማያዊዎቹ በ54 ጨዋታዎች 36 ግቦችን አስቆጥሯል። በአውሮፓ ዋንጫ ፍፃሜ ስፔን ላይ ግብ ማስቆጠርም ችሏል።

በስኬት ላይ ስኬት ቢደርብም ፓልመር የመጣበትን የሚረሳ አይደለም።

እግር ኳስ መጫወቻ ጫማው ላይ የእንግሊዝ እና የሴይንት ኪትስ ኤንድ ኔቪስ ባንዲራ ተለጥፏል።

"አራት ወይም አምስት ዓመቴ ሳለ አባቴ ሁሌ ይዞኝ ይወጣል። ዝናብ ቢኖርም ባይኖርም ይዞኝ ወደ አካባቢው ፓርክ ይሄዳል። የአባቴ ቤተሰቦች ከሴይንት ኪትስ ኤንድ ኔቪስ ናቸው። አባቴ ብርድ አይወድም ግን ለኔ ሲል ያደርገዋል። ባንዲራውን ጫማዬ ላይ የማደርገው ለአባቴ እና ለቤተሰቡ መታሰቢያ እንዲሆን ነው" ሲል ፓልመር በ2022 ተናግሮ ነበር።

ፓልመር ጎል ካስቆጠረ በኋላ ልክ እንደበረደው ሰው አጆቹን አጣምሮ ክርኑን ያሻሻል። ለዚህ ነው "ኮልድ" የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው።

ሴይንት ኪትስ ኤንድ ኔቪስ ያሉ ሕፃናት ጎል ካስቆጠሩ በኋላ እንደ ፓልመር ማድረግ ልማዳቸው ሆኗል።

ትንሿ የካሬቢያን ሀገር የሕዝብ ቁጥሯ 47 ሺህ 775 ነው። ሰባት የፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ስታድየማቸው ውስጥ ያለው የመቀመጫ ብዛት ከሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥር ይልቃል።

ፍሪድም ኤፍ የተባለው የራድዮ ጣቢያ ስለፓለመር ሳያወራ አይውልም። አሁን አሁን በሀገሪቱ እግር ኳስ በጣም ተወዳጅ ስፖርት እየሆነ መጥቷል።

ባለፈው ታኅሣሥ የፓልመር አባት የልጁ ስም ያለባቸው የቼልሲ ማሊያዎችን ለአንድ የስፖርት አካዳሚ አበርክተዋል።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴረንስ ድሪው ወደ አካዳሚው አዘውትረው ይመጣሉ። ታዳጊዎቹን ያበረታታሉ።

እርግጥ ነው ሴይንት ኪትስ ኤንድ ኔቪስ በፊፋ የሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ 144ኛ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው። የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ከሀገር ቤት እና ከውጭ የተውጣጡ ናቸው።

የራሽፈርድ ዘመድ የሆነው ሎይስ ሜይናርድ እና የሊቨርፑል ታዳጊው ካይል ኬሊ የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ናቸው።

የፓልመር አባላት ባለፈው ዓመት ወደ ሴይንት ኪትስ ኤንድ ኔቪስ ተጉዞ አባቱ የተወለደበትን ቦታ ጎብኝቶ ተመልሷል። ፓልመር አንድ ቀን ወደዚህ መምጣቱ እንደማይቀር ይናገራል። ነገር ግን በሴይንት ኪትስ በጣም ታዋቂ ከመሆኑ የተነሳ "የፖሊስ እጀባ ሳያስፈልገው አይቀርም" ይላል።

በሀገሪቱ ተወዳጅ የሆኑት ክለቦች ማንቸስተር ዩናይትድ እና አርሰናል ናቸው። አሁን አሁን ግን ቼልሲን የማይደግፉ ሳይቀሩ ለፓልመር ሲሉ የሰማያዊዎቹን ጨዋታ ያያሉ።