ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሴት ጋዜጠኞች ከታሊባን ሚኒስትር ጋር የሚታዩበት ምሥል ለምን አነጋጋሪ ሆነ?
በሕንድ ጋዜጦች ላይ የወጣ ምሥል ከሰሞኑ ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኗል። ምሥሉ ላይ ሴት ጋዜጠኞች በውይይት አዳራሽ ተሰብስብው ይታያል።
በደልሒ ጋዜጣዊ መግለጫው የተሰጠው በታሊባን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሆኑ ጉዳዩን አነጋጋሪ አድርጎታል።
ሚኒስትሩ አሚር ካሀን ሙቴቂ ባለፈው ሳምንት አርብ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ሴቶች አለመገኘታቸው ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቶ ነበር።
ሴት ጋዜጠኞች የተገኙበት ሌላ ጋዜጣዊ መግለጫ የተሰጠው ተቃውሞውን ተከትሎ ነው።
ሚኒስትሩ "ሴቶች በመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫ ያልተገኙት ሆነ ተብሎ አይደለም። የነበረን የጋዜጠኞች ስም ዝርዝር አጭር ነበር። ጥድፊያ ላይ ስለነበርን እነሱን ብቻ ጋበዝን" ብለዋል።
ሚኒስትሩ ይህን ቢሉም ታሊባን "የፆታ መድልዎ የነገሠበት አስተዳደር" ዘርግቷል ሲል የተባበሩት መንግሥታት በተደጋጋሚ ኮንኗን።
በአፍጋኒስታን ሴቶች የሁለተኛ ደረጃ እና የዩኒቨርስቲ ትምህርት እንዳያገኙ ታግደዋል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ እና መናፈሻም አይሄዱም።
ታሊባን ሴቶች የሚሰማሩባቸውን የሥራ ዘርፎች አጥብቧል። ከራስ እስከ እግር የሚሸፍን አለባበስን አስገዳጅ አድርጓል።
ሴቶች እንቅስቃሴያቸው እንዲገደብም ታሊባን አዟል። በሴቶች የተጻፉ መጻሕፍት ማስተማሪያ እንዳይሆኑ አግዷል።
እአአ በ2021 ወደ ሥልጣን የተመለሰው ታሊባን የሴቶችን መብት የሚያከብረው "ከአፍጋኒስታን ባህል እና የእስልምና ሕግ ጋር በሚጣጣም መልኩ" እንደሆነ ገልጿል።
ሴት ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች በታሊባን ዕውቅና ለማግኘት መቸገራቸውን ተናግረዋል።
ታሊባን በሴቶች ላይ የሚያደርሰው ጭቆና በዓለም የከፉ ከሚባሉት መካከል ይጠቀሳል።
የታሊባን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሩሲያ አመራሮች ጋር ለአንድ ሳምንት ውይይት ለማካሄድ ወደ ሕንድ አቅንተዋል።
እስካሁን ለታሊባን መንግሥት ሙሉ ዕውቅና የሰጠችው ሩሲያ ብቻ ናት።
ሕንድ ለታሊባን ዕውቅና ባትሰጥም የተወሰነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ታደርጋለች።
በካቡል ጥቂት የሕንድ ልዑካን የሚገኙ ሲሆን፣ ሰብዓዊ እርዳታም ከሕንድ ወደ አፍጋኒስታን ይላካል።
የታሊባን ሚኒስትር የሕንድ ጉብኝት የሁለቱን አገራትን ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ተብሏል።
ጉብኝቱ የታሊባን መንግሥት በሕንድ ዕውቅና ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት አንድ አካል ነው።
ሕንድ በካቡል የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለመክፈት ዕቅድ እንዳላት አስታውቃለች።
የታሊባን ሚኒስትር የመጀመሪያ ዙር ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ 16 ወንድ ጋዜጠኞች ተገኝተዋል። ሴት ጋዜጠኞች ግን ወደ ኤምባሲው እንዳይገቡ ተከልክለዋል።
በታሊባን አስተዳደር ውስጥ ያሉ ምንጭ እንደተናገሩት፤ ሴቶች በጋዜጣዊ መግለጫው አልተጋበዙም።
የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "በአፍጋኒስታን ኤምባሲ በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ውስጥ እጃችን የለበትም" ሲል መግለጫ አውጥቷል።
የፆታ መድልዎው ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞችን እጅግ አስቆጥቷል። የሕንድ መንግሥት መድልዎ እንዲፈጸም በመፍቀዱም ተወቅሷል።
ተቃዋሚ ፖለቲከኞው ራውል ጋንዲ "የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ንሬንድራ ሞዲ ጋዜጣዊ መግለጫው እንዲከናወን ፈቅደዋል። በዚህም ለሕንዳውያን ሴቶች መብት ለመቆም ብቃቱ እንደሌላቸው አሳይተዋል" በማለት ተችተዋል።
የሕንድ የሴት ጋዜጠኞች ማኅበርን ጨምሮ ሌሎችም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበራት ጠንካራ መግለጫ በማውጣት ሴት ጋዜጠኞች መገለላቸውን አውግዘዋል።
'ዘ ኤዲተርስ ጊልድ ኦፍ ኢንዲያ' ባወጣው መግለጫ "በቪየና ስምምነት መሠረት ዲፕሎማቶች ከለላ ሊኖራቸው ይችላል። ግን በሕንድ መሬት ላይ ዐይን ያወጣ መድልዎ ለመፈጸሙ ምክንያት አይሆንም" ብሏል።
"የተዘጋጀው በሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባይሆንም እንዲህ ያለ መገለል ሲፈጸም በዝምታ መታለፍ አልነበረበትም" ሲልም መግለጫው ያትታል።
'ኔትወርክ ኦፍ ውሜን ኢን ኢንዲያ' ባወጣው መግለጫ "የሕንድ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ መብትን የማስጠበቅ ኃላፊነት አለበት። የሴት ዜጎች መብት መከበር ይገባል። ይህም የመሥራት ነጻነታቸውን ይጨምራል" ብሏል።
የመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተሳተፉ ወንድ ጋዜጠኞች ለሴት የሙያ አጋሮቻቸው መብት ባለመቆማቸውም ተተችተዋል።
"ዝምታ እንደመተባበር ይቆጠራል። የፆታ መድልዎን ያባብሳል" በማለት የሴት ጋዜጠኞች ማኅበር አውግዟል።
የታሊባን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የደረሰበትን ነቀፋ ተከትሎ አዲስ ጋዜጣዊ መግለጫ አዘጋጅቶ ሴት ጋዜጠኖችን ጨምሮ ጋብዟል።
ሁለተኛው ጋዜጣዊ መግለጫ ለምን እንደተከናወነ ግልጽ ባይሆንም፤ የሕንድ መንግሥት ጣልቃ እንደገባ ይታመናል።
የታሊባኑ ሚኒስትር ከሴት ጋዜጠኞች ከተሰነዘሩላቸው ጥያቄዎች ማከከል ለምን ሴት ጋዜጠኞች ከመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫ ታገዱ? የአፍጋኒስታን ሴቶች ለምን ይጨቆናሉ? የሚሉት ይገኙበታል።
ሚኒስትሩ "ዩኒቨርስቲዎችን ጨምሮ በትምህርት ተቋሞቻችን 10 ሚሊዮን ተማሪዎች አሉን። ከ2.8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። በኢስላማዊ ትምህርት ቤትም ይማራሉ" ሲሉ መልሰዋል።
"የተወሰኑ ገደቦች አሉ። የሴቶች መማር ሐራም ነው ግን አላልንም። ትምህርት የተቋረጠው ቀጣይ አመራር እስከሚሰጥ ነው" ብለዋል ሚኒስትሩ።
ጋዜጠኞቹ ታሊባን ሴቶች ላይ የጫናቸውን አግላይ ትዕዛዞች በመጥቀስ ተጨማሪ ጥያቄዎች አቅርበዋል።
ሚኒስትሩ ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ "በአፍጋኒስታን የሴቶች መብት ጉዳይ አጥጋቢ ደረጃ ባይደርስም፤ ሁለተኛ ጋዜጣዊ መግለጫ ተዘጋጅቶ ከሴት ጋዜጠኞች ስለ ሴቶች መብት ጥያቄ መቀበላችን መሻሻል እንዳለ ያሳያል" ብለዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት ከ12 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች ትምህርት እንዲያቋርጡ ተወስኗል። የሥራ ዕድሎችም ውስን ሆነዋል።