ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ በምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት መመዝገቡ ተገለጸ
በኢትዮጵያ በምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛው የዋጋ ግሽበት እየተመዘገበ መሆኑን የአገሪቱ ብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት ገለጸ።
ምክር ቤቱ የዘጠኝ ወራት የምጣኔ ሀብት አፈጻጸምን ገምግሞ ባወጣው በዛሬው ግንቦት 2፣ 2014 ዓ.ም መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት ከፍተኛ ፈተና እየገጠመው ያለው ከዋጋ ግሽበት አንጻር መሆኑን ጠቁሟል።
በዚህም የዋጋ ግሽበቱ በዋናነት በምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መመዝገቡን ጠቅሶ፤ ይህም ካለፈው ዓመት የሚያዝያ ወር ጋር ሲነጻጸር የዋጋ ግሽበቱ 36.6 በመቶ መመዝገቡን አስፍሯል።
ምክር ቤቱ ጨምሮም ባለፉት ሦስት ዓመታት የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አሐዝ ለማውረድ በርካታ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቅሶ ነገር ግን በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ምክንያት የሚፈለገው ውጤት አልመጣም ብሏል።
ለዚህም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የጥሬ ዕቃዎች ዋጋ መናር፣ በአገር ውስጥ ያጋጠሙ ግጭቶች እና የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት የፈጠረው ዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዋጋ ግሽበት እንዲያሻቅብ ምክንያት መሆኑን አመልክቷል።
መንግሥት የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ የጠቀሰው መግለጫው፤ ከእነዚህም ውስጥ የመንግሥት ወጪን ከአገር ውስጥ ገቢ መሸፈን፣ የግብር ሥርዓቱን ማዘመን እና የተለያዩ ግብርን የተመለከቱ ማሻሻያዎች ማድረግ በቀጣይ ተግባራዊ ይሆናሉ ተብሏል።
ምግብ ነክ የሆኑና መሠረታዊነታቸው የታመነባቸው የፍጆታ ዕቃዎች በፍራንኮ ቫሉታ አሠራር ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መፈቀዱን እንዲሁም፣ የመድኃኒት፣ ነዳጅ፣ ማዳበርያ፣ ዘይት እና ሌሎችም መሠረታዊ ሸቀጦች ግዢ አቅርቦት አቅርቦት እንዲቀላጠፍ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገልጿል።
ነዳጅን በተመለከተ ደግሞ ሁሉን አካታች ከሆነ የመንግሥት የነዳጅ ድጎማ ቀስ በቀስ በመውጣት ድጎማ ለሚያስፈልጋቸው አካላት ብቻ እንዲሆን እየተሠራ ነው ተብሏል።
ብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት በተፈጥሯዊና በሰው ሰራሽ አደጋዎች በተፈጠሩ ጫናዎች በእጅጉ መፈተኑን ገልጾ፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት እና ድርቅን በዋናነት አንስቷል።
ቢሆንም ግን በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሩብ ዓመታት ላይ የተመዘገበው ዕድገትን መሠረት በማድረግ የዓመቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት በአማካይ በ6.6 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል።
ጨምሮም በአገሪቱ የብድርና ቁጠባ መጠን ላይ ጭማሪ መታየቱን በመጥቀስ፣ የባንኮች አጠቃላይ የቁጠባ መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ25 በመቶ ከፍ ብሎ ወደ 1.6 ትሪልዮን ብር መድረሱ ተገልጿል።
በዘጠኝ ወራቱ ውስጥ ከውጭ ንግድ 2.95 ቢሊየን ዶላር እንደተገኘና ከዚህ ውስጥ ደግሞ 2.05 ቢሊየን ዶላር የሚሆነው ከግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ የተገኘ ነው።
በተከታይነት ደግሞ የማዕድን ዘርፉ 453 ሚልዮን ዶላር እና አምራች ኢንዱስትሪው 378.5 ሚልዮን ዶላር ገቢ ተገኝቶባቸዋል ተብሏል።