"የኢትዮጵያ መንግሥት ሌላ ዙር ጦርነት ለማካሄድ ግልጽ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው" - ህወሓት

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የኢትዮጵያ መንግሥት "ሌላ ዙር ጦርነት ለማካሄድ ግልጽ እንቅስቃሴ" እያደረገ ነው ሲል ከስሶ፤ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን እንቅስቃሴ እንዲያስቆም አሳሰበ።

በኢትዮጵያ የሚገኘው የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ፣ 22 የአውሮፓ ኅብረት አገራት እና ኖርዌይ ደግሞ ከመጪው "አጠቃላይ ምርጫ በፊት" በፕሪቶሪያ ስምምነት ፈራሚዎች መካከል "ፖለቲካዊ ንግግር እንዲቀጥል" በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል።

ህወሓት እና የምዕራቡ ዓለም አገራት ኤምባሲዎች ይህንን ያሉት የትግራይ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ሦስተኛ ዓመትን በማስመልከት ትናንት እሑድ ጥቅምት 23/2018 ዓ. ም. ባወጧቸው የተለያዩ መግለጫዎች ነው።

የዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነቱ አንዱ ፈራሚ የሆነው ህወሓት፤ በፕሪቶሪያ ስምምነት አካማኝነት መፈጸም የነበረባቸው ተግባራት ተፈጻሚ አለመሆናቸውን በመግለጫው አንስቷል። በሁለት ዓመቱ ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅት የትግራይ ሕዝብ "ጭፍጨፋ"፣ "ፆታዊ ጥቃት"፣ "መፈናቀል" እንዲሁም ንብረት "ዘረፋ" እና "ውድመት" እንደተፈጸመበት ገልጿል።

ይህንን ጉዳት ያስከተለውን ውጊያ ለማስቆም ከሦስት ዓመት በፊት የፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረሙን ያስታወሰው ህወሓት፤ ይሁን እንጂ ጦርነቱ "በዝምታ [ከሚካሄድ] ዘር ማጥፋት ጋር ቀጥሎ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል" ብሏል።

በዚህም ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች መመለስ አለመቻላቸውን እንዲሁም "ወራሪ" ሲል በጠራው ኃይል ሥር የሚኖረው የትግራይ ሕዝብ "እየተገደለ"፣ "እየታፈነ" እና "በማንነቱ ምክንያት እየተሰቃየ" መሆኑን በማንሳት ወንጅሏል።

"የፍትሕ እና የተጠያቂነት ሂደት እንዲሁም የጦርነቱ መነሻ እና አፈታቱን በተመለከተ ፖለቲካዊ ንግግር አልተጀመረም" ሲል በስምምነቱ መሠረት መፈጸም የነበረበት አንዱ ተግባር አለመከናወኑን አስታውሷል።

"በአጠቃላይ የፕሪቶሪያ ስምምነት እንደተጠበቀው ውጤት ሳያመጣ ሦስት ዓመታትን ደፍኗል" ያለው ህወሓት፤ ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥትን እና በስምምነቱ ሂደት የተሳተፉ አካላትን ወቅሷል።

መግለጫው፤ የፌደራል መንግሥት ፕሪቶሪያ ላይ "የተስማማበትን ስምምነት መፈጸም አለመቻሉን" እንደ አንድ ምክንያት ጠቅሷል። "አደራዳሪ አገራት፣ አህጉራዊ ተቋማት እና ግለሰቦች" ስምምነቱ "በተፈረመበት መንፈስ እና [ተግባራዊ መሆን] በጀመረበት ፍጥነት እንዲሄድ መከታተል ላይ ያሳዩት መዘናጋትም" ለስምምነቱ በተሟላ ሁኔታ አለመፈጸም አስተዋጾ ማድረጉንም አንስቷል።

ህወሓት፤ የፌደራል መንግሥት የተጣሉበትን ግዴታዎች "ካለመፈጸም" ባሻገር፤ "ስምምነቱን የሚጥሱ ተግባራት ላይ ተጠምዶ" እንደሚገኝ በመግለጽ ከስሷል። "በትግራይ ሕዝብ እና ብሔራዊ ተቋማቱ ላይ ተከታታይ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ" እንዲሁም "ስም ማጥፋት" ማካሄድ ህወሓት በፌደራል መንግሥት ተፈጽመዋል ያላቸው ተግባራት ናቸው።

የፌደራል መንግሥት "ታጣቂዎች በመመልመል፣ በማሠልጠን እና በማደራጀት የትግራይ ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዲዋጋ እየሠራ ነው" ሲልም ከስሷል።

"ከዚህም አልፎ የፕሪቶሪያ ስምምነትን የሚያፈርስ እና ሌላ ዙር ጦርነት ለማካሄድ ግልጽ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል" በማለት በፌደራል መንግሥት ላይ ውንጀላውን አቅርቧል።

ህወሓት፤ የፌደራል መንግሥት "ሌላ ዙር ጦርነት" ለመክፈት የሚያደርገው እንቅስቃሴ በሁሉም መልክ በጣም የከፋ ጉዳት" እንደሚያስከትል በመጥቀስ አስጠንቅቋል። መንግሥት፤ "በጦርነት የሚሟላ ፍላጎትም ሆነ የሚፈታ ልዩነት እንደሌለ አውቆ፤ የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲፈጸም ኃላፊነቱን እንዲወጣ እና ፖለቲካዊ ንግግርን እንደመፍትሔ እንዲወስድም" አሳስቧል።

