ማክሮን ከሥልጣን የለቀቁትን ጠቅላይ ሚኒስትር መልሰው ሾሙ

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከአራት ቀናት በፊት ሥልጣን የለቀቁትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዳግመኛ ሾሙ።

የፈረንሳዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰባስሽን ሌኮርኑ አንድ ወር ሳይሞላቸው ሥልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል።

"ሥራውን አልፈልገውም፤ ኃላፊነቴን ጨርሻለሁ" ብለው ከሥልጣን የለቀቁት ሰባስሽን ሌኮርኑ ወደ ሥልጣን መመለሳቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

በድጋሚ የተሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር እስከ ሰኞ ድረስ የቀጣዩን ዓመት በጀት ለፓርላማ ማቅረብ አለባቸው።

የ39 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከማክሮን ዋነኛ ደጋፊዎች አንዱ ናቸው።

በኤክስ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት "ፕሬዝዳንቱ በሰጡኝ ኃላፊነት መሠረት የፈረንሳይን በጀት ከማቅረብ ባሻገር ፈረንሳውያን ለሚገጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ አበጃለሁ" ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት "ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኜ ለመቀጠል የሚያስችል ሁኔታ አልተሟላም" ሲሉ ለሥልጣናቸው መልቀቅ ምክንያት የሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

የፈረንሳይን እዳ ከመክፈል ጋር በተያያዘ የአገሪቱ ፖለቲከኞች ልዩነታቸው እየሰፋ መጥቷል።

በአንድ ዓመት ሦስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተለዋውጠዋል።

ከ2024 አንስቶ የፈረንሳይ ፖለቲካ ነውጥና ውጥረት በዝቶበታል።

የማክሮን ፓርቲ በአውሮፓ ምክር ቤት ውጤት ካጣ በኋላ በምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ለማግኘት ድንገተኛ ምርጫ አከናውነዋል።

ሆኖም ግን ምርጫው ምክር ቤቱ በተለያየ ጽንፍ ያሉ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች የሚፎካከሩበት እንዲሆን አድርጓል።

ማይክል ባርነር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ ሦስት ወራት ብቻ ነው ያገለገሉት።

ተከታያቸው ፍራንኮስ ባይሩ ለዘጠኝ ወራት ብቻ አገልግለው የበጀት ዕቅዳቸው በምክር ቤት ተቀባይነት ሳያገኝ ከሥልጣን ወርደዋል።

በ2024 የፈረንሳይ የበጀት ጉድለት ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ገቢ አንጻር 5.8 በመቶ ሲደርስ፤ አገር አቀፍ ዕዳ 114 በመቶ ደርሷል።

ከግሪክ እና ጣልያን ቀጥሎ በአውሮፓ ከፍተኛ ዕዳ ነው። እያንዳንዱ ፈረንሳዊ 50,000 ዩሮ ዕዳ አለበት ማለት ነው።

ማክሮን የቀራቸው የሥልጣን ዘመን 18 ወራት ብቻ ናቸው። በሕዝብ ያላቸው ተቀባይነት 14 በመቶ ደርሷል።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰባስሽን ሌኮርኑ የመተማመኛ ድምጽ ይሰጥባቸዋል።

ቀኝ ዘመም ፖለቲከኛ ጆርዳን ባርዳላ ከሥልጣን የለቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር በድጋሚ መሾማቸው "መጥፎ ቀልድ ነው" ብለዋል።

ፓርቲያቸው መተማመኛ ድምጽ እንደማይሰጣቸውም አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሦስት ሳምንታት ውስጥ ካቢኔ ቢያዋቅሩም ብዙም ሳይቆዩ ከሥልጣን ወርደዋል።

የሶሻሊስት ፓርቲ መሪው ኦሊቨር ፋውር "ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መተማመኛ ድምጽ ለመስጠት የሚያበቃ ድጋፍ አላገኘንም" ብለዋል።

የኮምኒስት ፓርቲ መሪው ፋቢያን ራሰል እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተቀባይነት አያገኙም።

የግሪንስ ፓርቲ መሪ ማሪን ቶንደልር በበኩላቸው፤ ማክሮን ለግራ ዘመሞች "ምንም ተጨባጭ ነገር አላቀረቡም" ብለው "ነገሮች እየተባባሱ ይሄዳሉ" በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ማክሮንና በድጋሚ የሾሟቸው ጠቅላይ ሚኒስትር የመንግሥትን የበጀት ጉድለን በአሥር ቢሊዮን ይሮ መቀነስ ይኖርባቸዋል። የአገሪቱ ብሔራዊ ባንክ እንዳለው የምጣኔ ሃብት ቀውሱ ሊባባስ ይችላል።