የተመድ አባላት መዋጮ እየከፈሉ ባለመሆኑ ተቋሙ የፋይናንስ ቀውስ ሊገጥመው እንደሚችል ተገለጸ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት የሚጠበቅባቸውን መዋጮ እየከፈሉ ባለመሆኑ ተቋሙ "በአጭር ጊዜ ውስጥ የፋይናንስ ቀውስ" ሊገጥመው እንደሚችል ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አስጠነቀቁ።

ተመድ የፊታችን ሐምሌ ላይ ያለው ገንዘብ ሊያልቅ እንደሚችል እና ይህም ሥራዎቹን እንደሚያሰናክል ተናግረዋል።

ተቋሙ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ እንዳይወድቅ 193ቱ አባል አገራት መዋጮ በመክፈል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጉቴሬዝ በጻፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል።

ለተመድ ከፍተኛውን ገንዘብ የምትለግሰው አሜሪካ ለፀጥታ አስከባሪዎች ትሰጥ የነበረውን ክፍያ ማቋረጧ ተቋሙን አጣብቂኝ ውስጥ ከትቷል።

አሜሪካ የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ ከሌሎችም የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋማት ለቅቃ ወጥታለች።

በትራምፕ ውሳኔ መሠረት አሜሪካ ራሷን ከተቋሙ ስታገል፤ ሌሎች አገራት ደግሞ ክፍያ ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆኑም።

ተቋሙ እአአ በ2025 መጨረሻ የፋይናንስ ሥርዓቱን ቢለውጥም ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ ሊገባ ይችላል።

በተመድ ዋና መቀመጫ ጄኔቫ ገንዘብ ለመቆጠብ ሲባል አሳንሱር እና የሙቀት ማቀዝቀዣ መሳሪያዎች አንዳንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል።

ጉቴሬዝ በጻፉት ደብዳቤ ገንዘብ አንከፍልም ያሉትን አገራት ባይዘረዝሩም፤ ተቋሙ ከዚህ ቀደም ከገጠመው የፋይናንስ ቀውስ "የአሁኑ እጅግ የከፋው ነው" ብለዋል።

"ቃል የተገቡ ክፍያዎችን አለመፈጸም ቋሚ በጀት ላይ ጫና ፈጥሯል። የተቋሙ ታማኝነት የሚወሰነው አባል አገራት ስምምነታቸውን በሚያከብሩት ልክ ነው" ሲሉም በደብዳቤያቸው አስታውቀዋል።

በ2025 ከሚጠበቀው ክፍያ 77% ብቻ እንደተሸፈነ ተናግረዋል።

"በጣም አጣዳፊ ችግር ነው። መዋጮ ሳይከፈል በጀት መመደብም ሆነ ክፍያ መፈጸም አንችልም። በዚህ ወር ብቻ ገንዘብ ሳንሰበስብ 227 ሚሊዮን ዶላር ለማውጣት ተገድደናል" ብለዋል ዋና ጸሐፊው።

የተመድ የተለያዩ ድርጅቶች የሚያስፈልጋቸውን ያህል ገንዘብ አሟልተው ሰብስበው ባያውቁም ላለፉት 12 ወራት የገጠማቸው ቀውስ ከዚህ ቀደም ያልታየ ነው።

ጉቴሬዝም በጻፉት ደብዳቤ "ሁሉም አባል አገራት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ በጊዜው እና ሙሉ በሙሉ መፈጸም አለባቸው። ካልሆነ የፋይናንስ ቀውሱ አይቀሬ ነው" ሲሉ አሳስበዋል።

በ2025 አሜሪካ ከተመድ ዓመታዊ በጀት የሚጠበቅባትን ድርሻ አልከፈለችም። ለፀጥታ አስከባሪዎች ከሚከፈለው ገንዘብ ውስጥም የምትሰጠው 30 በመቶውን ብቻ እንደሆነ ገልጻለች።

ትራምፕ ለተመድ የሚፈጸም ክፍያ "የአሜሪካውያን ግብር ከፋዮችን ገንዘብ ማባከን ነው" ብለው ከ31 የተመድ ተቋማት አገሪቱን አስወጥተዋል።

አሜሪካ አምና ለተመድ ሰብአዊ ድጋፍ የለገሰችው 2 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ሲሆን በ2022 ተቋሙ ያወጣው 17 ቢሊዮን ዶላር ነው።

ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን እና ሌሎችም አገራት ለተመድ የሚሰጡትን ገንዘብ እንደሚቀንሱ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ትራምፕ ያቋቋሙት 'የሰላም ቦርድ' የተመድን ሚና የሚገዳደር እንደሆነ እየተገለጸ ይገኛል።

ተመድ በተለያዩ አካባቢዎች መርማሪዎችን ለማሰማራት የሚያስፈልገው ገንዘብ ከሌለው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና የጦር ወንጀሎች ሳይመዘገቡ እንደሚታለፉ አስታውቋል።

በወሊድ ወቅት በሚገጥም የእናቶች ሞት ግንባር ቀደም በሆነችው አፍጋኒስታን የተመድ የእናቶች እና ሕጻናት ክሊኒኮች ተዘግተዋል።

በሱዳን ከእርስ በርስ ጦርነት ለሚሸሹ ተፈናቃዮች የዓለም ምግብ ፕሮግራም እርዳታ ማቅረብም አልቻለም።