"የዓለም ማኅበረሰብም በበኩሉ በኢትዮጵያ መንግሥት እየተቀጣጠለ ያለውን ሌላ ዙር ጦርነት ለማስቆም የሚጠበቅበትን ሁሉ መፈጸም ይገባዋል" ሲልም ጥሪውን አቅርቧል። አደራዳሪ አገራት እና አህጉራዊ ተቋማትም "ለሁኔታው ትኩረት" እንዲሰጡ ያሳሰበው ህወሓት፤ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ እንዲጠራ በድጋሚ ጠይቋል።

"የአፍሪካ ኅብረት ፓኔል እንዲጠራ እና የስምምነቱ ነባራዊ ሁኔታ ተገምግሞ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ወደ ዘላቂ የሰላም ስምምነት እንዲያድግ ጫና እንዲያደርጉ እንጠራለን" ሲል በመግለጫው አስፍሯል።

የፕሪቶሪያ ስምምነት የተፈረመበትን ሦስተኛ ዓመት በማሰብ መግለጫ ያወጡት በኢትዮጵያ የሚገኙ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት እና የኖርዌይ ኤምባሲዎችም በተመሳሳይ፤ በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል "ፖለቲካዊ ንግግር" እንዲካሄድ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኘው የአውሮፓ ኅብረት ልዑክ ጋር በመሆን ይህንን መግለጫ ካወጡት 22 አገራት መካከል ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ዴንማርክ፣ አየርላንድ እና ስፔን ይገኙታል።

አገራቱ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ለተከናወኑት "መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ"፣ "ሰብአዊ አቅርቦት መሻሻል" እንዲሁም የትጥቅ ማስፈታት፣ መበተን እና መልሶ ማዋሃድ ሂደት "መጀመር" ዕውቅና እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።

መግለጫው፤ "የተወሰኑ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንዲመለሱ የማስቻል" ተግባር መከናወኑን በመጥቀስ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓትን አመስግነዋል።

የዲፕሎማቲክ ልዑኮቹ፤ "በሰሜን ኢትዮጵያ እና በሰፊው ቀጣና" ላይ ሰላምን "ዘላቂ የማድግ እና የማጠናከር" አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል። በቀሪ የስምምነቱ ሂደቶች ላይ እገዛ ለማድረግ "ዝግጁ" መሆናቸውን የገለጹት አገራቱ፤ ሙሉ በሙሉ ካልተፈጸሙ ተግባራት መካከል የተፈናቃዮች መመለስን ጠቅሰዋል።

ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው መመለስ ያለባቸው "ዓለም አቀፍ ሰብአዊ ሕግን እና ምርጥ ተሞክሮዎችን ባሟላ አካሄድ" መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል። "ተአማኒ እና ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ የሽግግር ፍትሕ" ተፈጸሚነት ላይም እገዛ ለማድረግ ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙት የአውሮፓ ኅብረት እና የአገራቱ ዲፕሎማቲክ ልዑካን አክለውም፤ "ከመጪው አጠቃላይ ምርጫ አስቀድሞ በስምምነቱ ፈራሚዎች መካከል ፖለቲካዊ ንግግር እንዲቀጥል ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል።

በግጭት የተጠቁ የአገሪቱ ክፍሎች ከቁስላቸው "እንዲሽሩ" እንዲሁም "ፍትሕ" እንዲሰፍን ለማድረግ "ተጠያቂነት [መኖር]፣ የሰብአዊ መብት መከበር፣ በተለይም የሴቶች እና የሴት ልጆች መብት መከበር እና እርቅ" አስፈላጊ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

"አገሪቱ ውስጥ እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች በውይይት እንዲፈቱ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ሁሉ በአገራዊ ምክክሩ ሒደት ገንቢ በሆነ መንገድ እንዲሳተፉ እናበረታታለን" ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ትናንት ጥቅምት 23/2018 ዓ. ም. ከተፈረመ ሦስተኛ ዓመቱን የደፈነው የፕሪቶሪያ ስምምነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅትም ተነስቶ ነበር።

ዐቢይ፤ ከስምምነቱ እና ከትግራይ ክልል ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የሰጧቸው ማብራሪያዎች እንዲሁ በህወሓት ላይ ውንጀላን የሰነዘሩ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የትግራይ አመራሮች "መሣሪያ ደብቀው እንዳስቀመጡ" እና በ"ኮንትሮባንድ እያስገቡ" መሆኑ እንዲሁም ታጣቂዎችን "እያሠለጠኑ" እና "እያስመረቁ" እንደሆነ የሚጠቁም ውንጀላ አሰምተዋል። የትግራይ አመራሮች "ከውጭ [አገር መንግሥት] ጋር ምን እያደረጉ ነው?" ሲልም ተመሳሳይ ድምፀት ያለው ጥያቄ አንስተዋል።

"[በ]ትግራይ ክልል ተጨማሪ ውጊያ አያስፈልግም። ትግራይ የሚደረግ ውጊያ ዓላማ የለውም። ዓላማ የሌለው ውጊያ ደግሞ የተሳካ ይሁን ያልተሳካ ማረጋጫ የለውም" ሲሉ መንግሥታቸው ሌላ ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ገልጸዋል።

"ውጊያ ይበቃል አያስፈልገንም። ግድ የለም ብትዋጉም አታሸንፉም፤ አይታችሁታል" ያሉት ዐቢይ፤ "የኢትዮጵያን መንግሥት በኃይል" መቀየር "እንደማይቻል" ተናግረዋል።