አደገኛ 'መቅሰፍት' ከመከሰቱ በፊት አስቀድመው የሚያውቁ እንስሳት

የዓይን እማኞች እንደሚሉት እአአ 2004 ላይ ሱናሚ ከመከሰቱ በፊት ዝሆኖች ከፍ ወዳለ ቦታ ወጥተው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዓይን እማኞች እንደሚሉት እአአ 2004 ላይ ሱናሚ ከመከሰቱ በፊት ዝሆኖች ከፍ ወዳለ ቦታ ወጥተው ነበር።

የሱናሚ ርዕደ መሬት እንደሚከሰት አንዳንድ እንሰሳት ቀደም ብለው ያውቁ ነበር፡፡

ሱማኒ ትዝ አላችሁ? በሬክተር መጠን 9.1 የተመዘገበውን፡፡ 225ሺህ ሰዎችን የጨረሰውን፡፡ በኢንዶኒዢያ ጠረፍ በሕንድ ውቅያኖስ አቅራቢያ የተከሰተውን?

ያ 'መቅሰፍት' እንደሚመጣ አንዳንድ እንሰሳት ቀድመው ያውቁ ነበር፡፡ ነገር ግን ሳይንቲስቶች ንቀዋቸው አልሰሟቸውም፡፡

ሳይንቲስቶች የሚመኩት በርዕደ መሬት መለኪያ መሣሪያ ነበር፡፡ ያ ግን አልሠራም፡፡ ወይም እንቅጩን አልተናገረም፡፡

ከዚያ ሱናሚ ድንገት ተከሰተ፡፡ ሩብ ሚሊዮን ሕዝብ በልቶ ጭጭ አለ፡፡ ይህ አሳዛኝ ክስተት ካለፈ ከዓመታት በኋላ በሕይወት የተረፉ ሰዎች ምስክርነት መስጠት ጀመሩ፡፡

አንዳንድ እንሰሳት ቀደም ብለው ይህ 'መቅሰፍት' እንደሚመጣ ምልክት አሳይተው እንደነበረ ተናገሩ። ለምሳሌ ይላሉ ዝሆኖች ያን ግዙፍ ሰውነታቸውን ይዘው ከፍ ወዳለ ቦታ ለመውጣት ተፍ ተፍ ሲሉ ነበር፡፡

አገሬው ምን ነካቸው እስኪል ድረስ፡፡ ፍላሚንጎዎችም ቢሆኑ ጎጇቸውን ትተው እየሸሹ ነበር፡፡ ውሾችደግሞ ደጅ አልወጣ ብለው ማስቸገር ጀምረው ነበር፡፡

በታይላንድ ድንበር ላይ የባንግ ኮይ ነዋሪዎች እንደመሰከሩት ከሱናሚ በፊት ጎሾች (buffalo) ጆሯቸውን መቀሰር አብዝተው ነበር፡፡

ደግሞ ወደ ባሕር ዝም ብለው አፍጥጠው ይመለከቱ ነበር፡፡ ሱናሚ ከመድረሱ በፊት ደግሞ ቶሎ ወደ ከፍታ ቦታ ለመሄድ መሽቀዳደም ጀምረው እንደነበረም ተስተውሏል፡፡

ኢሪና ራፍሊያና በተባበሩት መንግሥታት የአደጋ ዝግጁነትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ክፍል ባልደረባ ነበሩ፡፡ 'ሱናሚ ከመምጣቱ ቀደም ብሎ ላሞች፣ ፍየሎች፣ ድመቶችና ወፎች ባልተለመደ ሁኔታ ወዲያ ወዲህ ይራወጡ ነበር፡፡ ከባሕሩ ርቀው ለመሄድም ይጣጣሩ ነበር፡፡' ሲሉ ከዐይን ምስክር ያገኙትን ተናግረዋል፡፡

የእነዚህ እንሰሳት ያልተጠበቀ ባሕሪ ያስፈራቸውና ከእንሰሳቱ ጋር የተሰደዱ ጥቂት ሰዎችም ከሱናሚ ሕይወታቸውን ታድገዋል፡፡

በሌላ አነጋገር እንሰሳቱን ያመኑ ድነዋል፡፡

ሳይንስ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘመናዊ መሣሪያዎች ረገድ ብዙ ርቀት አልሄደም፡፡

ያሉትም መሣሪያዎች ቢሆኑ ወይ ጥገና የሚሹ ናቸው ወይም ደግሞ በሁሉም አካባቢ ሊተከሉ አልቻሉም፡፡ ብቻ ከአልግሎት ውጭ ነበሩ፡፡

በዓለም ላይ 100 አገራት ዘመናዊ የሚባል የቅደመ አደጋ ማስጠንቀቂያ መሣሪያ የላቸውም፡፡

በእርግጥ እንሰሳት ወደፊት የሚመጣን መቅሰፍት የማወቅ ጸጋ ተሰጥቷቸው ይኾን?

