ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሞሐመድ ሳላህ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በርካታ ጎል ያስቆጠረ አፍሪካዊ ተጫዋች ሆነ
ትናንት እሑድ ዕለት የሊቨርፑሉ የፊት መስመር ተጫዋች ሞሐመድ ሳላህ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሃትሪክ መሥራቱን ተከትሎ፤ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ በርካታ ግቦችን ያስቆጠረ አፍሪካዊ ተጫዋች ሆኗል።
ግብፃዊው ሳላህ ትናንት ጨዋታውን ሲጀምር ከአይቮሪ ኮስታዊው የቼልሲ አጥቂ ዲዲየር ድሮግባ ጋር በ104 ግቦች እኩል ሆኖ ነው።
ነገር ግን ሞሐመድ ሳላህ ቡድኑ ሊቨርፑል በኦሌ ጎነር ሶልሻየር የሚመራው ማንቸስተር ዩናይትድ ላይ በመጀመሪያው አጋማሽ አራት ግቦችን ሲያዘንብ እሱ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል።
በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ጨዋታው በተጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ለራሱ ሦስተኛ እንዲሁም ለሊቨርፑል አምስተኛ የሆነችውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።
በዚህም የ29 ዓመቱ ሳላህ፤ ከዲዲየር ድሮግባ ጋር ሲጋራው የነበረውን የምንጊዜም የፕሪምየር ሊጉ አፍሪካዊ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ክብረ ወሰንን በሦስት ግብ አሻሽሏል።
ሳላህ በአውሮፓውያኑ 2017 ላይ ከሮማ ወደ ሊቨርፑል ከተዘዋወረ በኋላ በፕሪምየር ሊጉ ከታዩ ምርጥ የፊት መስመር ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀስ መሆን ችሏል።
የቀድሞው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋችና በፕሪምየር ሊጉ 95 ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ያኩቡ እንደሚለው፤ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ግብ ማስቆጠር የሚችል ተጫዋች የትኛውም ሊግ ሄዶ ግብ ማስቆጠር አይከብደውም።
ሞሐመድ ሳላህ ደግሞ ወደ ሊቨርፑል በመጣ በመጀመሪያው ዓመት 32 ግቦችን በማስቆጠር በርካቶችን አስገርሟል።
ባለፈው ዓመት ቡድኑ ሊቨርፑል የእንግሊዝ ሻምፒዮን ሲሆን ሳላህ 19 ግቦችን በስሙ ማስመዝገብ ችሎ ነበር።
እንደውም ያን ዓመት በጥሩ አቋም ላይ አለመሆኑ በርካታ ግቦችን እንዳያገባ አደረገው እንጂ በዛኑ ዓመት ከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ሊወስድ ይችል ነበር።
ሞሐመድ ሳላህ ሁለት ጊዜ የቢቢሲ እና የካፍ የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ተጫዋች ሽልማቶችን ማግኘት የቻለ ሲሆን፤ በሊቨርፑል ቆይታውም እስካሁን በዓመት ከ15 ግቦች በታች አስቆጥሮ አያውቅም።
ሳላህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሲመጣ የተጫወተው ለሌላኛው የፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ ቼልሲ ሲሆን ማስቆጠር የቻለው ግን ሁለት ግቦችን ብቻ ነበር።
"በጣም አስተዋይ ነው። እንቅስቃሴው የማይታመን ነው። ትክክለኛ የፊት መስመር አጥቂ አይደለም። ስለዚህ በክንፍ በኩል እየተሳበ ወደ መሐል በመግባት ግቦችን ያስቆጥራል። የት መሄድ እንዳለበት ያውቃል፤ መቼ መሮጥ እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል" ሲል ያኩቡ አድናቆቱን ገልጿል።
ጨምሮም "እንደ ሳላህ ያሉ ተጫዋቾች በዘመናዊ እግር ኳስ ጥቂት ናቸው። እውነት ለመናገር በጣም የተለየ ድንቅ አጥቂ ነው። ባርሴሎና በሜሲ ነበር የሚታወቀው፤ ሊቨርፑል ደግሞ በሞሐመድ ሳላህ። ሁለቱም ለክለቦቻቸው በርካታ ነገሮችን አድርገዋል፤ ትልቅ የሆነ ተጽዕኖ መፍጠር ችለዋል" ብሏል።