ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፕሪቶሪያ ስምምነት ተደራዳሪ አቶ አሰፋ አብርሃ፡ "በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ጦርነት የመቀስቀስ ዕድሉ ጠባብ ነው"
ከትግራይ ክልል ተወክለው የፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈራራሚ ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አሰፋ አብርሃ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ውጊያ ሊነሳ የሚችልበት ዕድል "በአመዛኙ ያለ አይመስለኝም" አሉ።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በተደጋጋሚ ጠንካራ የቃላት ክሶች ሲለዋወጡ ከመቆየታቸው ጋር በተያያዘ ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ የሚለው ስጋት እንዳንዣበበ ነው።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስከረም 200/2018 ዓ.ም. ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ የኤርትራ መንግሥት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) "ጽምዶ" በሚል ጥምረት ኢትዮጵያ ላይ "ጦርነት ለመክፈት" እየሠሩ ነው ሲል ከሷል።
ሚኒስቴሩ በጻፈው በዚህ ደብዳቤ፣ ሁለቱ አካላት በቅርቡ የፋኖ ታጣቂዎች የሰሜን ወሎ ዋና ከተማ የሆነችውን ወልዲያን ለመቆጣጣር ባደረጉት ሙከራ ውስጥ ተሳትፈዋል ሲል ወንጅሏቸዋል።
ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞትዮስ የተጻፈው ይህ ደብዳቤ "በኤርትራ መንግሥት እና በህወሓት አክራሪ አንጃ መካከል ያለው ጥምረት ባለፉት ጥቂት ወራት ግልጽ እየሆነ መጥቷል" ብሏል።
ከዚህ ደብዳቤ መጻፍ ቀደም ብሎ በነበሩት ወራት ደግሞ በተለይም ከቀይ ባሕር ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሁለቱ አገራት ውጥረት እየተባባሰ መጥቷል።
በአቶ ጌታቸው ረዳ ይመራ የነበረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አማካሪ የነበሩት አቶ አሰፋ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ውጥረት መንገሱን ተከትሎ ምን ሊፈጠር ይችላል? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው
"ጦርነት የመቀስቀስ ዕድሉ ጠባብ ነው" የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
"ከሻዕቢያ ጋር ያለውን ሁኔታ እንዴት ታየዋለህ? ላልከው፣ አንዱ የእነ ደብረፂዮን ህወሓት ስሌት ዐቢይ እና ኢሳያስ ይዋጋሉ የሚል ነው። ዐቢይ እና ኢሳያስ ይዋጋሉ? ሊዋጉ የሚችሉበት ዕድል አላቸው? እኔ በአመዛኙ አይመስለኝም። የሚያዋጋ ምክንያት የላቸውም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ይህንንም ሲያብራሩ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እንዲሁም አሜሪካ ባሉበት የተፈረረሙት ስምምነት ኢትዮጵያ ስለምታነሳው የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ስለሚሰጥ ነው ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ከማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪያቸው ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ቀይ ባሕር ከሠላሳ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ እጅ እንደነበረ ጠቅሰው "ስህተቱ ነገ ይታረማል" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
