ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በግርግር ሥርዓተ ቀብራቸው የተቋረጠው የጎንደሩ ሼኽ ቀብር ዛሬ ይፈጸማል ተባለ
በጎንደር ከተማ ከትላንት በስቲያ ሚያዝያ 18፣ 2014 ዓ. ም ሥርዓተ ቀብራቸው ሊፈጸም ባለበት ወቅት በተነሳ ግርግር የተስተጓጎለው የሼኽ ከማል ለጋስ ሥርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት እንደሚፈጸም ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት (ሚያዝያ 20፣ 2014 ዓ. ም. ረፋድ ላይ) ወደ ቀብር ስፍራው እያመሩ እንደሆነ የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የመስጅድ እና የዕውቀት ዘርፍ ኃላፊ ሐጂ ዑስማን ዑመር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከትላንት በስቲያ በተነሳው ሁከት ከ20 በላይ ሰዎች በመሞታቸውና ከ150 ሰዎች በላይ የአካል ጉዳት ስለደረሰባቸው በትናንትናው ዕለት የማረጋጋት ሥራ እየተሠራ ነበር ብለዋል ሐጂ ዑስማን።
የሼኽ ከማል ለጋስ የቀብር ሥነ ሥርዓት ግጭቱ በተነሳበት ሼኽ ኤሊያስ መካነ መቃብር እንደሚፈጸምም ሐጂ ዑስማን ለቢቢሲ አክለው ገልጸዋል።
ከትናንት በስቲያ በተነሳው ግጭት ከሰዎች ሕይወት መጥፋትና ከአካል ጉዳት በተጨማሪም መስጂዶች መቃጠላቸውንና የሙስሊሙ ኅብረተሰብ በተለይም የነጋዴው ሀብት ንብረት መዘረፉንም ሐጂ ዑስማን አስረድተዋል።
ሐጂ ዑስማን "ይሄ በግልጽ ታስቦበት ታቅዶበት የተደረገ ሴራ ነው።" ያሉ ሲሆን፣ በቦምብ ሰዎች መቁሰላቸውን እንዲሁም ጥቃቱ ወደ ከተማው ተስፋፍቶ መጠነ ሰፊ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል።
ከትናነት በስቲያ የቀብር ሥርዓታቸው የተስተጓጎለው ሼኽ ከማል በከተማው ትልቅ አባትና በአገር በቀል የሕክምና ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋዕኦ ያደረጉ መሆናቸውን ሐጂ ዑስማን ገልጸው "እኚህን አባት በክብር ለማሳረፍ በተደረገው ሂደት ላይ ነው አጸያፊ ድርጊት የተፈጸመው" ብለዋል።
"እኚህ አባት ለጎንደር ከተማ ሙስሊም እንዲሁም ክርስቲያንም ትልቅ አርዓያ የሆኑ አባት ናቸው። የኋላ እሴቶቻችንና የኋላ ታሪኮቻችን ስናስታውስ የመከባበበሩ፣ የመቻቻሉና የአብሮነት እሴቶች እየተሸረሸሩ መሆኑን በግልጽ የሚያመላክት ድርጊት መሆኑን ነው በኛ በኩል የተረዳነው። ይሄ አስተሳሳብ በጊዜ መታረቅ ካልቻለ ወደፊትም የከፋ ችግር ይከሰታል" ሲሉም ኃላፊው ምክራቸውን ለግሰዋል።
የክልሉ፣ የፌደራሉ መንግሥትና የሃይማኖት አባቶች በተለይም የክርስትና ሃይማኖት አባቶች ይህንን ጉዳይ እንዲያወግዙት፣ አጥፊዎችን ወደ ሕግ እንዲያቀርቡ፣ ተቀራርቦና ተከባብሮ የኖረውን ኅብረተሰብ ወደነበረው ማንነቱ እንዲመለስ በማድረግ ረገድ ሰፊ ሥራዎች እንዲሠሩም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ይህንንም ተከትሎ በአዲስ አበባ በአንዋር መስጅድ በትናንትናው ዕለት ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል።
ግጭቱ በተነሳበት እለት ምሽት ላይም አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኝ መስጅድ ሰላማዊ ሰልፍ መካሄዱ ይታወሳል።
ትላንት በአንዋር መስጅድ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ 'ፍትህ ለጎንደር ሙስሊሞች'፣ 'ደሴቱ ሰላም እንዲሆን ባሕሩን አትንካ' የሚሉና ሌሎችም ጠንካራ መልዕክት ያዘሉ መፈክሮች ተሰምተዋል።
በተለይም በተከበረው የረመዳን ጾም ወቅት ይህ ግጭት መነሳቱ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ተወግዟል።
ግጭቱ እንዴት ተነሳ?
