የብራዚሉ ፕሬዝዳንትና የሆሊውዱ ሊዮናርዶ ዲካፕሪዮ በአማዞን ደን ምክንያት እየተናቆሩ ነው

የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ጃይር ቦልሶናሮ እና የሆሊውዱ ተዋናይ ሊዮናርዶ ዲካፕሪዮ የአማዞን ጫካን አስመልክተው አንድ ሁለት እየተባባሉ ነው።

የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቹ ዲካፕሪዮ፣ የብራዚል ሕዝብ ለአማዞን ደን ደኅንነት ሲል በቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ ድምጽ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል።

ቦልሶናሮ ግን የዲካፕሪዮ አስተያየት አልጣማቸውም።

ዲካፕሪዮ "ብራዚል ለብዝሀ ሕይወት ቀጣይነት መሠረት የሆነው የአማዞን ደን ባለቤት ናት። ጤናማ ምድር እንዲኖረን የብራዚል ወጣቶች በቀጣዩ ምርጫ ድምጻቸውን ማሰማት አለባቸው" ብሏል።

የአካባቢ ጥበቃ ሕግጋትን የቀነሱት ቦልሶናሮ ግን በዲካፕሪዮ ንግግር ተሳልቀዋል።

"ሊዮ፣ ስለ ድጋፍህ እናመሰግናለን። በመጪው ምርጫ ሁሉም ብራዚላዊ ድምጽ መስጠት አለበት" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

አክራሪ ቀኝ ዘመሙ ቦልሶናሮ፣ የብራዚል ሕዝብ አማዞን ደንን በተመለከተ "የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት" አልያም "አገር በቀል ውሳኔ" እንደሚያሳልፍ የሚታይበት ምርጫ እንደሆነም ጠቆም አድርገዋል።

ዲካፕሪዮ እአአ በ2019 ለአማዞን ደን ጥበቃ 5 ሚሊዮን ዶላር ለግሷል።

ቦልሶናሮ ደግሞ ደኑ እንዲጨፈጨፍ በመፍቀድ ይተቻሉ።

አማዞን የዓለማችን ትልቁ ባለ ብዝሀ ሕይወት ደን ነው። የምድራችን 'ሳምባ' እየተባለም ይሞካሻል።

ቦልሶናሪ ይህ የተፈጥሮ ኃብት እንዲበዘበዝ ፈቅደዋል ተብለው ይታማሉ። አስተዳደራቸው በበኩሉ ድህነትን እየተዋጋ እንደሆነ ይከራከራል።

የሳተላይት መረጃ እንደሚያሳየው፣ ዘንድሮ ጥር ላይ የተጨፈጨፈው ደን ከአምናው አምስት እጥፍ ይልቃል።

የአማዞን ደን ከከባቢ አየር ካርበንን ጨምቆ ይወስዳል። ዛፍ ሲቆረጥ ግን የካበን ልቀት ወደ አየር ይዋሀዳል። ይህም የአየር ንብረት ለውጥን ያፋጥናል።

ዲካፕሪዮ እና ቦልሶናሮ ሲወዛገቡ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።

በ2019 ቦልሶናሮ ዲካፕሪዮን "አማዞን እንዲቃጠል ገንዘብ ሰጥቷል" ብለው ከሰዋል።

ቦልሶናሮ ለክሳቸው ማስረጃ አላቀረቡም።

ፕሬዝዳንቱ ፖሊሲያቸውን የሚነቅፍ ማንኛውም የተፈጥሮ ጥበቃ ድርጅት ወይም ተሟጋችን ከማጠልሸት ወደኋላ አይሉም።

ብራዚል አማዞንን መጠበቅ ካልቻለች፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ማንኛውንም ዓይነት የአካበቢ ጥበቃ ስምምነት ከብራዚል ጋር እንዳይፈርሙ የሚጠይቀው የዝነኞች ቡድን ውስጥ ዲካፕሪዮም ይገኝበታል።