በዚህ ረገድ ታሪክ የሰነደው ዶሴ ያለው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ373 ነው፡፡

የግሪክ ታሪከኛ ታይዲድስ እንደዘገበው በአንድ የዚያ ወቅት ውሾችና እባቦች እንዲሁም አቁሽጣ (ሸለመጥማጥ የሚመስል አውሬ) የሐሊስ ከተማን ለቅቀው ፈረጠጡ፡፡

ከቀናት በኋላ መሬት ነቅንቅ ርዕደ መሬት ተከሰተ፡፡

ተመራማሪዎች ፍየሎች የእሳተ ጎሞራ ፍንዳታን ከመከሰቱ ቀድሞ ያውቁ እንደሆነ ለመለየት አንገታቸው ላይ መሳሪያ ገጥመው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Christian Ziegler/MPI-AB

የምስሉ መግለጫ, ተመራማሪዎች ፍየሎች የእሳተ ጎሞራ ፍንዳታን ከመከሰቱ ቀድሞ ያውቁ እንደሆነ ለመለየት አንገታቸው ላይ መሳሪያ ገጥመው ነበር።

ወደ ቅርብ ታሪክ እንምጣ፡፡

በ1805 ኔፕልስ ክፉኛ በመሬት መንቀጥቀጥ ተመትታ ነበር፡፡ ከቀናት በፊት ግን በሬዎች፣ በጎች፣ ውሾችና ዝዮች (geese) በአንድ ሆነው ያላዝኑ፣ ይጮኹ ነበር፡፡

ፈረሶች ደግሞ ድንገት እግሬ አውጪኝ ማለት ጀመሩ፡፡ የአገሬው ሰው ግራ ገባው፡፡ በቀናት ውስጥ ታዲያ ኔፕልስ እንዳልነበረች ሆነች፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በ1906 ሳንፍራሲስኮ ተመሳሳይ ነገር ሆኗል፡፡ ፈረሶች ከመሬት ተነስተው ይደነብሩ ነበር፡፡

ይደነብሩ የነበረው የሚመጣው ቀድሞ ታይቷቸው ነው፡፡ የሰው ልጅ ግን ይህን ለመረዳት ዘግይቶ ነበር፡፡

ቻርሎቴ ፍራንሲያዝ የዚህ ዘርፍ ባለሙያ ናቸው፡፡

"በዚህ ሁሉ ሥልጣኔያችን የእንሰሳቱን ያህል እንኳ ነገ የሚሆነውን ቀድመው ለመናገር አለመቻላችን ይገርመኛል" ይላሉ፡፡

የእንሰሳቱን አቅም ትክክለኝነት ለማረጋገጥ አንድ ሁነኛ ጥናት ተደርጓል፡፡

ይህም የሆነው የመሬት መንቀጥቀጥ በማያጣው ማርቼስ በሚባለው ማዕከላዊ ጣሊያን ውስጥ ነው፡፡

በዚህ ግዛት ሳይንቲስቶቹ የእንሰሳቱን አካሄድ መከታተከል ጀመሩ፡፡ ውሾች፣ በጎችና ላሞች በጥናቱ ተሳተፉ።

በእነዚህ እንሰሳት ላይ እንቅስቃሴያቸውን የሚያነብ መሣሪያ ተገጠመ፡፡ ይህ መሣሪያ የእንሰሳቱን እያንዳንዱን እንቅስቃሴና ምህዋር ወደ ኮምፒውተር ይሰዳል፡፡

ይህ ጥናት ከ2016 ጀምሮ ለአንድ ዓመት ቀጠለ፡፡ በዚህ አንድ ዓመት በዚህ የጣሊያን ክፍል 18ሺህ አነስተኛ መሬት መንቀጥቀጦች ተከስተዋል፡፡

ታዲያ አብዛኛዎቹ በመሣሪያ ብቻ የሚመዘገቡ ነበሩ፡፡ በሬክተር መለኪያ 0.4 አካባቢ የሆኑ በጣም አነስተኛ ንቅናቄዎች፡፡

በእርግጥ ኋላ ላይ 6.6 የተመዘገበ የኖርሺያ ጠንካራ ርዕደ መሬትም ተከስቶ ነበር፡፡

ታዲያ እንሰሳቱ ይህ እንደሚሆን ቀደም ብለው አወቁ ወይስ ነገሩ የፈጠራ ወሬ ነው?

በእርግጥ ወሬ አይደለም፡፡

እንዲያውም ሳይንቲስቶቹን ያስገረመ ውጤት ነበር የተገኘው፡፡

ሁሉም የመሬት መንቀጥቀጦች ከመከሰታቸው ከ20 ሰዓት ቀደም ብሎ እንሰሳቱ ባሕሪያቸውና እንቅስቃሴያቸው እንደተለወጠ ማስተዋል ችለዋል፡፡

በሲሲሊም ተመሳሳይ ጥናት በ2020 ተደርጎ ተቀራራቢ ውጤት ታይቷል፡፡

አሁን ሳይንቲስቶቹ እያጠኑ ያሉት እንሰሳቱ ርዕደ መሬት ከመከሰቱ በፊት እንዲያውቁ ያስቻላቸው ምንድን ነው የሚለውን ነው፡፡

ለሰው ልጅ ያልተሰጠ ምን ዐይነት ጸጋ ቢኖራቸው ነው እንሰሳት ነገን ማወቅ የቻሉት?

ጥናቱ ቀጥሏል፡፡