አርሰናል ከአስተን ቪላ - ማን ይረታል? የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ግምት

ኒውካስል በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከታታይ 10 ጨዋታዎች ድል ሊቀናው ይችላል። ቅዳሜ ኒውካስል ከቦርንመዝ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

በሌላ ተጠባቂ ጨዋታ አርሰናል በሜዳው አስተን ቪላን ያስተናግዳል።

የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱተን ባለፈው የውድድር ዘመን አርሰናል ዋንጫ እንዳይበላ ያደረገው በአስተን ቪላ መረታቱ ነው ይላል።

ሱተን የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የ22ኛ ሳምንት ግጥሚያዎችን ግምት እንዲህ አስቀምጧል።

ቅዳሜ

ኒውካስል ከቦርንመዝ

ይህን ጨዋታ መገመት ከባድ ነው። ምክንያቱም ኒውካስል የሚያቆማቸው ያለ አይመስልም። ቦርንመዝ ደግሞ ባለፉት 10 ጨዋታዎች አንድም ሽንፈት አላስተናገዱም።

ኒውካስል ይህን ፍልሚያ የሚረታ ከሆነ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ 10 ተከታታይ ጨዋታዎችን ያሸንፋል ማለት ነው።

የኒውካስሉ አሠልጣኝ ኤዲ ሀው የድሮ ቡድናቸውን ከዚህ ቀደም ረትተው አያውቁም። በቅዳሜው ጨዋታ ግን ይህ የሚየቀየር ይመስለኛል።

ግምት፡ 2 - 1

ብሬንትፈርድ ከሊቨርፑል

ሊቨርፑል በሳምንቱ አጋማሽ ጨዋታ ከኖቲንግሀም ጋር በነበራቸው ጨዋታ አቻ ወጥተዋል። የዕድል ነገር ሆኖ እንጂ ጨዋታውን ማሸነፍ ነበረባቸው። የኖቲንግሀሙ በረኛ ድንቅ ነበር።

አርሰናል ማሸነፉን ተከትሎ ይህ ለሊቨርፑል እጅግ ወሳኝ ጨዋታ ነው። ይህን ጨዋታ ማሸነፍ አለባቸው።

ሊቨርፑል በአዲሱ ዓመት በሁሉም ውድድሮች አንድ ጊዜ ብቻ ነው ድል የቀናቸው። ወደ ብሬንትፈርድ ሜዳ ተጉዘው የሚያደርጉት ጨዋታም ቀላል የሚሆንላቸው ባይሆንም እንደሚያሸንፉ እገምታለሁ።

ግምት፡ 1 - 2

ሌስተር ከፉልሀም

ሌስተር ተስፋ እየቆረጡ የመጡ ይመስላል። ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ተሸንፈዋል። አቋማቸው ደካማ ነው።

ከታችኛቸው ሊግ የመጡ ክለቦች ለመቆየት መታገላቸው ያለ ቢሆንም ሌስተር ግን ይህን ፈተና እንደሚወጡት ጠብቄ ነበር።

የፉልሀም አቋምም እንዲሁም የደከመ ይመስላል። ነገር ግን ፉልሀም አቻ ቢወጡ እንጂ አይረቱም።

ግምት፡ 1 - 2

ዌስት ሀም ከክሪስታል ፓላስ

አዲሱ የዌስት ሀም አሠልጣኝ ግራሀም ፖተር በመጀመሪያ ጨዋታው ድል ቀንቶታል። ማክሰኞ ምሽት ፉልሀምን ቢረታም ቡድኑ ክፍተት እንዳለው ማየት ይቻላል።

ይህ ጨዋታ አቻ ይጠናቀቃል ማለት ይቻላል ግን ይህን አላደረግም።

በተቃራኒው ጥሩ አቋም ላይ ያሉት ፓላሶች እንደሚረቱ እገምታለሁ።

ግምት፡ 0 - 1

አርሰናል ከአስተን ቪላ

መድፈኞቹ ባለፈው የውድድር ዘመን ዋንጫ እንዳያነሱ ምክንያት ከሆናቸው ነገር አንዱ በቪላ መሸነፋቸው ነበር።

አርሰናሎች ይህን የሚረሱት አይመስለኝም። ምናልባትም አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ ይህን እንደማነቃቂያ ሊጠቀመው ይችላል።