"ቀይ ባሕር እኮ የዛሬ 30 ዓመት እኛ እጅ ነበር። ቀይ ባሕር የዛሬ 30 ዓመት የትናንት ታሪክ ነው። የተፈጠረው ስህተት ትናንትና ነው። ነገ ይታረማል፤ ብዙ ከባድ አይደለም" ማለታቸው አይዘነጋም።
ኤርትራ ነጻነቷን ስታገኝ ከቀይ ባሕር የተነጠለችው ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት እንዳላት ይፋ ካደረጉ በኋላ በኤርትራ በኩል ስጋት ተፈጥሯል።
የፕሪቶሪያ ስምምነትን በተመለከተ
ከትግራይ ክልል ተወክለው የፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈራራሚ ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አሰፋ አብርሃ ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል የፕሪቶሪያ ስምምነትን የሚመለከቱት ይገኙበታል።
"ፕሪቶሪያ ሲፈረም አዲስ አሰላለፍ እና ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ስንፈርመው ጀምሮ ይታወቅ ነበር" በማለት አቶ አሰፋ ተናግረዋል።
ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳይ የፕሪቶሪያን ስምምነት በተመለከተ "የስምምነቱ ተጽዕኖ ውጊያ ማቆም ብቻ አይደለም። በአፍሪካ ቀንድ የኃይል አሰላለፉን ይቀይራል ብሎ ገልጾት ነበር። በመሠረቱ የአሰላለፍ ለውጥ እንደሚኖር ግንዛቤ ነበር" ማለታቸውንም ጠቅሰዋል።
የፕሪቶሪያ ግጭት ማቆም ስምምነት ተፈራራሚው ህወሓት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዳግም ዕውቅና ቢሰጠውም ብዙም ሳይቆይ ሕጋዊነቱን አጥቷል።
አንዱ ተፈራራሚ ሕጋዊ ኅልውና ባጣበት ሁኔታ ስምምነቱ ምን ሊሆን ይችላል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ "ከ10 በላይ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የያዘ ዋና የፕሪቶሪያ ተደራዳሪ ትልቅ ቡድን ተቆርጦ ወጥቷል። በውስጣቸው ከተወሰኑ የሠራዊቱ አመራር ጋር ሆነው ደርግን የመሰለ ኃይል በማዋቀር የተረፈውን የመንግሥት መዋቅር ጎትተው ወደ ዋናው ፀረ ፕሪቶሪያ ወደሆነው ኃይል አሳልፈው እየሰጡት ነው። እያየን ያለነው ይህንን ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጨምረውም "ሁሉን አቃፊ የተባለው መንግሥት የባሰ ጠበበ። በድርድሩ የነበሩ እንዲሁም ከሽግግሩ በኋላ የተፈጠሩ ኃይሎች አብዛኞቹ ተበታተኑ።
ህወሓት ራሱ ለሁለት ለሦስት ተሰነጣጥቆ ጠፋ፣ ሕጋዊነቱንም አጥቶ መክኗል። ሠራዊቱም ከሁለት ሦስት ተከፍሎ ዕዙን አጥቷል" በማለት አቶ አሰፋ አሁን ያለውን ክፍፍል ገልጸዋል።
"አቃፊ ሳይሆን የባሰ በታኝ ነገር መጥቷል" ያሉት አቶ አሰፋ "የመንግሥት ወይም የጄነራል ታደሰን ትዕዛዝ ሰምቶ ከሚሰማራ ሠራዊት ይልቅ፣ እምቢ ብሎ ቤቱ የተቀመጠ፣ ወይ ትዕዛዝ ሲሰጠው አልቀበልም ብሎ ተራራ ሂዶ የተቀመጠ ይበዛል። ብዙ ኃይል እየፈረሰ ነው። ህወሓትም እንደምታያት ናት" ብለዋል።
በአቶ ጌታቸው የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር ለምን ፈረሰ?
