ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዛሬ ማታ ቬነስ እና ጁፒተር ከመቼውም በላይ ተጠጋግተው ይታያሉ
ዛሬ ማታ ትክክለኛው ሰዓት ላይ ወደ ሰማይ ካማተሩ፣ ዕድለኛ ሆነው ቬነስ እና ጁፒተር እጅጉን ተጠጋግተው ያያሉ።
ሁለቱ ደማቅ ፕላኔቶች ዛሬ ምሽት ለመነካካት ጥቂት እስከሚቀራቸው ድረስ ነው የሚቀራረቡት።
ፕላኔቶቹ በየዓመቱ ይቀራረባሉ። ዘንድሮ ግን ከመቼውም በበለጠ ነው የሚጠጋጉት።
ከመሬት ሲታዮ ደግሞ ሊጋጩ የደረሱ ይመስላሉ።
ይህንን አይነት ክስተት እስከ ጎርጎሮሳውያኑ 2039 ድረስ በድጋሚ አያጋጥመንም።
ክስተቱን ዛሬ ምሽት በዐይን ወይም በአጉሊ መነጽር መመልከት ይቻላል።
ከዛሬ በኋላ ሁለቱ ፕላኔቶች ተለያይተው ወደ የቀድሞው መስመራቸው ይመለሳሉ።
የሕዋ ሳይንቲስት እና ሶሳይቲ ፎር ፖፑላር አስትሮኖሚ ውስጥ ዋና የከዋክብት ተመልካች ፕ/ር ሉሲ ግሪን እንዳሉት፣ ክስተቱ ለከዋክብት አጥኚዎች ብቻ ሳይሆን ለተቀረው ማኅበረሰብም አስደናቂ ነው።
የፕላኔቶች መቀራረብ ምንድን ነው?
ፕላኔቶች በጣም ሲጠገጋጉ ወይም በስሱ ሲነካኩ በእግሊዘኛ planetary conjunction ተፈጠረ ይባላል።
ባለፉት ቀናት ቬነስ እና ጁፒተር ቀስ በቀስ እየተቀራረቡ ነበር።
በመካከላቸው ያለው ርቀት 430 ሚሊዮን ማይል ቢሆንም ከመሬት ወደ ሰማይ ሲታይ የሚነካኩ ይመስላል።
ክስተቱ ዛሬ ምሽት 1 ሰዓት አካባቢ (በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር) ይታያል ተብሎ ይጠበቃል።
ፕላኔቶቹ ሲቀራረቡ ዝቅ ብለው ነው የሚታዮት። ከፍ ያለ አካባቢ ቢሆኑ በደንብ ሊመለከቷቸው ይችላሉ።
ፕ/ር ሉሲ እንደገለጹት፣ ሁለቱ ፕላኔቶች ደማቅ ስለሆኑ ከሌሎች በተለየ ጎልተው ይታያሉ።
ቬነስ ከጁፒተር ትደምቃለች።
"ጁፒተር ከቬነስ ደብዘዝ ትላለች። ብርሃኗ የቬነስ አንድ ስድስተኛ ነው" ይላሉ ፕ/ር ሉሲ።
በበይነ መረብ ላይ የፕላኔቶችን እንቅስቃሴ የሚከታተሉ መተግበሪያዎች አሉ።
ምሽት ላይ ፕላኔቶቹ የት ጋር እንዳሉ ለማግኘት ከእነዚህ መተግበሪያዎች አንዱን መጠቀም ይችላሉ።
አጉሊ መነጽር ካለዎት ደግሞ ጁፒተርን ውስጧ ካሉ ጨረቃዎች ጭምር ሊያዮ ይችላሉ።
ማርስ እና ሳተርን ተደርድረው የአራት ፕላኔቶች መስመር ለማየትም አጉሊ መነጽር ሁነኛ ነው።
በተለያየ የሰዓት ዑደት ውስጥ ያሉ ሰዎች ክስተቱን እንደአካባቢያቸው ሰዓት አቆጣጠር በቀን ወይም በምሽት ያዩታል።
ዛሬ ማታ ሁለቱ ፕላኔቶች ተጠጋግተው ማየት ባይችሉ እንኳን ከዛሬ በኋላ ቀስ በቀስ እየተራራቁ ሲሄዱ መመልከትም ሌላ አማራጭ ነው።