በሳምንቱ አጋማሽ ጨዋታዎች ቪላ ኤቨርተንን፤ አርሰናል ደግሞ በሰሜን ለንደን ደርቢ ቶተንሀምን ማሸነፍ ችለዋል።

መድፈኞቹ የድል ግስጋሴያቸውን በዚህኛውም ጨዋታ ይቀጥላሉ ብዬ እጠብቃለሁ።

ግምት፡ 2 - 0

እሑድ

ኤቨርተን ከቶተንሀም

አዲሱ የኤቨርተን አሠልጣኝ ዴቪድ ሞየስ ከቀድሞው አሠልጣኝ በተለየ ክፍት የሆነ ጨዋታ ለመጫወት ቢሞክሩም በመጀመሪያ ፍልሚያቸው ሽንፈት ቀምሰዋል።

ከቶተንሀም ጋር የሚደረገውም ጨዋታ ክፍት የሚሆን ይመስለኛል።

ኤቨርተን የግብ እጥረት አለባቸው። ባለፉት 20 ጨዋታዎች 15 ግቦች ብቻ ነው ያስቆጠሩት። ቶተንሀም አሁን ያለበት አቋም ጥሩ ባይሆንም ይህን ጨዋታ እንደሚያሸንፍ አልጠራጠርም።

ግምት፡ 1 - 3

ማንቸስተር ዩናይትድ ከብራይተን

ዩናይትድ ሐሙስ በነበረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በሳውዝአምፕተን ተበልጦ ነበር።

ነገር ግን አማድ ዲያሎ በመጨረሻዎቹ 12 ደቂቃዎች ባስቆጠራቸው ሦስት ግቦች ሦስት ነጥብ ይዞ ወጥቷል። ይህም ማለት ዩናይትድ ወደ ቀደመ አቋሙ ተመልሷል ማለት ግን አይደለም።

አሠልጣኝ ሩበን አሞሪም ገና ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል። አንዱ ፈተና እሑድ የሚደረገው ጨዋታ ይሆናል። ምክንያቱም ብራይተን ከሳውዝአምፕተን ከበድ ያለ ቡድን ነው።

ጨዋታው በአቻ ውጤት እንደሚጠናቀቅ ነው ግምቴ።

ግምት፡ 1 - 1

ኖቲንግሀም ከሳውዝአምፕተን

ሳውዝአምፕተን ወደ ኦልድ ትራፈርድ ተጉዘው ጥሩ ጨዋታ ቢያደርጉም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተሸንፈዋል።

ነገር ግን ኖቲንግሀም ፎረስት አሁን ባለው አቋም በሳውዝአምፕተን ይፈተናል ማለት ዘበት ነው።

የፎረስቱ አጥቂ ክሪስ ዉድ ጎል ማስቆጠሩን ቀጥሏል። በዚህኛውም ጨዋታ ግብ ያስቆጥራል ብዬ ገምታለሁ።

ግምት፡ 2 - 0

ኢፕስዊች ከማንቸስተር ሲቲ

ኢፕስዊች ጥቂት ጨዋታዎችን አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ገስግሰው ሐሙስ ምሽት በብራይተን ተረትተዋል።

ሲቲ በበኩሉ 2 ለምንም ያሸንፋል የተባለውን ጨዋታ በተገባደደ ሰዓት ሁለት ግብ ተቆጥሮበት አቻ ወጥቷል።

የሲቲው አጥቂ ኧርሊንግ ሀላንድ በክለቡ የሚያቆየውን የዘጠኝ ዓመት ተኩል ኮንትራት ፈርሟል። ይህ ለሲቲ መልካም ዜና ነው።

ኢፕስዊች ለሲቲ ቀላል ባይሆኑም ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ያገኛሉ የሚል እምነት የለኝም።

ግምት፡ 1 - 2

ሰኞ

ቼልሲ ከዎልቭስ

ቼልሲ አሁን ያለበት አቋም የወረደ ነው። ነገር ግን ወደ ቀደመ አቋሙ እንደሚመለስ አልጠራጠርም።

የዎልቭስ አሠልጣኝ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ድል ቢያጣጥምም በቀጣዮቹ ሁለት ጨዋታዎች ተረትተዋል።

ቼልሲ ይህን ጨዋታ በቀላሉ ማሸነፍ አለበት።

ግምት፡ 3 - 0