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በአቶ ጌታቸው ረዳ ይመራ በነበረበት ወቅት አማካሪ የነበሩት አቶ አሰፋ፤ ይህ ጊዜያዊ አስተዳደር ለምን እንደፈረሰ ተጠይቀዋል።
"እኛ ከብልጽግናም ሆነ ከሻዕቢያ ጋር መወገን አይጠቅመንም የሚል እምነት ነበረን። ከሁለቱም ተከላክሎ የሚያሻግረን ፕሪቶሪያ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
"ደክመናል፣አቅም አጥተናል። ወደዚህም ወደዚያም ማለቱ አሽከር ለመሆን ካልሆነ በስተቀር የሚያመጣልን ነገር የለም። ይልቅ ራሳችንን በራሳችን ለማዳንና ለማከም እንሥራ" የሚል አቋም እንደነበራቸው ገልጸዋል።
አክለውም "ጉዳዮቻችን ደግሞ መልክ ባለው መልኩ ምላሽ እንዲያገኙ ይጠቅመናል። እኛ ራሳችንን አድነን እነርሱንም ወደ ጦርነት ከማስገባት እናተርፋቸዋለን የሚል እምነት ነበረን" በማለት የጊዜያዊ አስተዳደሩን አቋም አብራርተዋል።
ይህ አቋም ቢኖራቸውም ግን መጨረሻ ላይ "መካካድ" እና "መፈንቅለ መንግሥት" መምጣቱን ገልጸዋል።
"ይህ ማንም ሰው የማይስተው መሠረታዊ ነገር ነው። እናም በእነዚህ መሠረታዊ ነገሮች ላይ እንግባባለን የሚል ተስፋ ነበረን። የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ፖለቲካ የማይገባቸው የምትላቸው አይደሉም። ለምሳሌ ጄነራል ታደሰ በፖለቲካ የበቃ ነው። ይረዳዋል። በዚህ ጉዳይ አንካካድም የሚል እምነት ነበረን።"
አቶ አሰፋ ጨምረውም "መጨረሻ ግን እንዳየኸው ሆነ። የግል ጥቅም አሳስቧቸው ይሁን ወይም ሌላ ትስስር ይኑር አይታወቅም ክህደት ፈጽመው መፈንቅለ መንግሥት አደረጉ" ብለዋል።
በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው መከፋፈል መጠናከሩን ተከትሎ ለሁለት ዓመት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን በፕሬዝዳንትነት የመሩት አቶ ጌታቸው ረዳ መጋቢት 30/2017 ዓ. ም. ከሥልጣን ተነስተው ምክትላቸው ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ መተካታቸው ይታወሳል።
በቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በሚመራው የህወሓት ክንፍ መካከል ተከስቶ የነበረው ክፍፍል በክልሉ ላይ ስጋት ፈጥሮ ነበር።
አቶ አሰፋ የተፈጠረውን ልዩነት ሲገልጹ "እኛ ምንም የማንመርጠውን አማራጭ ይዘው መጡ። እኛን ለመግደል ዝግጁ ነበሩ። ሰው ለመግደል፣ ለማሰር፣ ቆርጠውና ወስነው ቀጠሉ። እኛ ለመነጋገር እና ለመወያየት እንጅ በጠመንጃ አስገድደን ልንፈጥረው የምንፈልገው ተጽዕኖ አልነበረንም" ብለዋል።
መልስ ያላገኘው የተፈናቃዮች ጥያቄ
በአቶ ጌታቸው ረዳ ይመራ የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር አላሳካቸውም ከሚባሉት መካከል አንዱ የተፈናቃዮች አለመመለስ ነው።
አቶ አሰፋ ተፈናቃዮችን በማስመለስ ረገድ ዋናው ኃላፊነት የፌደራል መንግሥት መሆኑን ያሰምሩበታል።
ሆኖም ጊዜያዊ አስተዳደሩ የገጠሙትን ችግሮችም ጠቅሰዋል።
"መጀመሪያ ሕዝባችንን ወደ ቀየው መመለስ፣ ከዚያም የግዛት ጉዳይ የሚቀጥል ይሆናል ብዬ ነው የማምነው። እነሱ ግን በተቃራኒው ነው የሚያስቡት" ሲሉ ይገልጻሉ።