የአማራ ክልል መንግሥት እንዲሁም ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ግጭቱ የተነሳው በሼኽ ከማል ለጋስ ቀብር ወቅት በመካነ መቃብሩ ስፍራ አጠገብ ካለው ቤተ ክርስቲያን ድንጋይ ተነስቷል በሚል እንደሆነ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸው የጎንደር ነዋሪ፣ የግጭቱ መነሻ ለሼኹ ቀብር የወጡ ሰዎች ከመካነ መቃብሩ አጎራባች ካለችና አዲስ ከተሠራችው ቤተ ክርስቲያን ድንጋይ ለማንሳት በመሞከራቸው ነው ይላሉ።
"ከቤተ ክርስቲያኗ ድንጋይ ሲያነሱ ለምን ታነሳላችሁ? የሚል ነው የግጭቱ መንስዔ ከዚያ በኋላም ወደ ቡድን ግጭት ተቀየረ" ይላሉ።
ሐጂ ዑስማን በበኩላቸው "ይህ የተሳሳተ ነው። ቀብር ሲፈጽሙ ድንጋይ የሚያነሱት እዛው ቦታቸው ላይ ነው። ከቤተ ክርስቲያን ክልል ውስጥ አይደለም። በሌሎች አካላት የተሰጠው መግለጫ ተቀባይነት የሌለውና ወንጀለኞችንና አጥፊዎችን ላለመያዝና ጥፋተኞችን ወደኛ ለማድረግ የሚደረግ ሙከራ ነው" ብለዋል።
ለዚህ ግጭት መነሻ ሊሆን የሚችል ጉዳይ የለም ያሉት ሐጂ ዑስማን፣ "አንድ አገር፣ አንድ ሃይማኖት የሚሉ ፅንፈኛ አክራሪዎች የፈጸሙት ድርጊት ነው" ይላሉ።
"ይህች አገር የኛ ብቻ ናት የሚል አስተሳሰብ ካልሆነ" የሚሰጠው ምከንያት ስህተት ነው ሲሉም ያስረዳሉ።
ሌላኛው የጎንደር ነዋሪ በበኩላቸው፣ እንዲህ ዓይነት ሃይማኖታዊ ግጭት በጎንደር ተከስቶ እንደማያልቅ ተናግረው "ታላቅ አባት ሞተው በቀብር ድንጋይ ነው ግጭቱ ተነሳ የተባለው። ይህ ምክንያት አይሆንም። በመሃል የገቡ አንዳንድ ችግር ፈጣሪዎች ነበሩ" አሁን ግን በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል።
ሐጂ ዑስማን በትናንትናው ዕለት የተፈጠረው ግጭት አዲስ እንዳልሆነና ላለፉት ሰባትና ስምንት ዓመታት ሲንከባለል የመጣ ችግር እንደሆነ ያስረዳሉ።
"በሆደ ሰፊነት ችግሩ እንዲፈታ በተደጋጋሚ በደብዳቤ፣ በአካልም ከሚመለከታቸው የመንግሥት መዋቅሮች ጋር ሰፊ ውይይት ለማድረግ ጥረት አድርገናል" የሚሉት ሐጂ ዑስማን፣ "ነገር ግን የመንግሥት አመራሮች ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠታቸው የተፈጠረ ችግር ነው" ይላሉ።
በአሁኑም ወቅት በሕግ አግባብ ችግሮች እንዲፈቱ፣ አጥፊዎች እንዲያዙ፣ ወንጀለኞች እንዲቀጡ፣ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ የማድረግ ሥራዎችን እየሠሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
በትናነትናው ዕለት የፀጥታ መሻሻል የታየ ሲሆን "ሕዝበ ሙስሊሙ እንዲረጋጋ፣ በሕግና በሕግ ብቻ መብቱን እንዲያስከብር የማረጋጋት ሥራዎች እየተሠሩ ነው"ብለዋል።