ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል ጋዛውያንን ሆን ብላ በገፍ በማፈናቀል የጦር ወንጀሎች በመፈጸም ተከሰሰች
እስራኤል በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን ሆን ብላ በገፍ በማፈናቀል የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል መፈጸሟን ሂውማን ራይትሰ ዋች አስታወቀ።
ባለፈው ዓመት 90 በመቶ የሚሆነው፣ 1.9 ሚሊዮን ህዝብ ቀያቸውን ለቀው እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል። እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ያስገባቻት ጋዛ 79 በመቶ የሚሆነው መሬቷም እስራኤል የማፈናቀል ትዕዛዝ ቁጥጥር ስር ያደረገችው እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።
ይህ ሁኔታ” በግዳጅ ማፈናቀል” እንደሆነ የጠቀሰው የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት “ስልታዊ እና የመንግሥት ፖሊሲ” አካል እንደሆነ መረጃዎቹ መጠቋማቸውን አክሏል።
እስራኤል የፈጸመቻቸው ድርጊቶች የዘር ማጽዳት ጋር ተመሳሳይነት አለው ብሏል።
እስራኤል በበኩሏ ሪፖርቱን አጣጥላ “ሙሉ በሙሉ ስህተት እና ከእውነታ የራቀ ነው” ብላለች።
“በሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ከወጣው በተጻራሪ እስራኤል ጥረቷ የሃማስን የሽብር አቅም በማውደም ላይ ብቻ ያተኮረ እንጂ በጋዛ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ አይደለም” ሲሉ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኦረን ማርሞርስቴይን በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
አክለውም እስራኤል “በጦርነት ህግ መሰረት ዘመቻዋን ትቀጥላለች” ብለዋል።
ሂውማን ራይትስ ዋች በዚህ ሪፖርቱ ሃማስ በሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ ቤቶች እና መሰረተ ልማቶች በመንቀሳቀስ እንዲሁም ዜጎችን በሽፋንነት ተጠቅሟል ሲል ከሷል።
ሪፖርቱ የወጣው እስራኤል በሰሜን ጋዛ እየወሰደችው ያለውን የተቀናጀ የምድር ጥቃት ተከትሎ ባለፉት አምስት ሳምንታት እስከ 130 ሺህ የሚደርሱ ዜጎች እንዲፈናቀሉ መደረጋቸውን ተከትሎ ነው።
በጃባሊያ፣ ቤይት ላሂያ እና ቤይት ሃኖን ከተሞች 75 ሺህ ነዋሪዎች የውሃ እና የምግብ አቅርቦት እየተመናመነ በመጣ ከበባ ውስጥ መሆናቸው የተባበሩት መንግሥታት ይፋ አድርጓል። የእስራኤል ጦር በበኩሉ ሃማስን ዳግም እንዳያሰራራ ለመከላከል ነው ብሏል።
ሂውማን ራይትስ ዋች ፍልስጤማውያን “እንዲሰፍሩ በተዘጋጁባቸው የተጠበቁ ስፍራዎች እና መውጫ መንገዶች በተደጋጋሚ በእስራኤል ወታደሮች ጥቃት ደርሶባቸዋል” ብሏል።
የእስራኤል ባለስልጣናት ከሽርፍራፊ በስተቀር መሰረታዊ የሰብዓዊ እርዳታ፣ ውሃ፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ ውሃ እና ነዳጅ ሰላማዊ ዜጎች እንዳይደርሳቸው ማገዳቸውን ተቋሙ አስፍሯል። በተጨማሪም እስራኤል እንደ ሆስፒታል፣ ዳቦ መጋገሪያዎች ያሉ የማህበረሰቡ መገልገያዎች ላይ ጥቃቶችን በመፈጸም ማውደማቸው ተገልጿል። የእስራኤል ጦር “ሆን ብሎ የሰላማዊ ዜጎችን መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም መኖሪያ ቤቶችን አውድሟል” ብሏል።
“ጥፋቱ በጣም የከፋ ከመሆኑ የተነሳ በርካታ ነዋሪዎችን ሆን ብሎ በዘላቂነት የማፈናል አላማ ማንገቡን ያሳያል” ሲል አስጠንቅቋል።
የእስራኤል ሚኒስትሮች የጋዛን ግዛት በመቀነስ መሬቱን ለእስራኤላውያን ሰፋሪዎች እናከፋፍላን ማለታቸው በሪፖርቱ ዋቢ ተደርገዋል።