ቅድሚያ የሚሰጠው ለሰብዓዊነት መሆኑን በመግለጽ "ግዛት ወይም ካርታ የማረጋገጥ ጉዳይ አይደለም። ግዛቱ የእኛ የሚሆነው ሕዝቡ በመሬቱ ላይ ሲኖርበት ነው። ሕዝቡ እዚያ ከሌለ ቦታው የእኛ አይደለም" በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ተፈናቃዮች አሁንም ለጥያቄያቸው መልስ አለማግኘታቸውን በመናገር ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግም ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።
አቶ አሰፋ "አሁን ሕዝባችን ወጥቶ እየጠፋ ነው። ከተፈናቀሉት መካከል አሁን 10 በመቶ አይገኝም። ሁለት ዓመት ከጨመርክ የሚመለስ ሰው አይኖርም" በማለት ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
"ከዚህ ቦታ እየተነቀልን ነው ያለነው። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ እኔን ጨምሮ የማይጨነቅ ሰው የለም" ያሉት አቶ አሰፋ የተፈናቃዮችን ጉዳይ በተመለከተ ድርድር መካሄዱን ገልጸዋል።
በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ተፈናቃዮችን የመመለስ እና የማቋቋም ኃላፊነት ያለበት የፌደራል መንግሥት እንደሆነና የስምምነቱ ፈራሚዎች፣ የተባበሩት መንግሥታት ተቋሞች እንዲሁም ህወሓት ያላቸው ሚና የማገዝ መሆኑን አስረድተዋል።
ተፈናቃዮችን የተመለከተው የፕሪቶሪያ ስምምነት ክፍል "ርዕሱ ራሱ ሰብዓዊነት ነው የሚለው" የሚሉት አቶ አሰፋ ዋነኛ ኃላፊነት ያለበት የፌደራል መንግሥት እንደመሆኑ የፌደራል መንግሥት ዕቅድ እንዳወጣ ጠቅሰው ከአንድ ዓመት በፊት "ጌታቸው፣ ፍስሐ ማንጁስ እና ታደሰ ወረደ ከትግራይ ተወክለው ተደራደሩ። ተደራድረውም ተስማምተዋል" ብለዋል።
"በዚሁ ስምምነት መሠረት ትግራይ ይህንን ታድርግ፣ ፌደራል ይህንን ያድርግ በሚል ተስማምተን ራያ እና ጸለምት ተመለሱ" ብለዋል።
አክለውም "ወደ ምዕራብ ትግራይ፣ ወልቃይት ሊሻገሩ ሲሉ ነው ጉዳዩ የተስተጓጎለው" በማለት ተናግረዋል።
ዕቅዱ ከጸደቀ በኋላ የትግራይ ሚና ማስፈጸም እንደሆነ አቶ አሰፋ ይናገራሉ።
ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ወስዶ መልሶ ማቋቋምና ደኅንነታቸውን መጠበቅ የትግራይ ክልል ሚና እንደሆነም ተናገዋል።
በዚህም መሠረት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ፣ ሥራ ተከፋፍለውና ተስማምተው ሳለ "በመሐል ከኮሚቴው መካከል ሦስት አራት የሚሆኑ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ጄኔራል ታደሰን ይህንን ዕቅድ ግን ህወሓት ያውቀዋል? ብለው ጠየቁት" በማለት እንዴት መስተጓጎሉ እንደተከሰተ አስረድተዋል።
ጉዳዩ የመንግሥት እንጂ የፓርቲ አለመሆኑን ቢገልጹም "ፓርቲያችን ተስማምቶ ያላጸደቀውን የግብረ ኃይሉ አባላት አንሆንም አሉት" በማለት የተፈጠረውን ይገልጻሉ።
"አላውቅም፤ ጄኔራል ታደሰ ትልቅ ስህተት ሰርቷል። እኔን እንደዚያ አልተረዳሁትም አለኝ ። በቃ እንስማማለን ብሎ ስብሰባውን ከእነአካቴው አቆመው። ግብረ ኃይሉን እርሱ ነበር የሚመራው።"
ይህ በተከሰተ በቀናት ውስጥ ግብረ ኃይሉ ሥራ ማቆሙን አቶ ጌታቸው እንደገለጹላቸው አቶ አሰፋ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
ከጄነራል ታደሰ ማብራሪያ እንደጠየቁ ጠቅሰውም "እንደዚያ አልነበረም የገባኝ ብሎ መለሰልኝ። ይህ የተለመደ የታደሰ ማምለጫ ነው። እርሱ አልተረዳሁትም ይበል እንጅ ጉዳዩን ወደ ህወሓት ወስዶት ስለነበር እነሱ የሚሉትን ጠብቀን እንነጋገርበታለን አለኝ" ብለዋል።
