እስራኤል በሊባኖስ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ማዕከል ላይ በፈጸመችው ጥቃት 15 የነፍስ አድን ሰራተኞች ተገደሉ

እስራኤል በሰሜን ምስራቅ ሊባኖስ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ማዕከል ላይ በፈጸመችው ጥቃት 15 የነፍስ አድን ሰራተኞች መገደላቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።

ሐሙስ፣ ኅዳር 6/ 2017 ዓ.ም በማዕከሉ ላይ የተፈጸመው ይህ ጥቃት በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ምላሽ እየሰጡ በነበሩ የነፍስ አድን ሰራተኞች ላይ የደረሰ የከፋ ጥቃት ተብሏል።

በዱሪስ ከተማ በተፈጸመው ጥቃት ከሊባኖስ መንግሥት ጋር አብሮ የሚሰራው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ህንጻ ወድሟል።

ኤጀንሲው በኢራን ከሚደገፈው የሄዝቦላህ ቡድን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ተገልጿል።

በዚህ ጥቃት በከተማዋ የኤጀንሲው ኃላፊ ቢላል ራድ መገደላቸውን የግዛቲቷ አስተዳደር ባቺር ክሆድር ገልጸዋል።

የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር “አረመኔያዊ” ሲል በፈረጀው በዚህ ጥቃት ላይ የእስራኤል ጦር ምንም አይነት መግለጫ አልሰጠም።

የሊባኖስ የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ፍለጋዎችን፣ ነፍስ የማዳን ስራዎችን እና የእሳት አደጋ የማጥፋት ምላሽን ጨምሮ የአደጋ ጊዜ አገልግሎቶችን የሚሰጥ መስሪያ ቤት ነው።

በሌላኛው ደቡባዊ ናባቲህ ግዛት ሐሙስ ዕለት በተፈጸመ ሌላ የእስራኤል ጥቃት በሳሊም ከተማ የሚገኘው የዚሁ የሲቪል መከላከያ ማዕከል ቅርንጫፍ ወድሟል።

በዚህ ጥቃት አምስት የህክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ መንግስታዊው የዜና ወኪል ኤንኤን ዘግቧል።

እስራኤል ከመስከረም ጀምሮ እየፈጸመችው ባለው የአየር ጥቃት ቢያንስ 192 የድንገተኛ አደጋ እና የጤና ሰራተኞች መገደላቸውን የሊባኖስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል።

እስራኤል በቅርብ ቀናት ውስጥ በመዲናዋ ቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች እየፈጸመችው ያለችውን የአየር ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።

እስራኤል ለአራተኛ ቀን የማያባራ የአየር ጥቃት እየፈጸመች ሲሆን ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት ያላቸው መሰረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነው ሲል መከላከያዋ አስታውቋል።

በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ዓለም አቀፍ ጥሪዎች እየቀረቡ ሲሆን የአሜሪካ ባለስልጣናት የመጀመሪያውን የስምምነት ሃሳብ ለሊባኖስ ባለስልጣናት መቅረባቸው ተገልጿል።

ማንኛውም ስምምነት በሄዝቦላ እና በእስራኤል መካከል በአውሮፓውያኑ 2006 የተከሰተውን ጦርነት የቋጨው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 1701 በተሰኘው ውሳኔ መሰረት መሆን እንዳለበት የሊባኖስ መንግሥት አጽንኦት ሰጥቷል።

የተመድ የውሳኔ ኃሳብ እስራኤል እና ሊባኖስ ከሚዋሰኑበት በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘው 'ብሉ ላይን' በተሰኘው በአገራቱ ይፋዊ ባልሆነው ድንበር አካባቢ የሄዝቦላህ ተዋጊዎች እንዲርቁ ማድረግን ያካተተ ነው።

ሊደረግ የሚችለው አዲሱ ስምምነት የሊባኖስ ጦር አባላት በአካባቢው እንዲሰማሩ እንዲሁም አፈጻጸሙን መከታተል የሚያስችል ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል ቢባልም ዝርዝሩ ግልጽ አልሆነም።

እስራኤል በበኩሏ ስምምነቱን በቅርበት ለመቆጣጠር በሊባኖስ ውስጥ የመንቀሳቀስ መብት እንዲኖራት ትፈልጋለች።

ሄዝቦላህም ሆነ የሊባኖስ መንግሥት ይህንን ጥያቄ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆናቸውን የሚያሳዪ ፍንጮች የሉም።