ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጦር ወንጀል ማስረጃ እንዲጠፋ ተባብሯል መባሉን አጣጣለ
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በምዕራብ ትግራይ የትግራይ ተወላጆች በጅምላ መቀበራቸውን የሚያሳይ የጦር ወንጀል ለመደበቅ የአማራ ሚሊሻዎችን ረድቷል የሚለውን ሪፖርት አጣጣለ።
ቢቢሲ ከቀናት በፊት ባወጣው ዘገባ ላይ የዓይን እማኞች የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች የጦር ወንጀል ማስረጃዎችን እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል ለሚሊሻ አባላት ምክር ሲሰጡ አይተናል ብለዋል።
የዓይን እማኞቹ እንደሚሉት፣ አስክሬኖችን በማቃጠል ማስረጃ ማስወገድ የተጀመረው እአአ ሚያዝያ 4 ሲሆን፣ ይህም በጎንደር ዩኒቨርስቲ ባለሙያዎች ክትትል እየተደረገ ነው የተከናወነው።
የዘገባውን መውጣት ተከትሎ ዩኒቨርሲቲው ለቢቢሲ በላከው ደብዳቤ ላይ ዘገባውን፤ "በመረጃ ያልተደገፈ መሠረተ ቢስ ክስ" ብሎታል።
ከዚህ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በጅምላ የተቀበሩ የትግራይ ተወላጆች አስክሬን አልተገኘም ብሏል።
መሰል ግኝቶች ቢኖሩ፤ "የተመራማሪዎች ቡድን . . . ቀድሞ እውቅና እንደሚኖረው እና ማስረጃ ያቀርብ እንደነበረ" ዩኒቨርሲቲው ገልጿል።
ዩኒቨርሲቲው በደብዳቤው የሕብረተሰቡን አንገብጋቢ ችግሮችን መፍታት ላይ የሚያተኩር እና በኢትዮጵያ ከሚገኙ የትምህርት ተቋማት መካከል የከበረ ስም ያለው መሆኑን በደብዳቤው ገልጿል።
የጎንደር ዩኒቨርስቲ አጥኚዎች የጅምላ መቃብሮች እንዳገኙና እነዚህ መቃብሮች በህወሓት ከተፈጸሙ ግድያዎች ጋር የተያያዙ እንደሆኑ አስታውቀዋል።
ባለፈው ወር የመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጎንደር ዩኒቨርስቲ 12 የጅምላ መቃብሮች ላይ ምርምራ እያደረገ እንደሆነ ገልጸው ነበር።
እነዚህ የጅምላ መቃብሮች፣ ህወሓት በዘር ጭፍጨፋ እጁ እንዳለበት ጠቋሚ መሆናቸውም ተዘግቧል።
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ተሳታፊ የሆኑት የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የአማራ፣ የትግራይ ኃይሎች በአጠቃላይ የጅምላ ግድያ በመፈጸም ይወነጀላሉ።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዋች በቅርቡ ባወጡት ሪፖርት፣ የአማራ ክልል ባለሥልጣናትና የደኅንነት አባሎች በአካባቢው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ የዘር ማጽዳት ፈጽመዋል ብለው ነበር።