ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሃይማኖት በዳዳን የገደላት ግለሰብ የ21 ዓመት እስር ተፈረደበት
በጥቁር አንበሳ የጤና ኮሌጅ የህክምና ተማሪ የነበረችውን ሃይማኖት በዳዳን የገደላት ግለሰብ የ21 ዓመት ፅኑ እስር እንደተፈረደበት የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የከባድ የሰው ግድያና የውንብድና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በዛሬው ዕለት ታህሳስ 28፣ 2014 ዓ.ም ደግነት ወርቁ በተባለው ተከሳሽ ላይ የ21 ዓመት ፅኑ እስራት ብያኔ አስተላልፏል።
የ2ኛ ዲግሪ መመረቂያ የምርምር ስራዋን በመስራት ላይ የነበረችው ሃይማኖት በዳዳ አሰቃቂ በሚባል ሁኔታ በስለት ተወግታ የተገደለችው ግንቦት 17፣ 2012 ዓ.ም ነበር።
በፍትህ ሚኒስቴር ማህበራዊ ትስስር ገፅ የሰፈረው የዓቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ደግነት ወርቁ የተባለው ግለሰብ በተጠቀሰው ዕለት ከቀኑ 9 ሰዓት ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግቢ ውስይ ከሚገኝ የፋርማሲ ትምህርት ቤት ህንፃ አራተኛ ፎቅ ቤተ ሙከራ ውስጥ ነው የገደላት።
ግለሰቡ የቤተ ሙከራ በሩን ከፍቶ ከገባ በኋላ በሩን በመቆለፍ በቢላ ደረቷን እንደወጋትና አንገቷንም በቢላዋ ያረዳት ሲሆን በዚህም የአንገቷ የደም ስር በመቆረጡ ምክንያት ከመጠን በላይ በሆነ ሁኔታ ደም ፈሷት ህይወቷ አልፏል።
ተከሳሹ የሃይማኖትን ህይወት ካጠፋ በኋላ አይፎን ስልክ፣ ላፕቶፕ፣ ቼክና ጥሬ ገንዘብ በጠቅላላው 27 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት እንደወሰደ የዓቃቤ ህግ ክስ ያስረዳል።
ግለሰቡ በ20ዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኝና የአስራ ሁለተኛ ክፍል የአርባ ምንጭ ነዋሪ መሆኑንም በወቅቱ በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት ተዘግቦ ነበር።
ተከሳሹ ከሟችም ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለውና ግለሰቡ የኤች አይቪ ኤድስ መድኃኒት ለማግኘት ምርመራ ላይ መሆኑን በመግለፅ የጥቁር አንበሳ ሐኪሞች እንዲረዱት በተደጋጋሚ ይመላለስም ነበር ተብሏል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የከባድ የሰው ግድያና የውንብድና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ጥቅምት 11፣ 2014 ዓ.ም ነበር በግለሰቡ ላይ የጥፋተኝነት ብያኔ ያስተላለፈው።
አቃቤ ህግ ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ሃይማኖትን ስለገደላት ግለሰቡ የዕድሜ ልክ እስራት እንዲፈረድበት መከራከሪያ አቅርቦ ነበር።
ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ግለሰቡ ከዚህ በፊት የጥፋት ሪከርድ የሌለበት መሆኑን እንደ አንድ የቅጣት ማቅለያ በመያዝ በእስራት እርከን 36 ስር በማሳረፍ በ21 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑንም ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሰረዳል።
ሃይማኖት ማነች?
የ28 ዓመቷ ሃይማኖት ተወልዳ ያደገችው መተሃራ ከተማ ሲሆን ወላጆቿ ነዋሪነታቸው በአዳማ ከተማ ጎሮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።
የሃይማኖት አባት አቶ በዳዳ ፈይሳ ልጃቸው 2009 ዓ.ም ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ በ'ክሊኒካል ፋርማሲ' በማዕረግ ተመርቃ በዩኒቨርስቲው በመምህርነት ስታገለግል መቆየቷን ቢቢሲ የሃይማኖት ግድያ በተሰማ ወቅት ባናገራቸው ወቅት ተናግረዋል።
ከዚያም ሁለተኛ ዲግሪዋን ለመማር ወደ ጥቁር አንበሳ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተልካ ትምህርቷን በመከታተል ላይ እንደነበረች አስረድተዋል።
"2010 ላይ የጀመረችውን የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት የፊታችን ሰኔ ላይ ትመረቅ ነበር። የመመረቂያ ጽሑፏን ለመጨረስ ወደ ትምህርት ቤት እየተመላለሰች ትሰራ ነበር" ብለዋል አቶ በዳዳ።
"ልጄ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ዩኒቨርሲቲ እስክትገባ ድረስ አንድኛ ነበር የምትወጣው" ሲሉ የልጃቸውን ጥንካሬ ያስረዳሉ።
አቶ በዳዳ ልጃቸው በአገሪቱ አለ በሚል ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ በአንዲህ አይነት አሰቃቂ ሁኔታ መገደል እጅጉን እንዳሳዘናቸው በወቅቱ ተናግረው ነበር