ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መከላከያ ሠራዊት ብሔራዊ ጥቅሞችን በማስከበር ሂደት ለሚመጣ "የደኅንነት አጣብቂኝ" እንደሚዘጋጅ ቃል አቀባዩ ተናገሩ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፤ እንደ "በውሃ የመጠቀም መብት" እና "የወደብ ጥያቄ" ያሉ ብሔራዊ ጥቅሞችን በማስከበር ሂደት ውስጥ ሊከሰት ለሚችል "የደኅንነት አጣብቂኝ" መዘጋጀት እንዳለበት የሠራዊቱ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄነራል ጌትነት አዳነ ተናገሩ።
በቅርቡ ለመከላከያ ሠራዊት አባላት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች የተሰጠው የማዕረግ ዕድገት "ተጨማሪ ግዳጅ እና ተልዕኮንም ታሳቢ ያደረገ" እንደሆነ የሠራዊቱ የሰው ኃብት አመራር ዋና መመሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል አጫሉ ሸለመ ገልጸዋል።
ሁለቱ ጄነራሎች፤ ከሳምንት በፊት የተሰጠውን የጦር መኮንኖች የማዕረግ ዕድገት በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት አርብ መስከረም 16/2018 ዓ. ም. በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በተላለፈ ቃለ መጠይቅ ነው።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ መስከረም 10 ቀን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቅራቢነት ለ66 መኮንኖች የማዕረግ ዕድገት መሰጠቱ ይታወሳል።
ከፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ዕድገቱን ከተቀበሉት የጦር መኮንኖች መካከል አራቱ ወደ የሙሉ ጄነራልነት ማዕረግ አግኝተዋል።
የሙሉ ጄነራልነት ማዕረግ ከተሰጣቸው መካከል ከዚህ ቀደም በሌተናል ጄነራልነት ማዕረግ ላይ የነበሩት የጠቅላይ ኤታማዦር ሹም አማካሪ ዓለምሸት ደግፌ እና የመከላከያ ምህንድስና ዋና መምሪያ ኃላፊ ደስታ አብቼ ይገኙበታል።
የመከላከያ ትምህርት እና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ይመር መኮንን እና የመከላከያ ኢንስፔክተር ኃላፊ ድሪባ መኮንንም ወደ ሙሉ ጄነራልነት አድገዋል።
የሠራዊቱ የሰው ኃብት አመራር ዋና መመሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል አጫሉ፤ ይህ የማዕረግ ዕድገት የተሰጠው የመከላከያ ሠራዊት ሕጎች እና አሠራሮች ተጠብቀው እንደሆነ ተናግረዋል።
የማዕረግ ዕድገቱ ሲሰጥ ታሳቢ ከሚደረጉ መስፈርቶች ውስጥ "ወታደራዊ ግዳጅ አፈጻጸም"፣ "የአመራር ችሎታ"፣ "ብቃት" እና "ሥነ ሥርዓት አክባሪነት" እንደሚገኙበት ዘርዝረዋል።
ሹመቱን የሚያገኙ መኮንኖች ስብጥር "ኢትዮጵያን እንዲመስል" ማድረግ እና "ክፍት የሹመት ቦታ" መኖርም ከግምት ውስጥ እንዲገቡ አስረድተዋል።
ሌተናል ጄነራል አጫሉ፤ "ሹመት ቀጣይ ሊኖር የሚችለውን ግዳጅ መሸከም እንዲችል ኃላፊነትን ተቀብሎ የመሥራት ጉዳይ" መሆኑን ተናግረዋል።
የጦር መኮንኖች ወታደራዊ ሹመት የሚያገኙት "ተጨማሪ ግዳጅ እና ተልዕኮ መሸከም እንደሚገባ ታሳቢ ተደርጎ" እንደሆነም ገልጸዋል።
በቅዳሜ ዕለቱ ሹመት የብርጋዴር ጄነራልነት ማዕረግን ያገኙት የመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጌትነት አዳነ በበኩላቸው፤ የተሰጠው ሹመት "የሠራዊቱን ዝግጁነት" እንደሚያጠነክር እና "ለወደፊት ተልዕኮ በጎ ተጽእኖ" እንደሚፈጥር አንስተዋል።
የማዕረግ ዕድገቱ "ከብሔራዊ ጥቅም" እና "ሉዐላዊነትን ከማጽናት" አንጻርም መታየት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅት መንግሥት "ብሔራዊ ጥቅም" በሚል በአጀንዳነት ያቀረባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፤ ከእነዚህም መካከል "በውሃ የመጠቀም መብት" እና "የወደብ ጥያቄ" እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
"ጋዝ፣ የኒውክሌር ማብላያ ፕላንት፣ የማዳበሪያ ኢንዱስትሪዎች መመሥረት" ጉዳዮችም ከአጀንዳዎቹ መካከል እንደሆኑ አንስተዋል። ብርጋዴር ጄነራል ጌትነት፤ "በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እነዚህን ብሔራዊ ጥቅሞችን 'እነዚህ ናቸው ላሳካቸው የምፈልገው' እስካለ ድረስ ሠራዊት ደግሞ መዘጋጀት አለበት" ብለዋል።
ሠራዊቱ የሚያደርገው የመጀመሪያ ዝግጅት አንጀንዳዎቹን በማስፈጸም ሂደት ውስጥ በሌላ አካል ሊፈጠር ከሚችል "ወደ ኃይል አማራጭ መምጣት" ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተናግረዋል።
"የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ይህንን ጥያቄ ሲያነሳ 'በሰላማላዊ መልኩ እፈታዋለሁ' ብሎ ነው የሚያነሳው። ግን ደግሞ በዚህ ውስጥ የሚገባ security dilemma የሚባል ነገር አለ" ሲሉ በሂደቱ የደኅንነት አጣብቂኝ ሊፈጠር እንደሚችል ጠቁመዋል።
" 'ኢትዮጵያ ይህንን ካነሳችማ እንዲህ ሊሆን ነው' ብሎ ወደ ኃይል አማራጭ የሚመጣ ነገር ከሆነ ሠራዊት መዘጋጀት አለበት ማለት ነው" ሲሉም ሐሳባቸውን አብራርተዋል።
በሠራዊቱ በኩል የሚደረገው ዝግጅትም "የመንግሥትን ተልዕኮ እና ትዕዛዝ ያደረገ" እንደሚሆንም አክለዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ይህንን የተናገሩት የኢትዮጵያ መንግሥት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ እያነሳ ያለው የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ጎልቶ እየወጣ ባለበት ወቅት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት መስከረም 6/2018 ዓ.ም. ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ "የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና ለዘላለም" እንደማትኖር መናገራቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ "አይቀሬ" መሆኑን በአጽንኦት የገለጹት ዐቢይ፤ ሀገራት "በፈጠነ ጊዜ ራሳቸውን ለድርድር ዝግጁ" እንዲያደርጉ አሳስበዋል።