ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቤልጄየም በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ መኪና በፍጥነት ተነድቶ 6 ሰዎች ሞቱ
በሰሜን ቤልጄየም በምትገኝ አነስተኛ ከተማ አንድ ግለሰብ ለባህላዊ ክብረ በዓል አደባባይ በወጡ ሰዎች ላይ መኪና በፍጥነት ነድቶ 6 ሰዎችን ገደለ።
ይህ ክስተት ያጋጠመው ትናንት እሁድ ከመዲናዋ ብራሰልስ 50 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በምትገኘው አነስተኛ ከተማ ነው።
ከሞቱት ስድስት ሰዎች በተጨማሪ ከ40 ያላነሱ ሰዎች መቁሰላቸውን እና ከእነዚህም መካከል ለሕይወታቸው አስጊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ እንዳሉበት የከተማዋ ከንቲባ ተናግረዋል።
"ከ150-200 የሚሆኑ ሰዎች በዓሉ ወደሚከበርበት ቦታ እየሄዱ ሳለ መኪናው ከጀርባቸው መጥቶ ገጫቸው" ብለዋል ከንቲባ ጃኩዌስ ጎበርት።
ግለሰቡ መኪናውን በሕዝብ መሃል በፍጥነት እያሸከረከረ ለ100 ሜትር ያክል መሄዱን ያስታወሱት ከንቲባው፤ "ይህ ብሔራዊ አደጋ ነው" ሲሉ የክስተቱን መጠን አጉልተዋል።
በጉዳዩ ላይ ምርመራ መጀመሩን ያስታወቀው ፖሊስ ይህ ድርጊት ከሽብር ጥቃት ጋር አይገናኝም ብሏል።
"አሰቃቂ የሆነ አደጋ ነው። መኪናው ሰዎችን ገጭቶ ለማምለጥ ሞክሮ በፖሊስ እንዲቆም ተደርጓል" ሲሉ የፖሊስ ቃል አቀባይ ክርስቲና ላኖኮ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከአሸከርካሪው ጋር ሌሎች ሰዎችም በመኪናው ውስጥ እንደነበሩ የገለጹት ቃል አቀባይዋ፤ ሁሉም በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብለዋል።
የቤልጄየም የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር አኔሊስ ኤርሊንደን በትዊተር ገጻቸው በክስቱት ለሞቱ ሰዎች ወዳጅ ዘመዶችን መጽናናትን ተመኝተዋል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዲ ክሮ አደጋው ያጋጠመበትን ስፍራ በቅርቡ ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።