ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባለፉት ቀናት 15 የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች መታሰራቸውን የንቅናቄው አስተባባሪዎች ተናገሩ
ከጤና ባለሙያዎች የከፊል የሥራ ማቆም አድማ መምታት ጋር በተያያዘ 15 የሚሆኑ ባለሙያዎች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የንቅናቄው አስተባባሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
የደሞዝ እና የጥቅማ ጥቅምን ጨምሮ የጤና ሥርዓቱ እንዲስተካከል ጥያቄ ያቀረቡት የጤና ባለሙያዎች፤ የንቅናቄው "መሪዎች" ናችሁ የተባሉ በርካታ ባለሙያዎች "በመላው አገሪቱ" እየታሰሩ እና ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው እንደሆነ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አስተባባሪዎች ገልፀዋል።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንትን ጨምሮ በርካታ ባለሙያዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፤ መንግሥት የጤና ባለሙያዎችን "የዳቦ ጥያቄ" ከመመለስ ይልቅ "አፈና እና ወከባ" እያደረገ ነው ብለዋል።
እየታሰሩ ያሉት ባለሙያዎች በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ክልሎች ድንገተኛ ክፍልን ጨምሮ አገልግሎት እየሰጡ የነበሩ "ጋዎን የለበሱ" ባለሙያዎች መሆናቸውን አንድ አስተባባሪ ተናግረዋል።
የጥቁር አንበሳ እና ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ባለሙያዎችን ጨምሮ፣ የፈለገ ሕይወት፣ የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል፣ የለኩ ሆስፒታል (ሲዳማ ክልል)፣ የጎንደር ዩኒቨርስቲ፣ አዲስ ዓለም፣ ነፋስ መውጫ ሆስፒታሎች ባለሙያዎች መታሰራቸውን ገልፀዋል።
ትናንት ረቡዕ ግንቦት 6/2017 ዓ.ም. ጠዋት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሐኪሞች ዶ/ር ሳዶር በረከት እና ዶ/ር ኢፋ አዱኛ ከማደሪያቸው ወደ ሆስፒታል ሲገቡ በፖሊስ እንደተያዙ የዓይን እማኞች እና አስተባባሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሁለቱ ሐኪሞች "እንቅስቃሴውን ስለደገፉ" አዲሱ ገበያ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን የተናገሩት አንድ አስተባባሪ፤ "የፖለቲካ አጀንዳ አላችሁ ብለው እየመረመሯቸው ነው" ብለዋል።
ከሲዳማ ክልል ለኩ አጠቃላይ ሆስፒታል ዶ/ር ደረጀ የተባሉ የማህፀን እና ፅንስ ሐኪም፤ "እስከ 11፡00 ሰዓት ድረስ ቀዶ ሕክምና ሠርቶ ማደሪያው ላይ ነው መጥተው የያዙት" ብለዋል።
"ዶ/ር ደረጀ እስከ ትናንት [ረቡዕ] ድረስ ሥራ አላቆመም፤ አድማው ውስጥ አልነበረም። አንድ ብቻውን ስለሆነ ሥራ ሊያቆም አይችልም። እያንዳንዱን ቀዶ ሕክምና ገብቶ ሲሠራ ነበር። ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ነው የያዙት" በማለት ስለ እስሩ ተናግረዋል።
ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ዶ/ር ሀብታሙ መንክር የኦርቶፔዲክስ (የአጥንት ሕክምና) ፕሬዚደንት ሐኪም ዛሬ ግንቦት 7/2017 ዓ.ም. ከሆስፒታል ተወስደው መታሰራቸውንም የንቅናቄው አስተባባሪ ገልፀዋል።
ባለሙያዎቹ ከእስራቱ ባለፈ ከመንግሥት እና ከሆስፒታል የሥራ ኃላፊዎች ወከባ እና ዛቻ እየደረሰባቸው እንደሆነም ገልፀዋል።
በርካታ ሆስፒታሎች በሥራ ላይ የማይገኙ ባለሙያዎች ላይ "አስተዳዳራዊ እርምጃ" እንደሚወስዱ ማስጠንቀቂያዎችን አውጥተዋል።
ማስተማሪያ ሆስፒታሎችም ሥራ የማይገቡ ሬዝደንት ሐኪሞች "መኖሪያ ቤት" ለቀው እንዲወጡ አስታውቀዋል።
"ችግሮቻችን ለመስማት የተዘጋጀ አካል የለም" ሲሉ እስካሁን ከመንግሥት አዎንታዊ ምላሽ አንዳላገኙ የተናገሩ አንድ አስተባባሪ፤ ሆስፒታሎች አድማ በመቱ ባለሙያዎች ፈንታ ተጠባባቂ ባለሙያዎችን እየጠሩ እና የቅጥር ማስታወቂያ እያወጡ እንደሆነም ጠቁመዋል።
"ማስፈራራቱ፣ ዛቻው፣ ደብዳቤ መፃፉ፣ ሆስፒታል ውስጥ ወታደሮች ማብዛት ቀጥሏል። ጥቁር አንበሳም፣ ቅዱስ ጳውሎስም ትናንት [ረቡዕ] በአካል ሄጄ ሁለቱን ሆስፒታሎች አይቻለሁ። በፖሊስ ተከበው ነው ያሉት" ሲሉ እየደረሰብን ነው ያሉትን ጫና ገልፀዋል።
ባለፈው ሰኞ ምሽት በብሔራዊው ቴሌቪዥን ላይ የቀረቡት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ መንግሥት የጤና ባለሙያዎቹን ጥያቄ ለመመለስ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የመንግሥት እርምጃ ንቅናቄው የበለጠ እንዲቀጣጠል እያደረገ ነው የሚሉት አስተባባሪው፤ ክፍት የነበሩት የሕክምና ክፍሎች በጫናው ምክንያት አገልግሎት ማቆማቸውን ገልፀዋል።
ሌላ አስተባባሪ በበኩላቸው "ነገሩን እያባባሱት ነው። በመካከል ሕዝቡ ነው ሊጎዳ የሚችለው። . . . እስከ ችግሩም ቢሆን ላቡን ያፈሰሰ፤ ደሙን የለገሰ ባለሙያ ይህ ሁሉ ውርደት፣ ድብደባ፣ ወከባ የሚገባው አይደለም" ሲሉ መንግሥት እየወደሰ ያለውን እርምጃ "ትልቁ ስህተት" ብለውታል።
"ይህን እንቅስቃሴ በኃይል ማስቆም አይቻልም" ያሉ ሌላ አስተባባሪ፤ የታሰሩ የጤና ባለሙያዎች ካልተፈቱ ከነገ አርብ ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ አድማ እንደሚመቱ አስጠንቅቀዋል።
በሥራ ማቆም አድማው ታካሚዎች እየተስተጓጎሉ እንደሆነ ያልሸሸጉት አስተባባሪው፤ "ታማሚዎች ቁጭ ብለው ወረፋ እየጠበቁ ነው፤ ባለሙያው ደግሞ የለም" ሲሉ ለዚህ ኃላፊነቱን የሚወስደው ግን መንግሥት ነው ብለዋል።
'የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ' በሚል ስያሜ የደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄን ጨምሮ 12 ጥያቄዎችን ያነሱ ባለሙያዎች፤ የ30 ቀናት የማስጠንቀቂያ ጊዜ ከሰጡ በኋላ ከግንቦት 5/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ከፊል የሥራ ማቆም አድማ መምታታቸውን አስታውቀዋል።
ቢቢሲ ከጤና ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ለቀናት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።