ቢያንስ ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው ይመለሱ፤ትጥቅ ይፈታ፤ ተዋቅሮ የነበረው አስተዳደር እና የፀጥታ ኃይል ፈርሶ ምርጫ ተደርጎ ተፈናቃዮች የራሳቸውን አስተዳደር ያቋቁሙ የሚል አቋም እንደነበራቸው ተናግረዋል።
"የሚቋቋመው አስተዳደር ተጠሪነቱ ለማን ይሁን? የሚል ነገር ሲነሳ፣ እየተገበርን እንየው ብለን ክፍት ተውነው፤ይህ ነበር የደረስንበት መግባባት። ነገር ግን ታደሰ ጉዳዩን ወደ ህወሓት ከወሰደው በኋላ አይ እኛማ እዚያ የነበረው ሚሊሾች እና የቀድሞ አስተዳደሮችን ሳንይዝ ሕዝባችንን አንመልስም ብለው መያዣ አድርገው ቆለፉት" ሲሉም የተፈጠረውን ገልጸዋል።
ከትግራይ ሠራዊት ያፈነገጡ ወታደሮች ጉዳይ
ከትግራይ ሠራዊት አፈንግጠው ከወጡት ወታደሮች ጋር ስላላቸው ግንኙነት እንዲሁም እነዚሁ አፈንጋጭ ወታደሮች "የፌደራል መንግሥት ድጋፍ አላቸው" ስለሚባለውም ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አሰፋ፤ "ወደዚህ ሁኔታ ያስገባን ምክንያት አንድ ነው። አሁን ወደ ነጻ መሬት የወጡት'ኮ በባለፈው ጦርነት ከፍተኛ ስም እና ብቃት የነበራቸው አዛዦች ናቸው" ብለዋል።
"ኮር እና ከኮር በላይ በሚል በተካሄደው ስብሰባ ላይ ዘፋኝ እና ኮሚሳር ጦሩን ወክሎ ድምጽ ሲሰጥ እውነተኛ አዛዦች አይሆንም ብለው ስብሰባው ረግጠው የወጡት ናቸው" ሲሉም አክለዋል።
ጨምረውም "እነ ወዲ አንጥሩ፣ እነ ወዲ ጉዕሽ፣ እነ ወዲ አባተ ቀላል ሰዎች እንዳይመስሉህ። የምንታገለው ለትግራይ ሕዝብ እንጅ ለአንድ ፓርቲ አይደለም። ለህወሓት አይደለም፣ የህወሃት አባልም አይደለንም ብለው ነው የወጡት" ብለዋል።
አቶ አሰፋ ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ "በዚህ ጉዳይ ላይ እኔም ከእነርሱ ጋር ነኝ። ወታደር ብሆን ኖሮ ከእነርሱ ጋር ነበር የምወግነው" በማለት ከትግራይ ሠራዊት አፈንግጠው የወጡት ወታደሮችን በተመለከተ ያላቸውን አቋም ገልጸዋል።
"አሁን ሁሉም ነገር እየጠራ ነው። መሄድ የፈለገ ሁሉ ቆርጦ ወደ እነሱ እየሄደ ነው። አሁን እነርሱ ተደራጅተው ያግዙናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ከእኔ ጋር ያለን ግንኙነት በዚህ መልኩ ነው።"
ከፌደራል መንግሥት ጋር ያለውን ግንኙን በተመለከተ "የፌደራል በጀት ወደ ትግራይ ተልኮ ነው ለጆን መዲድም፣ ለታደሰ ወረደም ደመወዝ የሚከፈለው። ስለዚህ እነሱም ከዚህ በጀት የድርሻ ጥያቄ አንስተዋል" ብለዋል።
"የትግራይ ሠራዊት ነን፤ የትግራይ አስተዳዳሪዎች ነን፤ የወረዳ እና የዞን አስተዳዳሪዎች ነን። እዚህ ያለው መንግሥት አላቀፈንም፤ አይወክለንም። የሚያቅፈንና የሚወክለንን መንግሥት ለማቋቋም ስምምነት ነበረ። ነገር ግን ያ ስምምነት አልተፈጸመም፤ ስለዚህ ድርሻችን ይገባናል ነው እያሉ ያሉት።"
የደኅንነት ስጋት
አቶ አሰፋ በእሳቸው እንዲሁም በአቶ ጌታቸው ረዳ እና ጄነራል ፃድቃን ገብረትንሳይ ላይ "የደኅንነት ስጋት" ማንዣበቡን ለቢቢሲ ትግርኛ ገልጸዋል።
"በአገራችን በመቀለ መኖርና መሥራት የማንችልበት የደኅንነት ሁኔታ ፈጥርው፤ ጌታቸው እንዴት ብሎ እንደወጣ ታውቃለህ" ብለዋል።
አክለውም "አጃቢህ ብለው የመደቡልኝን ሰው መልምለው፣ በእኔ አማካኝነት እኔን ጨምሮ ጌታቸውን እና ፃድቃንን ለመግደል ተልዕኮ ተሰጥቶት ራሳቸው ናቸው በቤቴ የያዙት" በማለት ተናግረዋል።
አቶ አሰፋ ጨምረውም፤ የአሜሪካ መንግሥት በአቶ ጌታቸው እና በጄነራል ፃድቃን ላይ "የተቀነባበረ ግድያ አለ" በሚል እንዳስወጧቸው ገልጸዋል።
"በኋላም ሰምተናል፤ የሆኑ ሰዎች ቤቱ ጋር መጥተው ተይዘዋል። ስለዚህ ርቀው ሄደዋል፤ እዚህ ላይ ብዙም ባንደንደባበቅ" ሲሉም ተናግረዋል።