ቻይና በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ አወገዘች

በኤርትራ የሁለት ቀናት ጉብኝት ያደረጉት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ አወገዙ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአንድ ፓርቲ በብቸኝነት በምትተዳደረውና በምዕራባውያን ዘንድ በተገለለችው ኤርትራ ያደረጉትን ጉብኝታቸውን ረቡዕ ከሰዓት በኋላ አጠናቀዋል።

ዋንግ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መወያየታቸውን እና "ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን" ለማጠናከር ፕሬዝዳንቱ በቻይና ጉብኝት እንዲያደርጉ መጋበዛቸውንም የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከስብሰባው በኋላ በጋራ በሰጡት መግለጫ "በዲሞክራሲና በሰብአዊ መብት ሰበብ በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ የሚደረግ ጣልቃገብነትን" አውግዘዋል።

"ቻይና በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማንኛውንም ማዕቀብ ትቃወማለች" ማለታቸውም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ የአሜሪካ መንግሥት በአራት የኤርትራ ተቋማትና በሁለት ኤርትራውያን ላይ በያዝነው ዓመት ማዕቀብ ጥሏል።

ማዕቀቡ የኢትዮጵያን መረጋጋትና አንድነት እያናጋ ነው ባለው ቀውስና ግጭት ውስጥ አስተዋጽኦ አላቸው ያላቸውን የኤርትራ ተቋማትና ዜጎችን ኢላማ ያደረገ መሆኑን የአሜሪካ የፌደራል ግምጃ ቤት በወቅቱ አመልክቷል።

በዚህም መሠረት ዕቀባው የተጣለባቸው ተቋማት የኤርትራ መከላከያ ኃይል፣ የኤርትራ ገዢ ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ፣ ህድሪ ትረስ እና ሬድ ሲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽን ሲሆኑ ግለሰቦቹ ደግሞ አብረሃ ካሳ ነማሪያም እና ሐጎስ ገብረሕይወት ወልደኪዳን የተባሉት ናቸው።

ኅዳር ወር መጨረሻ አካባቢ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው የነበሩት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ጣልቃ ገብነትን ተቃውመዋል።

"ኢትዮጵያውያን ውስጣዊ ችግሮቻቸውን መፍታት ስለሚችሉ ቻይና በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮች ጣልቃ ገብነትን ትቃወማለች" ማለታቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በወቅቱ አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ጉብኝታቸውንም በተመለከተ ቻይና በኢትዮጵያ ላይ ያላትን መተማመን እንደሚያሳይ እና ቻይና ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ያላትን ድጋፍ የሚገልጽ ነው ማለታቸውም የሚታወስ ነው።

ቻይና በቅርብ ወራት በተለይ ደግሞ ከትግራዩ ጦርነት ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ መድረኮች ላይ ድጋፏን ስትገልጽ ቆይታለች።

የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል የሆነችው ቻይና፤ የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ መክሮ የውሳኔ ሐሳብ እንዳያወጣ ሲቃወሙ ከነበሩ አገራት መካከል አንዷ ነች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኤርትራው ጉብኝታቸው በተጨማሪ ቻይና ለአገሪቱ የምትሰጠውን የ100 ሚሊዮን ዩዋን ተጨማሪ ድጋፍ ማስታወቃቸውንም የማነ በትዊተር ገጻቸው ጠቅሰዋል።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በበኩላቸው ቻይና በባለፉት 100 ዓመታት ላስመዘገበችው ትልቅ እድገት እንዲሁም ለቻይና ሕዝቦች እና ለዓለም ሁሉ ያበረከተችውን አስተዋፅኦ አድንቀው መናገራቸውም ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ ቻይና ዓለም አቀፍ ሕግን በማክበር ላይ የተመሰረተ ሚዛናዊ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት እንዲመጣ ላበረከተችው ጉልህ ሚናም አመስግነዋል ተብሏል።

የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ከኤርትራ ጉዟቸው ተከትሎ ለሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ረቡዕ ኬንያ ናይሮቢ የገቡ ሲሆን በቆይታቸው፣ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በመገናኘት በተለያዩ መስኮች የትብብር ስምምነቶችን እንደሚፈርሙ ይጠበቃል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኬንያ በኋላ ቀጣይ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ወደ ሕንድ ውቅያኖሷ ደሴት ኮሞሮስ ያቀናሉ ተብሏል።