ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢንስታግራም ህጻናትን እንዴት ኢላማው እንዳደረገ የአሜሪካ ግዛቶች ምርመራ ጀመሩ
ለህጻናት አደጋ ሊሆን ይችላል የተባለው ኢንስታግራም ህጻናትን እንዴት ኢላማው እንዳደረጋቸው የአሜሪካ ግዛቶች ቡድን እየመረመረ ነው።
ከዲሞክራት እና ሪፐብሊካን ግዛቶች የተዋቀረው ቡድን የሸማቾች ጥበቃ ህጎች መጣሳቸውን ለማወቅ ነው የኢንስታግራምን እና የፌስቡክ ባለቤት ሆነው ሜታን የሚመረምረው።
በማሕበራዊ ሚዲያዎቹ ላይ ምርመራው የተጀመረው የኩባንያውን መረጃ አሳልፈው የሰጡ ግለሰብ ኩባንያው ምርቶቹ ህጻናትን ሊጎዱ እንደሚችሉ እንደሚያውቅ ምስክርነት ከሰጡ በኋላ ነው።
ሐሙስ የሜታ ቃል አቀባይ ማሕብራዊ ሚዲያዎቹ ጤናማ አይደሉም ስለመባሉ አስተባብለዋል።
ስለምርመራው ቀድመው ይፋ ያደረጉት ዴሞክራቷ የማሳቹሴትስ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ማውራ ሄሌይ በትዊተር ገጻቸው "ኢንስታግራም ከወጣቶች ድብርት፣ ከአመጋገብ መዛባት እና ራስን ማጥፋት ጋር የተገናኘ መሆኑን ፌስቡክ ወይም ሜታ ያውቃል" ሲሉ አስፍረዋል።
"ህጎች ከተጣሱ ለይተን እስከመጨረሻው በደል እናስቆማለን"
ሪፐብሊካኑ የኔብራስካ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ዶግ ፒተርሰን ኩባንያዎቹ "ልጆቻችንን ለረዥም ጊዜ ስክሪን ላይ እንዲቆዩ እና መረጃን ለመሰብሰብ በማሰብ እንደ ሸቀጥ ይመለከቷቸዋል" ብለዋል።
የኒው ዮርክ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ሌቲሺያ ጀምስ በበኩላቸው "የማህበራዊ ደር አምባዎቹ እጅግ በጣም አደገኛ ናቸው። በወጣቶች ላይ አካላዊ እና አዕምሮአዊ ጉዳት እንደሚያደርሱም ተረጋግጧል" ብለዋል።
የኢንስታግራም እና የዋትስአፕ ባለቤት የሆነው ፌስቡክ ከበርካታ ቅሌቶች በኋላ ስሙን ወደ ሜታ የቀየረው ባለፈው ወር ነበር።
የሜታ ቃል አቀባይ የቡድኑን ውንጀላ ተቃውመዋል።
ቃል አቀባዩ በሰጡት መግለጫ "እነዚህ ክሶች ሀሰት ናቸው። እውነታውን አለመረዳት ያሳያሉ" ብሏል።
"ወጣቶችን የመጠበቅ ተግዳሮቶች በአጠቃላይ ኢንዱስትሪው ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ ቢሆንም ማንቋሸሽን በመዋጋት፣ ራስን የማጥፋት ሃሳቦችን፣ ራስን መጉዳትን እና የአመጋገብ ችግሮችን ለመቅረፍ ድጋፍ በማድረግ ከኢንዱስትሪውን ቀዳሚ ነው" ሲል አክሏል።
ይህ መግለጫ የቀድሞው የፌስቡክ ባልደረባ ፍራንሲስ ሃውገን አሾልከው ባወጡት ሰነድ ላይ የተመሰረቱ አስደንጋጭ ሪፖርቶችን ተከትሎ የመጣ ነው።
ለአሜሪካ የሕግ አውጭዎች በሰጡት ምስክርነት ኩባንያው የጤና ችግሮችን ሊያስከትል እንደሚችል እያወቀ ምርቶቹን ለታዳጊ ህጻናት ማድረሱን ተናግረዋል።
ኢንስታግራም ልክ እንደሌሎች መተግበሪያዎች እድሜያቸው ከ13 ዓመት በላይ የሆናቸው ብቻ እንዲጠቀሙ ቢፈቅድም አንዳንድ ተጠቃሚዎች ከተቀመጠው ዕድሜ እንደሚያንሱ ኩባንያው እንደሚያውቅ አምኗል።